Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 27 October 2012 11:12

ጥሩነሽ ለሁለት የኮከብነት ምርጫዎች ታጨች

Written by 
Rate this item
(8 votes)

አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ በ2012 ምርጥ ብቃት አሳይተዋል ከተባሉ የዓለማችን ብቁ አትሌቶች ተርታ በሁለት የሽልማት ምርጫዎች እቹ ሆና ተሰለፈች፡፡ በእጩነት የቀረበችባቸው የአይኤኤኤፍ የዓመቱ ሴት ኮከብ አትሌት ምርጫ እና የአትሌቲክስ ዊክሊ መፅሄት የአመቱ ምርጥ አትሌት ምርጫዎች ናቸው፡፡ በአይኤኤኤፍ የ2012 የዓመቱ ኮከብ ሴት አትሌቶች ከቀረቡ አስር እጩዎች አንዷ የሆነችው አትሌት ጥሩነሽ ለተመሳሳይ ሽልማት ስትታጭ የዘንድሮው ሁለተኛዋ ነው፡፡ላለፉት 4 ዓመታት በጉዳት ከውድድር ርቃ ከቆየች በኋላ ባለፈው ክረምት በለንደን ኦሎምፒክ በ10ሺ የወርቅ እንዲሁም በ5ሺ የነሐስ ሜዳልያ የወሰደችውና ወደ ጎዳና ሩጫ በመግባት ከኦሎምፒክ በኋላ የቡፓ ግማሽ ማራቶንን ያሸነፈችው አትሌቷ በዓለም አትሌቲክስ እንደ ብርቅዬ ኮከብ ከሚጠቀሱት አንዷ ሆና ቀጥላለች፡፡

ለ2012 የዓለም ኮከብ አትሌት በሁለቱም ፆታዎች የቀረቡ አስር እጩዎችን የመለመሉት የአይኤኤኤፍ የኤክስፕርቶች ፓናል አባላት ሲሆኑ የመጨረሻዎቹን ሶስት እጩዎች ለመለየት የዓለም አትሌቲክስ ቤተሰቦች በኢሜል የሚሰጡት ድምፅ ሰሞኑን በይፋ እንደሚጀመር ታውቋል፡፡ በሌላ በኩል ታዋቂው አትሌቲክስ ዊክሊ መፅሄት በ2012 ምርጥ ሴት አትሌቶችን አንባቢዎቹ እንዲመርጡ ካቀረባቸው እጩዎች ጥሩነሽ ዲባባ እንደምትገኝበት ታውቋል፡፡ የ70 አመታት ልምድ ያለው መፅሄቱ ጥሩነሽ ዲባባ በለንደን ኦሎምፒክ ባስመዘገበችው ውጤት በውድድር ዓመቱ ከታዩ ዓለም አቀፍ ምርጥ አትሌቶች አንዷ መሆኗን ገልጿል፡፡
አይኤኤኤፍ 100ኛ ዓመቱን መታሰቢያ ባደረገበት ዝግጅት የ2012 የዓለም ኮከብ አትሌት በመሆን የሚመረጡት አሸናፊዎች ከወር በኋላ ባርሴሎና በሚደረግ ስነስርዓት በይፋ ታውቀው ይሸለማሉ፡፡ በሴቶች ምድብ የቀረቡት አስር እጩዎች ኢትየጵያዊቷን ጥሩነሽ ዲባባ ጨምሮ የኒውዝላንዷ ቫለሪ አዳምስ፤ የግሬት ብሪትኖቹ ጄሲካ ኤኒስ ፤ የአሜሪካዎቹ አሊሰን ፊሊክስ ፣ሳንያ ሪቻርድስና ብሪትኒ ሪስ፤የጃማይካዋ ሼሊ አን ፈሬዘር፤ የራሽያዋ የለና ላሽማኖቫ ፤ የአውስትራሊያዋ ሳሊ ፒርሰን እና የቼክ ሪፖብሊኳ ባርቦራ ስፖታኮቫ ናቸው፡፡ በ30ኛው ኦሎምፒያድ ኢትዮጵያን ለወከሉ ኦሎምፒያኖች የኢትዮጵያ መንግስት ከ3 ሳምንት በፊት ሽልማት ሲሰጥ ጥሩነሽ ዲባባ በ3 ኦሎምፒኮች ከፍተኛውን የሜዳልያ ውጤት ያስመዘገበች አትሌት በመሆኗ በ21 ካራት ወርቅ የተሰራና 100 ግራም የሚመዝን የክብር ሜዳልያ ከክቡር ፕሬዝዳንት ወልደጊዮርጊስ እጅ መቀበሏና 920ሺ ብር የምትገመት ቶዮታ ያሪስ መኪናም መሸለሟ ይታወሣል፡፡
ከለንደን ኦሎምፒክ በኋላ በ3 ኦሎምፒኮች በ10ሺ ሁለት ወርቅ፤ በ5ሺ 1 ወርቅ እና ሌላ ነሐስ ሜዳልያ በመሰብሰብ የኢትዮጵያን አንደ’ የሜዳልያ ውጤት ያስመዘገበችው ጥሩነሽ በ10ሺ እና በ5ሺ ሜትር በ2008 እኤአ ቤጂንግ ላይ ድርብ የወርቅ ሜዳልያ በማግ’ት በታሪክ የመጀመርያዋ አትሌት መሆኗ ይታወቃል፡፡ በ5ሺ ሜትር እና በ15 ኪሎሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ሁለት የዓለም ሪከርዶችን ይዛ የምትገኘው አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ በ10ሺ ሜትር የኢትዮጵያ እንዲሁም በ5ሺ ደግሞ የኢትዮጵያና የዓለም ሪከርድንም እንደያዘች ነች፡፡
በ2008 እኤአ ላይ በትራክ ኤንድ ፊልድ መፅሄት የዓመቱ ኮከብ አትሌት የነበረችው ጥሩነሽ በዚያው የውድድር ዘመን በአይኤኤኤፍ የኮከብ አትሌት ምርጫ ሁለተኛ ደረጃ ማግኛቷ የሚታወስ ሲሆን በምትወዳደርበት የ10ሺ እና የ5ሺ ሜትር ርቀቶች የዓመቱ ምርጥ አትሌት ተብላ በአይኤኤኤፍ ለሶስት ግዚያት ተሸልማለች፡፡

Read 5760 times