Saturday, 29 August 2020 10:42

መንግስት ሃገሪቱን ወደ ብሔራዊ መግባባት የሚወስድ ፖለቲካዊ መፍትሔን እንዲከተል ኦፌኮ አሳሰበ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(11 votes)

   ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ከእስር እንዲፈቱ ተጠየቀ

              መንግስት ከሃይል እርምጃዎች ተቆጥቦ የሀገሪቱን ችግር በፖለቲካዊ ውይይት እንዲፈታ የጠየቀው የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግሬስ (ኦፌኮ)፤ በሀገሪቱ ለተፈጠረው ችግር መፍትሔው ፖለቲካዊ ነው ብሏል፡፡
ኦፌኮ ለአዲስ አድማስ በላከው መግለጫው፤ በኦሮሚያ ክልል የተፈጠረው ፍጥጫ ለሀገሪቷ መረጋጋት እንቅፋት የሚሆን ነው፤ ለዚህም ከሃይል እርምጃ ይልቅ ፖለቲካዊ ውይይት ቀዳሚ መፍትሔ ሊሆን ይገባል፡፡ “ለውጡ አደገኛ መስቀለኛ መንገድ ላይ ይገኛል” ያለው ኦፌኮ፤ ባለፉት ሁለት አመታት የተለያዩ የፖለቲካ ውይይቶችን ለማድረግ ቢሞከርም የተጠበቀውን ያህል ውጤት አላመጣም፤ በዚህም የፖለቲካ ምህዳሩ እየጠበበ ጽ/ቤቶቻችን እየተዘጉ፣አባሎቻችንም እየታሠሩ ነው ብሏል፡፡
ችግሮቹ እየሰፉ እንዳይሄዱ የእርምት እርምጃዎች ይወሰዱ ዘንድ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግስት ባለስልጣናትን በደብዳቤና በቃል በማነጋገር ሲጠይቅ እንደቆየም ኦፌኮ አስታውቋል - በተለያየ ጊዜም ለጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፣ ለፓርላማው፣ ለኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን፣ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድና ለጠቅላይ አቃቤ ህግ ያቀረባቸውን የአቤቱታ ደብዳቤዎችም በመግለጫው አያይዟል፡፡ እስከ ዛሬ ከማናቸውም ምላሽ አለማግኘቱንም አልሸሸገም፤ መግለጫው፡፡  
የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሣ ግድያን ተከትሎ፣ሁኔታዎች የበለጠ እየተወሳሰቡ መምጣታቸውን፣ የአርቲስቱም ግድያ በነፃና ገለልተኛ አካል ሊጣራ ይገባው እንደነበረና በርካቶችን ማሰርም ፖለቲካውን ከማወሳሰብ ያለፈ ውጤት እንደማያመጣ ፓርቲው በተደጋጋሚ ማሳሰቡን፣ ነገር ግን ከመንግስት ቀና ምላሽ አለማግኘቱን አስታውቋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠሩ ፍጥጫዎችና አለመረጋጋቶችም የዚህ ውጤት መሆኑን የጠቆመው ኦፌኮ፤ “ችግሩ የፖለቲካ በመሆኑ በፖለቲካዊ መንገድ መፍትሔ ማበጀት ይገባል” ብሏል፡፡
#ከዓለምም ሆነ ከራሳችን ተሞክሮ እንደምንረዳው የፖለቲካ ችግር በዋናነት የሚፈታው በእስርና ጠመንጃ ሳይሆን በራሱ በፖለቲካ ነው” ያለው ፓርቲው፤ መንግስት የሃይል እርምጃዎችን በአስቸኳይ አቁሞ ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲ አባላትን ከእስር በመፍታት፣ ሀገሪቷን ወደ መረጋጋት፣ ህዝቦቿን ወደ ብሔራዊ መግባባት እንዲመራ ጠይቋል፡፡

Read 12973 times