Saturday, 03 June 2023 20:15

ድህረ-ዘመናዊነት፤ ማህበረሰባዊ ዕዳ ወይስ ቡራኬ?

Written by  (ዮናስ ታደሰ)
Rate this item
(0 votes)

 እንደ መግቢያ
ድህረ-ዘመናዊነት እንደ መወያያ ርእሰ ጉዳይ ሆኖ በሚቀርብበት የፍልስፍናዊ ውይይት መድረኮች ላይ፣ “ድህረ-ዘመናዊነት ከሰው ልጅ የሐሳብ ታሪክ ሂደት አንፃር ሲታይ እንደ እድገት ነው የሚወሰደው ወይስ እንደ ውድቀት?” የሚል ጥያቄ ሁሌም የጦፈ ክርክር እንዳስነሳ ነው።
“ድህረ-ዘመናዊነትማ ቡራኬ ነው” ብለው ከሚከራከሩት ወገን (በአብዛኞቹ የውይይት መድረኮች ላይ ያስተዋልኩት፣ የሚበዛው የውይይቱ ተሳታፊ ቡራኬ ነው የሚል ነው) የሚነሳ አንድ የመከራከሪያ ሐሳብ ታድያ ግርምትን የሚያጭርብኝ ነው። የመከራከርያ ሐሳቡ ጭብጥ ይዘት ሲጨመቅ እንዲህ የሚል ነው:-
ልክ የሰው ልጅ ግብርና ዘመንን ተሻግሮ የኢንዱስትሪ ዘመን ሲገባ፤ ወይም የኢንዱስትሪ ዘመንን ተሻግሮ የኢንፎርሜሽን ዘመን ሲቀላቀል እድገት ነው እንደምንለው ሁሉ፣ ድህረ-ዘመናዊነትም ዘመናዊነትን ተሻግረን የምንቀላቀለው ዘመን ስለሆነ እንደ እድገት ነው መወሰድ ያለበት።
የዚህ  ዓይነቱ መከራከሪያ ሐሳብ ህፀፅ እንግዲህ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ታሪክና የፍልስፍና ታሪክ አካሄድ አንድ ዓይነት አድርጎ መፈረጁ ነው።
ማለትም ልክ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ታሪክ ላይ በጊዜ ሂደት የታየው ነገር የሐሳብ እድገት ዝግመተ-ለውጥ (በተለይ ያለፉትን ሁለት ወይም ሦስት መቶ ዓመታትን ስንመለከት ፈጣን የሚባል) ስለሆነ እና፤ የዚህን የሳይንስና ቴክኖሎጂ እድገት ተከትሎ የሚመጣው ውጤት ደግሞ ማህበረሰባዊ እድገትና ስልጣኔ ተደርጎ እንደሚወሰደው ሁሉ፤ በፍልስፍና ታሪክ ላይም በጊዜ ሂደት የሚታየው ነገር የሐሳብ እድገት ዝግመተ-ለውጥ መሆን አለበት፤ ከዚህ የተነሳም የሐሳብ ዝግመተ-ለውጡን ተከትለው የሚፈጠሩ ዘመኑን የሚበይኑ ንቅናቄዎችም ማህበረሰባዊ እድገት ተደርገው ነው መወሰድ ያለባቸው የሚል አንድምታ አለው። ይሄ ግን ስለ  ፍልስፍናዊ ንቅናቄዎች (ወይም ስለ ፍልስፍናዊ የዘመን ብያኔዎች) ያለውን የግንዛቤ እጥረት አጉልቶ የሚያሳይ እንጂ ምንም ውሃ የማይቋጥር መከራከርያ መሆኑን በፍልስፍና ታሪክ ውስጥ የግሪክና የሮማ (አንዳንዴ ግሪኮ-ሮማ በመባል የሚታወቀው ዘመን) ስልጣኔዎች ከነበሩበት ዘመን በኋላ ቀጥሎ የመጣውንና ለ 10 ክፍለ ዘመናት የዘለቀውን የጨለማው ዘመን (The Dark Age) የሚባለውን ማስታወስ በቂ ነው።
የዚህ ፅሑፍ ዓላማ ግን ይሄን ስሑት የመከራከርያ ሐሳብ መተቸት ሳይሆን፤ እንደው ለመሆኑ በፍልስፍና ታሪክ ውስጥ የሚታወቁትን የዘመን ብያኔዎች ወይም ደግሞ በየጊዜያቱ ለሚከሰቱ ፍልስፍናዊ ንቅናቄዎች በአወንታዊ (ቡራኬ) ወይም በአሉታዊ (ዕዳ/እርግማን) መንገድ እንዲፈረጁ የሆኑበትን ምክንያት በአጭሩ በመዳሰስ፤ በዚሁ መነፅርም ድህረ-ዘመናዊነትስ የትኛው ምድብ ላይ—ዕዳ/እርግማን ወይስ ቡራኬ— እንደሚመደብ ወይም ሊመደብ እንደሚገባ ለማሳየት ነው።
ስለዚህ የፅሑፉ አካሄድ የሚሆነው በመጀመርያው የፅሑፉ ክፍል (section) ዘመናዊነት ምንድን ነው? ለሚል ጥያቄ አጭር ብያኔ በማስቀመጥ፣ በዚሁ ብያኔ መሰረት ድህረ-ዘመናዊነት ዘመን ላይ ነው ያለነው ሊያስብሉ የሚችሉ መገለጫዎችን ከተለያዩ ኣቅጣጫዎች በተለይም ከሳይንስ፣ ከባህል፣ እና ከአርት አንፃር ማሳያ ሊሆኑ የሚችሉ ክስተቶችን ወይም ኩነቶችን እያጣቀስን እንመለከታለን። በሁለተኛው የፅሑፉ ክፍል ደግሞ ለድህረ-ዘመናዊነት መነሳት ዋና መግፍኤ ምክንያት የሆነውን ነገር ለማንፀር እንዲረዳን፣ አሁንም አጭር የፍልስፍና ታሪካዊ ዳራ በማስቀመጥ፤ በዚሁ የፍልስፍና ታሪክ ማእቀፍ ውስጥ ተለይተው በስፋት የሚታወቁትን  የዘመን ብያኔዎች ወይም ደግሞ ፍልስፍናዊ ንቅናቄዎችን በአዎንታ ወይም በአሉታ የሚወሱበትን ምክንያትም  እንመለከታለን። ከዚህ በመነሳትም በሦስተኛውና  የፅሑፉ መደምደሚያ በሚሆነው ክፍል “ድህረ-ዘመናዊነት ዕዳ ወይስ ቡራኬ?” ለሚለው ጥያቄ ተገቢው መልስ መሆን ያለበትን በማስቀመጥ እንቋጫለን።
1. ድህረ-ዘመናውነት ምንድን ነው? መገለጫዎቹስ?
በመጀመርያ ደረጃ ሊታወቅ የሚገባው ነገር ቢኖር፣ ድህረ-ዘመናዊነት ለየዘመናዊነት (modernity) ንቅናቄ  ግብረ-መልስ ሆኖ፣ በ1970ዎቹ አካባቢ የተነሳ ንቅናቄ እንጂ አንድ ወጥ የሆነ በስርዓት የተዋቀረ ፍልስፍና ወይም ዶክትሪን አይደለም።  ድህረ-ዘመናዊነት ማለት:-
ሰዎችን ሁሉ እኩል በሆነ መንገድ የሚያስማማ ሁለንታዊ እውነት (universal truth) የሌለበት፤ እውነትና ሞራሊቲ  አንፃራዊ የሆኑበት፤ ሁሉም ባህሎችና ሃይማኖቶች ትክክል የሚሆኑበት (“ጎጂ ባሕል” የሚባል ነገር የሌለበት)፤ ሰዎች እውነትን ከገሃዱ ዓለም ጋር አመሳክረው የሚፈልጉበት ሳይሆን፣  
በዲስኩር፣ በቋንቋና በፖለቲካ ላይ ተመርኩዘው የ”እውነትን” ተፈጥሮ የሚረዱበት አዲስ ዓለም ነው። (ፋሲል መርዓዊ፣ የፍልስፍና ትምህርት ቅፅ-፩)
ድህረ-ዘመናውያን “እውነትን አንፃራዊ” ከማድረጋቸው ወይም ደግሞ አሁን አሁን በ”ድህረ-እውነት/post-truth” አቋማቸው “እውነት የሚባል የለም” ከማለታቸው የተነሳ፤ ከባህል፣ ከሞራሊቲ፣ ከፖለቲካ፣ ከቋንቋ ወዘተ ኣንፃር እጅግ የተለያዩና አብዛኛውን ጊዜም እርስ በራሳቸው እየተጣረሱ በሚያቀርቡት ሐሳብ ምክንያት፣ ድህረ-ዘመናዊነትን በተመለከት አንድ ወጥ የሆነ ብያኔ ለማስቀመጥ አስቸጋሪ ቢያስመስለውም፤ ከስነ-እውቀት አኳያ ግን ሁሉንም ኣስተሳስሮ የሚይዝ መሰረተ-ሐሳብ (premise) አለ:-ብዙ ከስረ-መሰረታቸው የሚለያዩ ግን ደግሞ “በእኩልነት ተገቢ” የሚባሉ ዓለምን የምናውቅባቸው መንገዶች አሉ፤ ሳይንሳዊው የእውቀት መንገድም ከነዚህ የእውቀት መንገዶች አንዱ እንጂ ብቸኛው የእውቀት መንገድ አይደለም። (Paul Boghossian, The Fear of Knowledge) ስለ ድህረ-ዘመናዊነት ብያኔ ይሄን ያክል ካልን ይበቃናል። እስቲ አሁን ደግሞ ድህረ-ዘመናዊነት ዘመን ላይ ነን ሊያስብሉ ከሚችሉ መገለጫዎች ውስጥ ጎልተው የሚታዩትን በጥቂቱ እንመልከት።
ይቀጥላል...




Read 903 times