Saturday, 12 December 2020 00:00

በአገር ክህደት ወንጀል የተጠረጠሩ ፍርድ ቤት እየቀረቡ ነው

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(1 Vote)

- አምባሳደር አዲስ አለም ባሌማ የቻይና የህውሃት የኮሚኒስት ፓርቲ ለመፍጠር ሲሰሩ ነበር ተብሏል
                 - ሜ/ጄ ገብረመድህን ፍቃዱ (ወዲ ነጮ) ለጦርነቱ የገንዘብ ድጋፍ ሲያሰባስቡ ነበር
                               
               ከፀረ ሰላም ቡድኑ ጋር ተቀናጅተው በመስራት በአገርና በህዝብ ደህንነት ላይ ከፍተኛ አደጋ ለማድረስ ሲሰሩ ተገኝተዋል በሚል ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉት የህወሃት ቡድን አባትላ ፍ/ቤት መቅረብ ጀምረዋል።
በፍርድ ቤት ቀርበው ቀጠሮ ከተጠየቀባቸው ተጠርጣሪዎች መካከል ሜጄር ጀነራል ገብረመድህን ፍቃዱ(ወዲ ነጮን) ጨምሮ 7 የመከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ የጦር መኮንኖች፣ አምባሳደር አዲስ አለም ባሌማ፣ የቀድሞ የመከላከያ አካዳሚ ኮሌጅ አመራር  ብርጋዴል ጀነራል አሊጋዝ ገብሬን ጨምሮ 4 ከፍተኛ የጦር መኮንኖች እንዲሁም የቀድሞ የህውሃት ከፍተኛ አመራር  የአምባሳደር ስዩም መስፍን ባለቤትና አንድ ወንድ ልጃቸው ይገኙበታል።
ጦርነቱ በህውሃት ሃይሎች  አሸናፊነት እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ ሲያሰባስቡ ተገኝተዋል የተባሉት ሜጀር ጀነራል ገብረመድህን ፍቃዱ፤ የህውሃት ቡድን በሰው ሃይልና በገንዘብ አቅም የተደራጀ እንዲሆን ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውም ተጠቁሟል።
በተለይ ሜጀር ጀነራል ገብረመድህን ፍቃዱ በመንግስት በጀት ለህውሃት ፀረ-ሰላም ቡድን ሰዎች ሲመለምልና ለ2 ወራት ፍቃድ በመስጠትና ከመንግስት ካዝና አበል በመክፈል፣ በድብቅ ወደ ትግራይ በማስገባት፣ ለቡድኑ ከፍተኛ እገዛ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ፖሊስ በምርመራ  መዝገቡ ላይ አትቷል።
በአገር ክህደት ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉት አምባሳደር አዲስዓለም ባሌማም በፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ 1ኛ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ቀርበው የ14 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ተሰጥቷቸዋል። አምባሳደሩ ከፀረ-ሰላም ቡድኑ ጋር በማበር ፣በአገርና በህዝብ ላይ አደጋ ሊያደርስ የሚችል ተግባር ላይ ተሳትፈዋል ያለው ፖሊስ፤ ተጠርጣሪው ስልጣናቸውን በመጠቀም የአፍሪካ ከፍተኛ አመራሮች በፌደራል መንግስት ላይ ጫና እንዲያሳድሩ ግፊት ሲያደርጉ እንደነበር ገልጿል።
ህገ-መንግስቱንና ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን በሃይል ለመናድ ከሚንቀሳቀሰው የህወኃት ቡድን ጋር በመሆን አገር የማፍረስ እቅድ ሲነድፉ ነበር ብሏል የምርመራ መዝገቡ።
ወጣቶችን በመመልመል  ሁከት ለማስነሳት በየክልሉ ሲያስተባብሩ ነበር የሚል ክስ የቀረበባቸው አምባሳደር አዲስ አለም፤ ከቻይና ከአንድ የቻይና  ባለስልጣን ጋር በመገናኘት የቻይና ህውሃትን የኮሙኒስት ፓርቲ ለመፍጠር ሁኔታዎችን ሊያመቻቹ ነበር ተብሏል።
ተጠርጣሪው በአምባሳደርነት በሚሰሩበት ወቅትም ኢትዮጵያ ከውጪ አገራት ጋር የነበራትን መልካም ግንኙነት ለማቋረጥና ለማበላሸት ሲሰሩ እንደነበርም ተመልክቷል። ከዚህ በተጨማሪም ከኦነግ ሸኔ አባላት ጋር መረጃ በመለዋወጥና የአገር ምስጢርን አሳልፈው በመስጠት ከፍተኛ ወንጀል ፈፅመዋል ሲል ፖሊስ በችሎቱ ተናግሯል። ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሰራዊት አባት ላይ የተፈጸመው ጥቃት ተግባራዊ እንዲሆን ሁኔታዎችን ሲያመቻቹ እንደነበርም ተገልጿል። ፖሊስ ሌሎች ማስረጃዎችን ለማሰባሰብ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት በጠየቀው መሰረት ፍ/ቤቱ 14 ቀናት  የምርመራ ጊዜ መፍቀዱንም ለማወቅ ተችሏል።
ከትናንት በስቲያ ፌደራል ከፍተኛው ፍ/ቤት አራዳ ምድብ 1ኛ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት የቀረቡት የህወሃት ከፍተኛ አመራር የአቶ ስዩም መስፍን ባለቤትና ወንድ ልጃቸው አግአዚ ስዩም ላይ ፖሊስ ምርመራ እያካሄደ መሆኑንና ምርመራው ባለመጠናቀቁም ተጨማሪ ጊዜ እንዲፈቀድለት ጠይቆ፤ ተጨማሪ 8 ቀናት  ጊዜ ተሰጥቶታል።
ፖሊስ ለፍ/ቤቱ እንደገለጸው፤ የአምባሳደር ስዩም መስፍን ባለቤት ወ/ሮ ፈለገ ህይወት በርሄና ልጃቸው አግአዚ ስዩም፣” ከመስከረም 30 በኋላ መንግስት የለም” በማለት ከህውሃት ቡድንና ከኦነግ ሸኔ አባላት ጋር በመመሳጠርና ተልእኮ በመቀበል፣ በአዲስ አበባ ከተማ ሁከት ለመቀስቀስ ሲንቀሳቀሱ አግኝቻቸዋለሁ ብሏል። በአምባሳደር ስዩም ስም ተመዝግበው  በሚገኙ ቤቶች ላይ ባደረገው፤ ፍተሻም፤ ሁለት ሽጉጦችን ማግኘቱን ፖሊስ ቢያስታውቅም፤ ወ/ሮ ፈለገ ህይወት፤ ሽጉጦቹ አንደኛው ባለቤቴ ራሱን  እንዲጠብቅበት ከመንግስት የተሰጠው ሲሆን ሌላው ደግሞ ከውጪ አገር በስጦታ የተሰጠው ነው ብለዋል። ፍ/ቤቱ ፖሊስ ባቀረባቸው ክሶች ላይ  ተጨማሪ ማስረጃ እንዲያሰባስብ  የ8 ቀናት ጊዜ የፈቀደ ሲሆን ተጠርጣሪዋ እናት “የአእምሮ ህመምተኛ ነው የተባለው ልጃቸው መድሃኒት ማግኘት የሚችሉበት ሁኔታ እንዲመቻች” ትዕዛዝ ሰጥቷል።
ፖሊስ በቀጣይም በአገርና በህዝብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ለማድረስ አሲረዋል ባላቸው ተጠርጣሪዎች ላይ የሚያደርጋቸውን ምርመራዎችና  ፍርድ ቤት የማቅረቡ ሂደትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል  ተገልጿል።



Read 2717 times