“በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የተካተቱት መጣጥፍ (ወግ) ሀሳቦች…በስድስት አመት ጊዜ ውስጥ የተፃፉ የግል እይታዎቼ ናቸው፡፡ ነገር ግን የግል ዕይታም ቢሆን የሚመነጨው ከአጠቃላይ የተጨባጭ እውነታ ነው፡፡ በአጭሩ ከእናንተ፡፡ ባይሆን ኖሮ እኔም የምጽፍበት እናንተም የምታነቡበት ምክንያት ባልኖረ ነበር” ብሏል ሌሊሳ ግርማ - በመፅሃፉ፡፡ በመጽሐፉ ጀርባ ላይ አስተያየት የሰጠው አንጋፋው ደራሲ አዳም ረታ፤ “የሌሊሳን ሱሪያሊስት ምናባዊ ግራ ገብ ታሪኮች የተወሰኑትን ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ አንብቤአለሁ፡፡ ራሳቸውን የቻሉ ወጥ እና አጫዋች በመሆናቸው እወዳቸዋለሁ…የሱን ጽሑፍ ከተለመዱት የሥነጽሑፍ ዘዬዎች አንፃር መመልከት ይከብዳል፤ የአፃፃፍ ስልቱ ከየትኛው ዓይነት የሥነ ጽሑፍ ዝርያ የበቀለ እንደሆነ መግለጽ ማለቴ ነው፡፡” በማለት ስለ ፅሁፎቹ ያብራራል፡፡ ገጣሚና ደራሲ ነቢይ መኮንን በበኩሉ በሰጠው አስተያየት፤ “ሌሊሳ ግርማ በአፃፃፍ ስልቱ ከተለመደው ወጣ ይላል፡፡ ሆኖም ወጣ ላሉት ብቻ ሳይሆን ገባ ላሉትም ይጥማል” ብሏል፡፡ በ197 ገፆች የተቀነበበው መጽሐፉ በ39 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡
ደራሲው ከዚህ ቀደም “የነፋስ ህልም” የተሰኘ የአጫጭር ልብወለዶች መድበል ለንባብ ማቅረቡ ይታወቃል፡፡