Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 08 September 2012 12:59

ቦብ ጌልዶፍ መንግስታት የገቡትን ቃል እንዲያከብሩ መታገሉን ቀጥሏል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

አየርላንዳዊው የሮክ ሙዘቀኛ ፤ በጎ አድራጊ እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቦብ ጌልዶፍ የዓለም ሃብታም አገራት በድህነት ለሚሰቃዩ ህዝቦችና አገሮቻቸው እርዳታ ለመስጠት የገቡትን ቃል አክብረው እንዲሰሩ መታገሉን እንደቀጠለ ተገለፀ፡፡ ሰር ቦብ ጌልዶፍ በ1984 እ.ኤ.አ ሚጅ ኡሬ ከተባለ ሌላ ሙዚቀኛ ጋር በኢትዮጵያ ተከስቶ ለነበረው ድርቅና ረሃብ ባንድ ኤይድ የተባለ የበጎ አድራጎት ተቋም በማቋቋም በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በሚዘጋጁ የሙዚቃ ኮንሰርቶች፤ ተያያዥ ንግዶችና የቅስቀሳ ዘመቻዎች ላይ በመሳተፍ ለእርዳታ የሚውል ገቢ ሲያሰባስብ ቆይቷል፡፡ በ1985  ላይቭ ኤይድ በሚል ስያሜ ቦብ ጌልዶፍ እና አጋሮቹ በእንግሊዝ በአሜሪካ፤ በጀርመንና በአውስትራሊያ የሙዚቃ ኮንሰርቶች ያቀረቡ ሲሆን   በ2005 እ.ኤ.አ ላይም ላይቭ ኤይት  የእርዳታ ማሰባሰቢያ ዘመቻ ተካሂዶ ነበር፡፡

ድህነትን ታሪክ እናድርገው በሚል፡፡ ሰር ቦብ ጌልዶፍ ከዘመቻው በተያያዘ የዓለም ሃያላን መንግስታት ለድሃ አገራት በተለያዩ ጊዜያት እርዳታ ለመስጠት የገቡትን ቃል አለማክበራቸው እንደሚያሳስበው በተደጋጋሚ ሲገልፅ ቆይቷል፡፡ ሰር ቦብ በዚህ የበጎ አድራጎት እንቅስቃሴው ለኖቤል የሰላም ሽልማት ታጭቶ የነበረ ሲሆን ከእንግሊዝ ንግስት ‹የሰላም ሰው› የሚል የክብር ማእረግ አግኝቷል፡፡በላይቭ ኤይድ እንቅስቃሴ ከተሳተፉ ሙዚቀኞች መካከል ሰር ቦብ ጌልዶፍን ጨምሮ ቦኖ፤ ስቲንግ፤ ፊል ኮሊንስ፤ ጆርጅ ማይክል፤ ዱራን ዱራን የሙዚቃ ባንድ፤ ዩ2፤ ማዶና፤ ኤልተን ጆን፤ ኤሪክ ክላፕተን ይገኙበታል፡፡

ከ27 ዓመታት በፊት የእነ ቦብ ጌልዶፍ የሙዚቃ ቡድን ለኢትዮጵያ ረሃብ የእርዳታ ገቢ ማሰባሰቢያ ኮንሰርቶችን በለንደን ዌምብሊ እና በአሜሪካ ፊላደልፊያ በሚገኘው የጆንኤፍ ኬኔዲ ስታዲዬሞች አቅርቦ ነበር፡፡ በወቅቱ በለንደን 72ሺ በፊላደልፊያ ደግሞ ከ100ሺ በላይ  ታዳሚዎች ኮንሰርቶቹን እንደተከታተሏቸው የሚታወስ ሲሆን በተመሳሳይ መነቃቃት በጀርመን እና በአውስትራሊያ ሌሎች ኮንሰርቶች ተካሂደዋል፡፡  ከኮንሰርቶቹም 150 ሚሊዮን ፓውንድ ገቢ ተሰባስቧል፡፡ በ2005 እ.ኤ.አ ላይ በተደረገው  የላይቭ ኤይት ገቢ ማሰባሰቢያ የሙዚቃ ኮንሰርት ከመላው ዓለም የተውጣጡ 1000 ሙዚቀኞች አስተዋፅኦ ማድረጋቸው ሲታወቅ  ድህነትን ታሪክ እናድርግ በሚል መሪ ቃል የቀረበውን  ዝግጅት በመላው ዓለም እስከ 3 ቢሊዮን ተመልካች እንደተመለከተው ታውቋል፡፡ በዚህ ዘመቻም የቡድን ስምንት አገራት ለአፍሪካ እና ለድሃ አገሮቿ የሚሰጡትን የእርዳታ ገንዘብ ከ25 ቢሊዮን ፓውንድ ወደ 50 ቢሊዮን ፓውንድ በእጥፍ እንዲያሳድጉ ግፊት መደረጉም ይታወሳል፡፡ ይሁንና ባለፉት ሶስት ዓመታት  በመላው ዓለም በተከሰተው የኢኮኖሚ ቀውስ የተነሳ መንግስታት በገቡት ቃል መሰረት ለአፍሪካ አገራት የሚያደርጉትን የገንዘብ እርዳታ ተግባራዊ ማድረግ ተስኗቸዋል፡፡ የሰር ቦብ ጌልዶፍ እንቅስቃሴ ያስገኘው የእርዳታ ገንዘብ ለድሆች ከመለገስ ይልቅ ለመሳርያ መግዣ በመዋል ተመዝብሯል የሚሉ ዘገባዎች ላለፉት ሰባት ዓመታት ሲናፈሱ የቆዩ ሲሆን  ዘመቻውንም ክፉ ጥላሸት ሲቀባ ቆይቷል፡፡ከወራት በፊት በኢትዮጵያና ሶማሊያ ድንበር በምትገኝ ዶሎ አዶ በተባለች ስፍራ ጉብኝት ያደረገው የ60 ዓመቱ ሰር ቦብ ጌልዶፍ የዓለም ሃያላን መንግስታት ቃላቸውን አለማክበራቸው ቢያሳዝነውም የሚንቀሳቀስባቸው እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገራት መንግስታት ካሉበት የድህነት አረንቋ ለመውጣት በሚተገብሩት ፖሊሲ እና የልማት አስተዳደር መፅናናቱን ተናግሯል፡፡ የላይቭ ኤይድ የእርዳታ እንቅስቃሴ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገራት ውጤታማ መሆኑን ያደነቀው ሰር ቦብ ጌልዶፍ በዶሎ አዶ ባደረገው ጉብኝት በአካባቢው በተዘረጋ የመስኖ ፕሮጀክት ስኬታማ ስራዎች መመልከቱ ፤የአካባቢው ልጆች ወደ ትምህርት ቤት መሄዳቸውን ማስተዋሉ እና በሞባይል ስልኩ በአካባቢው ኔትዎርክ ማግኘቱን ያስገረመው ሲሆን በተፈጠረው መሻሻል  መደመሙን ዘገባውን ለአይሪሽ ታይምስ በኩራት ተናግሯል፡፡

 

 

Read 1528 times Last modified on Saturday, 08 September 2012 13:03