Saturday, 22 April 2023 20:06

“የደመና ሳቆች”ን… ከጠቆረ ደመና ሰማይ ስር

Written by  አብዲ መሐመድ
Rate this item
(3 votes)

ከሰሞኑ በበልግ ዝናብ ሰማዩ ሲዳምን፣ የደመና ሳቆችን እንደዘበት ገልጬ ማንበብ ጀመርኩ፡፡ ለስንተኛ ጊዜ እንደሆነ አላውቅም መቀጠል እንጂ ማቋረጥ አልቻልኩም፡፡ ደራሲና ሀያሲ ደረጀ በላይነህ ጠፍቶብኛል፡፡ ባልገባኝ ምክንያት ብዕሩ ይናፍቀኛል፡፡ አዎ ብዕሩ አብሮኝ አድጓል፡፡ የሂሶቹ ትዝታ ውል እያለ የጎድን አጥንቴ መሀል ያለችው ልቤን ዛሬም እንደ አዲስ ያሞቃታል፡፡ ጋዜጣ ላይ እንደቆሎ ፈሰው ያለገደብ ዘግኜ ላጣጣምኳቸው ስራዎቹ ዘወትር የማይበርድ ልዩ ፍቅር አለኝ፡፡ አቤት ይሄ ደራሲ ስንት ችግሬን አስረስቶ በውብ የምዕናቡ አለም አሳርፎ አስጠልሎኛል መሰላችሁ? ስንቴስ ይሄን ደስታ ለምጄ ጥበብ አምድ ላይ ደረጀን ላነብ ተንሰፍስፌ ባጣሁት ቁጥር ድባቴ ክፉኛ መቶኛል መሰላችሁ?
 ቅዳሜ በመጣ ቁጥር እንደ እሳት እራት ለሳምንት ከጋረደኝ የዘመን ጽልመት ሸሽቼ ጽሁፎቹን የብርሃን ተስፋ ሙቀት ፍለጋ እጠጋለሁ፡፡ ያኔ ፊቴ አበባ ይለብሳል፣ በሁለመናዬ የደስታ ችቦ ይለኮሳል፡፡ ደስ የሚል ስሜት ነፍሴን ያናውጣታል፡፡ ከወረሰኝ ጨለማ መንጥቀው ተስፋዬን ያለመልማሉ፣ ነገዬን ያፀኸያሉ፡፡ ብዕሩ ደመናን ማሳቅ፣ የቀትር ፀሃይን ማፍነክነክ ይሆንለታል፡፡ የተስፋ ፀደይን እያረዘመ የጭንቅ ክረምትን ማሳጠር ይዋጣለታል፡፡ የገጣሚ ስስ ነፍሱ፣ የደራሲነት የቋንቋ ክህሎቱ…ከካበተ የንባብ ልምዱ ጋር ተጋምደው ደረጀን ዘርፈ ብዙ ባለተሰጥኦና የተለየ ጠሊቅ የጥበብ ሰው አድርገው ሰርተውታል፡፡ባለብዙ ቀለምዋ ህይወት አያሌ ጠብታዎች አሏት፡፡ እንደ ሻማ ጠብታ ቀልጠው፣ በዘመን ሰም ተወልውለው ሲያበቁ የሚቀመጡ፣ በልብ ውስጥ እየተፍለቀለቁ የሚኖሩ፡፡ ደረጀ በደመና ሳቆች ከእነዚህ ልቡ ውስጥ ለዘመናት ከኖሩ ጠብታዎች መሀል፣ በሁለት ክፍል ሰድሮ የልጅነትና የብሔራዊ ውትድርና ህይወቱን ተጠቦባቸዋል፡፡ በውበትና ዘይቤ አላቁጦ በተዋቡ ቋንቋዎቹ ከሽኖ ከትቦልናል፡፡ ደረጀ ሁለቱን የህይወት መልኮች በአንድ መጽሐፍ ውስጥ፣እንደ አለማችን ዝነኛው ደራሲ ሌቭ ቶልስቶይ አጠቃሎ ያቀረበ ትልቅ ደራሲያችን ነው፡፡ በርግጥ የቶልስቶይን እውነተኛ የህይወት ታሪክንም ብንገልጥ ከልጅነት፣ ከውትድርና እንዲሁም ከስነጽሁፍ ብዙም የራቀ አይደለም፡፡ በአለም ህብረተሰብ ዘንድ ከፍተኛ እውቅናን ያተረፈው የሩሲያው የብዕር ሰው፣ የተለያዩ የሕይወት ምኞትና እቅዶች የሚፈራረቁበት ደራሲ እንደነበር ከህይወት ታሪኩ አናት ተዘግቦ እናገኛለን፡፡ በአንድ በኩል ወታደር ለመሆን ያስባል፣ በሌላ በኩል ደግሞ በመንደሩ ለገበሬ ልጆች ትምህርት ቤት ለመክፈት ያልማል፡፡ እንደገና ደግሞ ባለ ሀይሉ የስነጽሁፍ ሥራውን ለመጀመር ያቅዳል፡፡ ወጣቱ ቶልስቶይ የሕይወቱን አቅጣጫ መወሰን የግድ ስለሆነበት በ1851 በታላቅ ወንድሙ ምክር ወደ ካፍካዝ በመጓዝ በወታደርነት ሙያ ተሠማራ፡፡ በካፍካዝ በውትድርና ላይ ሆኖም የሥነጽሁፍ ሥራውን አላቋረጠም፡፡ ልጅነት የተባለውን ከታላላቅ የሩሲያ ደራሲያን ጎን ሊያሰልፈው የቻለውን የፈጠራ ስራውን ያጠናቀቀው በዚሁ በውትድርና የህይወቱ ምዕራፍ ላይ ሆኖ ሳለ ነበር፡፡ ቶልቶይ ከስነጽሁፍ ባሻገር በጦርነቱ  አውደ ውጊያም ጉልህ ሚና ተጫውቷል፡፡ በታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ ባለው በሴባስቶፖል ጦርነት ግዛት ለመውረር የመጣውን ጦር በመቋቋምና አደገኛ በሆኑ የውጊያ ቦታዎች ላይ ሁሉ ግንባር-ቀደም ሆኖ በመግጠም፤ ጀግንነቱንና ቆራጥነቱን በይፋ አስመስክሯል፡፡ ቶልስቶይ የጦርነት እውነተኛ ገጽታን፣ የሩሲያ ወታደሮች ጀግንነትን ከፍተኛ ተቀባይነትንና ዝናን ባተረፉለት “የሴባስቶፖል ትረካዎች” እና “ጦርነትና ሰላም” በተሰኙ ሥራዎቹ በሚገባ ገልጧል፡፡ በዚህ መጽሐፉ የተጨቆነውና አማኙ የሩሲያ ሰፊ ህዝብ ለእናት ሀገሩ ለሩሲያ  ሲል አንዲት ሕይወቱን ሳይሳሳ ለመስጠት በቆራጥነት የተነሳ መሆኑን በግልጽ አስመስክሯል፡፡…      የኛው ደረጀ በደመና ሳቆች ውስጥ ያነሳው ጭብጥ ከቶልስቶይ የህይወት አውድ እሚመሰልና እሚስተካከል ትርክት የሚቀነቀንበት ኖቭል ነው ማለት እንችላለን፡፡ በራሱ ቀለም የራሱን ሀገር በቀል ጭብጥ ይፈለቅቃል፡፡ ደረጀ ከዚህ ድርሰቱ ቀደም ሲል ለህትመት አብቅቷቸው ከነበሩ ሰባት መጽሐፍቶቹ (አጫጭር ልቦለዶች፣ ግጥሞችና የፍቅር ደብዳቤዎች) በተለየ የልጅነት ዘመንና የደርግ ውትድርና  ወሳኝ ጥያቄዎችና ችግሮች በስፋት የገለፀበት ድንቅ መጽሐፉ ነው፡፡  በወጣትነት ዘመን እየተንፈቀፈቁ የሚወጡ ግንፍል የሀገር ፍቅር ስሜቶች…ከነ‘ታሪካዊ ሁነቶች በተጨባጭ በማቅረቡ የደመና ሳቆችን በተለየ አትኩሮት እንድናየው ያደርገናል፡፡
ልጅነት እንደ ጥንቅሽ እየተላጠ የሚበላ ጣፋጭ ነው፡፡ እዚያ በክፍል አንድ፣ በአስራ ዘጠኝ ምዕራፎች ስር አፍላነት ደርቷል፡፡ ዋናው ገፀባህሪ ደጀኔ ልጅነቱን የሚያዋዙለት አራት መሰሎቹ አሉ፡፡ ሳርኬ፣ ሻረው፣ ምንዳና ደመና ናቸው፡፡ መቼቱን ሲዳሞና ተፈሪ ኬላ አድርጎ አስገራሚ ህይወታቸው ይተረክበታል፡፡ ምንዳ ዱለኛ ነው፣ ሻረው ድንጉጥ ነው፡፡ ደመና ቀብራራ ነው፣ ሳርኬ ሀብታምና ዘናጭ ነው፡፡ ከሰው ግቢ የደረሰ ዘይቱንና ትርንጎ ለመቅጠፍ መከራ እሚባሉ ፣ በድፎ ዳቦ፣ በጉዝጓዝ ሥጋ ድግስ እሚራኮቱ ማቲዎች… ማደጋቸውን አንድ ሴት ለአምስት በመውደድ በይፋ አውጀዋል፡፡ የፍቅር ደብዳቤ ለተፈቃሪ አሰለፈች በመፃፍ የራሳቸው ለማድረግ በማለምና ካልተስማማች በቡድን ለመጥለፍ ተስማምተዋል፡፡ የቡድን ህይወት ነው፡፡ በየተራ ይሰራረቃሉ፣ አንዳንዱ ፍራፍሬ…ሌላው እህቱንም ይሰረቃል፡፡ ልጅነት ነውና መቀያየም የለም፡፡ “እናንተ ህፃናት አይደላችሁ? ልባችሁ ያለ እድሜያችሁ አድጓል!” ባልተጠበቀ ምላሿ ጊዜያዊ መበርገግ እንጂ ወደ ኋላ ማፈግፈግ አይታይባቸውም፡፡ በድንጋጤ ብቻ ያልተገታ ሌላ ሙከራ ደግሞ ይጠነሰሳል፡፡ ሮማንን የመጥለፍ ውጥን!...እንዲህና እንዲያ እያለ እሚሽከነተር ፍሰት፣ በልጅነት ዜማ ውስጥ ሆድ የሚያባባ ነገር፣ አንዳች ልብ የሚያስደስት ጨቅላነት ውስጥ ያለ ስሜት፣ ወይም የሆነ ሊተረጎም የማይችል ቋንቋ በነፍስ ሀዲድ ላይ ይንከባለላል፡፡ ነፍስ የምትለው ነገር አላት፡፡ ግን ለማንም አይሰማም፡፡ በደጀኔና በትርሲት በኩል የሚደመጠው የመፈላለግ እንጉርጉሮ ከልብ ይልቅ ለነፍስ ቅርብ ነው፡፡ የትርሲት ነገር የማይሆንለት ደጀኔ ድብቅ ፍቅሩ እንዲታወቅበት ስለማይፈልግ ሸሽጎ መቀመጥን መርጧል፡፡….“የትርሲት ነገር አይሆንልኝም፡፡ ጓደኞቼን ሁሉ ብወድም እንደሷ አይሆኑም፡፡ ትርሲትን አስባታለሁ፡፡ እሷን ለማግኘት ነበር ሀሳቤ፡፡ ትልቅ ስሆን ባልዋ ብሆን ይሄኔ አብረን እንተኛ ነበር፡፡ ታቅፈኛለች፣ ምሳና ራት ትሠራልኛለች፣ አብረን እንኖራለን፡፡ ደስ ይላል! ሳቅፋት ደስ ይለኛል፣ ስስማት ደስ ይለኛል፣ ምንም አናደርግም ግን እሞቃታለሁ፤ ትሞቀኛለች፡፡ እንደ ብርድ ሰዓት ከሰል ትሞቀኛለች፡፡” (ገጽ 33)    
  ትርሲት በሰብዕና ጠንካራ ሆና ተስላለች፡፡ መጽሐፍት በበቂ ሰርተዋታል፡፡ ወታደር ቤት በየሳምንቱ ጉንጉን፣ ጣምራ ጦር የመሳሰሉ መጽሐፍትን ይዛላት እየመጣች አስነብባዋለች፡፡ ብዙ ልፍስፍስ አይደለችም፡፡ በብዙ አቅጣጫ ማየት ትችላለች፡፡ ምናልበት ቅሽምናዋ በፍቅር ስትያዝ ነው፡፡ ደጀኔን የሱን ያህል መሠረቱን አፍላነት ላይ በጣለ ከልቧ ታፈቅረዋለች፡፡…“አትፍራ የቀድሞዋ ትርሲት ነኝ!...ያቺ የምትወድህ! አንተም አቅፍ እያደረክ ጨለም ያለ ቦታ እቅፍ አድርገህ የምትስማት፣ ማስቲካ በኪስህ ደብቀህ የምትሰጣትና ደብቃ የምትቅበልህ!”  ደጀኔ አጠገቡ ካለችው ሙሉ የመላመድ መውደድ ውስጥ ወድቆ ይሳሳታል፡፡ ይሁንና ህሊናው ትርሲትን እያመጣ ሲወቅሰው ሲያሰቃየው፣ እንዴት ከእሷ እጅ ማምለጥ እንዳለበትና የሚያስለቅሰው ሙግቱን፣ የሚሰድበው ህሊናውን… መውተርተሩን ሁሉ ከመጽሐፉ እናነባለን፡፡
ሀገሪቱ በቀይ ሽብር መንፈስ በምትናጥበት ወቅት ልጅነት ከአብዮት አኩል ተፋፍሞ ቀጥሏል፡፡ የትረካው ጥንስስ ድህረ አብዮት ጅማሬ ላይ ነው፡፡ እናቶች…ይሄ አብዮት መከራ አሳየን!....ሁሌ ጭፈራ!...ሁሌ ዘፈን! ሀገሪቱ የማንም መጫወቻ ሆነች! አይ ስምንተኛው ሺህ…የስንት ጀግና ሀገር! ሲሉ…የፈረደባቸው ልጆች ደግሞ ለሰልፉና ለጭፈራው ሲሉ… አብዮት ይኑርልን! ይላሉ…የልጅ ነገር፣ ልባቸው ከሰልፉ፣ ዘፈኑ፣ ባንዲራው መፈክሩ ላይ ነውና ደስ ይላቸዋል፡፡ የዛን ጊዜዋ ሲዳማ ወደ አንድ መሶብ የሚዘረጉ ብዙ የህፃናት እጆች ያሉባት ትንሽ ከተማ ናት፡፡ እብድና ዱርዬ ፍየል ከሌለ ከተማ ይሞታል እንዲል ደጀኔ! ትኩስ ዳቦ እየበላ ልቡ ያበጠው የረዲ አህያ፣ ለከተማዋ ውበትም ድምቀትም ነበር፡፡ የጥቂት ቤተሰቦች መኖሪያና የተለያየ ቋንቋ የሚናገሩ፣ ብዙ ወንዝ ተሻግረው የመጡ፣ ነገር ግን ብዙ ልዩነታቸውን ጥለው ልባቸው አንድ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች መናኽሪያም ነበረች፡፡ አይኖችዋን በሚገባ ያልገለጠች፣ ግን ደግሞ አይናቸውን የገለጡና ከከተማዋ አቅም በላይ የሠለጠኑ ሰዎችም አልጠፉባትም፡፡
ደረጀ በዚህ መጽሐፉ በምስል ከሳች ብዕሩ ይህንን የከተማዋን ታሪካዊ ሁነት፣ የነዋሪዎቿን ማህበራዊ ትስስር ከኖረበት የደርግ የዘመን መንፈስ ጋር አሰናስሎ ሰፊ ቦታ በመስጠት አሳይቷል፡፡  በክፍል ሁለት የታሪኩ ገፀባህሪያት እድገት የሚከናወነው ብሔራዊ ውትድርና እና አየር ወለድ ማሠልጠኛ ማዕከል ውስጥ ሆኖ ከራሱ ከትረካው አወቃቀርና እድገት ጋር ነው፡፡ በሙሉ ልብ መማር የሚቻልበት ዘመን ቀረ፡፡ ገና በለጋነት መቀጠፊያ ዘመን እውን መሆኑ ገሀድ ሆነ፡፡ ተስፋ የሚታይበት አድማስ ሸሸ፡፡ የወጣቶች ተስፋ ዩኒቨርስቲና ኮሌጅ ሳይሆን (ደጀኔ አንዱ ነው) ጦር ሜዳ እየሆነ ሲሄድ ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር ሲባል የመዳረሻ ፍፃሜ ታሪክ ያኮበኩባል፡፡ ሀገር መከራ ገባች፡፡ ጣሯ በዛ፡፡ ወይ ጊዜ! እግዜር የተጣለው ዘመን፡፡ ክፉ ዘመን ነበር፡፡ ንጋት ከምሽት የበለጠ ተስፋ የሚያጣበት ዘመን አልነበረም፡፡ ሁሉ ነገር የጨለመበት፡፡ በስጋት የተሞላ ጊዜ! ሰው ሁሉ ስለተስፋ የማያወራበት፣ ሁሉም ሰው ነገን በውበቱ አይጠብቀውም፣ በፍርሃት እንጂ፡፡ ተማሪ ተለቅሞ እየታፈሰ ለውትድርና ተማግዷል፡፡ ወላጆች…አይ ፍርጃ ልጆችን አሳድጎ ለወግ ማዕረግ ማድረስ ቀርቶ ለጦር ሜዳ መሸኘት ሆነ? ብለው ያማርራሉ? በንባብ የዳበረ እውቀት ያላቸው፣ ዩኒቨርስቲ ለመግባት ብቃት ሳያንሳቸው ቤተሰብና ረዳት በማጣት ወደ ውትድርና የገቡ ብዙ ናቸው፡፡ ትዳራቸውን ጥለው ለእናት ሀገራቸው የዘመቱም እንዲሁ…የጎንደሩ ዘሪሁን፣ ሻለቃ ጉርሙ፣ ከድር…እያንዳንዳቸው ሂደቱን ጠብቆ በሚወርደው የታሪኩ ምንጭ ውስጥ ይገባሉ፡፡ ወሬያቸው፣ ህልማቸው ግላዊ አይደለም፣ ሁሉም ንግግሩ ስለ ሀገርና ስለቀጣዩ የሀገሪቱ ዕጣ ፈንታ ነው፡፡ ስለ ባንዲራ ታሪክ፣ ስለ ነፃነትና ጀግኖችም ጭምር ነው፡፡ ልዩነት የላቸውም፣ ልዩነት ቢኖራቸው እንኳን ለሀገር የሚሰጡት ትርጓሜ ላይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰው የልቡን የተናገረበት ጊዜና ቦታ ያ የዘመቻ ጊዜና ማሠልጠኛ ጣቢያ ውስጥ ይመስላል፡፡ ግምታቸውም ሆነ መላምታቸው  ሀገሪቱ በሁለት ጠላቶቿ ተከብባ አጣብቂኝ ውስጥ መሆንዋ ነው፡፡ ዙፋን ላይ የተቀመጠውም ከበረሃ የሚመጣውም ያው ናቸው፡፡ ሀገሪቱ የሚያስፈልጓት ወታደራዊ መንግስት ሳይሆን በህዝብ የተመረጠ ሲቪል መንግስት ነበር ብለው የሚያምኑ የዚያኑ ያህል ይበዛሉ፡፡ የወታደሩ እድል በሰፊው ህዝብ እድል ውስጥ ገብቶ የራሱን ቦታ ይዞ ይታያል፡፡
የደረጀ የህይወት ፍልስፍናውና ነገር አተያዩ ከዳበረ የህይወት ልምዱ ጋር ተጣምሮ ከጦር ሜዳው አስደናቂ ትርኢት ጋር ተዋህዶ ቀርቧል፡፡ ጦርነት ብቻ አይደለም፤ በዚህ ጦርነት የሰፊውን ህዝብ ብሔራዊ ስሜት፣ የደጀኔና የጓደኞቹ ተሳትፎ እንዴት እንደሆነ ያሳያል፡፡ ስሜት ይቀስቅሳል፡፡ ስብከቱ ሀገር ናት፡፡ በሀገር ጉዳይ ቆራጥነቱንም እንዲህ ይገልፃል፤ “…ሀገርህን ውደድ፣ ያለ ሀገር ክብር የለም፤ ያለ ሀገር ሰላምና ዕፎይታ የለም፡፡ በተለይ እኛ ኢትዮጵያውያን ጥቁሮች ብንሆንም ጉልበታችን ለነጭ አልተንበረከከም፡፡ ህሊናችን በባርነት አልጨቀየም፡፡ ስማችን በውርደት አልተጣለም፡፡ የምናያቸው ብዙ የስልጣኔ ምልክቶች፣ በርካታ የጀግንነት ምዕራፎች አሉን፡፡ አሁን በርግጥ ደካማ ነን፡፡ ይሁን እንጂ ይህን የእንጀራ ድህነት የምንለውጥበት ታሪካዊ መሠረት አለን፡፡ የሀገራችንን ደህንነት ማስከበር ከቻልን ሌላው አያቅተንም፤ ይህንን ለማድረግ ደግሞ አደራው የኛው ነው፡፡” (ገፅ 175)
በደመና ሳቆች ውስጥ! ደመና የዋጣቸው ሳቆች በህዋ ላይ ተርከፍክፈዋል፡፡ አንዳች ልብን የሚዘለዝል ስቃይ…በማማሰያ የሚያማስል ሁከት አለ፡፡ የእንባ ቋንጣዎች ከአድማስ ወደ አድማስ የሚወረወሩ፡፡ ከክራቸው የተበተኑ ዥንጉርጉር ዶቃዎች ድምፅ በሰማዩ ይናኛል፡፡ ደረጀም እንደ ቶልስቶይ በደጀኔ በኩል የሕይወቱን ዕጣ ፈንታ ሊወስኑ የሚችሉ ብዙ ውሳኔዎችን ሊያሳልፍ ሲቸገር እናያለን፡፡ ግቡን ለማግኘትና ህልሙን ለመኖር ይባዝናል፡፡ በአንድ በኩል ገጠር ሄዶ ከገበሬው ጋር ማሳለፍ ያስባል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የስነ-ጽሁፍ ጥማቱ እዚያ ለአዕምሮ ስፋት የሚጠቅሙ መጻህፍትና ጋዜጦች ላይገኙ ይችላሉ ይለዋል፡፡ ቀጣይ የትምህርት ዕድልም የለም ሲል ይሞግተዋል፡፡ ሂሳብ አይወድም፣ የእርሻ ትምህርት ማጥናት ደግሞ ይፈልጋል፡፡ በመጨረሻ ወደ ውትድርና በቆራጥነት ተሠማርቶ፣ የስነጽሁፍ ስራውን ሳያቋርጥ በግጥም ውድድር አንደኛ ሆኖ ስሙ ሲጠራ ህልሙም ሲሳካ ከሩሲያው ደራሲ ህይወት ጋር አንድነቱ ስሙም ሆኖ ይገጣጠምልናል፡፡ ደራሲና ሀያሲ ደረጀ በላይነህ ገና በወጉ ባልጠና አራስ የንባብ ፍቅሬ ጀምሮ አውቄው ስራዎቹ በልቤ እየተመላለሱ በነፍሴ ያደጉ ባለ አሻራ የህልሜ ደራሲ ነው፡፡ በቅጡ መድረሴን እርግጠኛ አይደለሁም እንጂ የዘራብኝ ዘር በዝቶ ቡቃያው የተንሰራፋ ነው፡፡ የንባብ ሰፊ አዝመራው በአይነት የተከማቸበት የተንጣለለ ጎተራ ነው ማለት ይቻላል፡፡ የስነ ግጥም፣ አጭር ልቦለድ፣ ማህበራዊ ሂስ…ወዘተ፡፡ ሌሎችም አመርቂና አጥጋቢ ስራዎቹ ለሌላ ሂሳዊ ምልከታ ከሁሉም አቅጣጫ የራሱን ዘርፈ ብዙ እድል ይሰጣል፡፡ ይህም ደረጀን ስራቸው ለትንታኔ ሰፊ ሚና ካላቸው ጥቂት እውቅ የሀገራች ደራሲያን መካከል አንዱ ያደርገዋል፡፡



Read 737 times