Saturday, 03 June 2023 20:21

ፍርፍር፣ መንደሪን እና ኤልሳ በሐምራዊ ተረኮች

Written by  ታምሩ ከፈለኝ
Rate this item
(1 Vote)

ልጅነቴ ጠረኑ የመንደሪንና ፍርፍር
             ቅልቅል፤ ቀለሙም ሐምራዊ ነበር።
                    (ገጽ 20) መስከንተሪያ
                  
        ሐምራዊ ተረኮች 15 ምእራፎች አሉት። 15 ተረኮችም ብንል ብዙ አንስትም። 1.. 2 .. እየተባሉ የተደረደሩት ምእራፎች ብቻቸውን ሲነበቡም ስሜት ይሰጣሉ። ለዚህም ይመስላል የመጽሐፉ ርእስ ላይ “ተረኮች” የሚል አብዢ ቅጥያ ያለው ቃል የገባው። ሙሉ የመጽሐፉ ቅርፅ እንደ ረጅም ልቦለድ ሆኖ የሚገኘው ግን ሁሉም ሲነበቡ ነው። እነዚህ ምእራፎች በብዙ ገመድ ተሳስረው የቆሙ ሲሆን ዋናዋ አስተሳሳሪ ገመድ ደግሞ ሳባ ትባላለች።
ሳባ ከዩኒቨርሲቲ ከወጣች በኋላ ወደ ኋላዋ ተመልሳ ልጅነቷን ታስባለች። በትዝታዋ በልጅነቷ የምትተክዝ፣ የምትቆዝም ዓይነት ወጣት ናት። ለዚህ መሰለኝ ያንን ያፍላነት ዕድሜዋን በአባቷ ‘እስኪ ወጣ በይ’ እስክትባል ድረስ ጋቢ ለብሳ በቤቷ የተቀመጠችው። (ገጽ 12)
ሳባ ልጅነቷን ስታስብ ሁለት ነገር እንደሚመጣባት ትናገራለች። ፍርፍርና መንደሪን። ፍርፍርና መንደሪን ደግሞ በመጽሐፉ ውስጥ በልዩ ልዩ መልክ ሲከሰቱ እናገኛቸዋለን።
~ ፍርፍር እንደ ሰላም ምንጭ
ሳባ እናትና ጎረቤት ተቀባብለው የሚያሸቱት እጅ አላት። እናቷ ሎሚ ለገበያ ወጣ ባለች ቁጥር ወደ ጎረቤት ትወስዳትና እዛ እንድትቆይ ታደርጋለች። ጎረቤቷ ወይዘሮ አመዘነች፣ የሳባ እናት ሎሚ ቤቴ ስትገባ ሎሚ ሎሚ ትለኛለች ይላሉ። እናቷን ያልደፈሩት አመዘነች ከእናቷ ጠረን የተጋባባትን ሳባን ይዘው እጇን ያሸታሉ። በምሳጤ ያሸተቱት የሳባ እጅ በትዝታ ወደ ኋላቸው ይወስዳቸውና የቀድሞ ሀገሬ የሚሉት ኢሊባቡርን ያስታውሳቸዋል። (ገጽ 25)
የሳባን አልቃሻነት ችለው በቤታቸው የሚያቆዩዋት አመዘነች፣ ቅቤ ተቀብቶ የደረቀ እንጀራ ድርቆሽ በቅቤና ቋንጣ አብዶ የተሰራ ፍርፍር ይሰጧታል። ሳባ የዚህ ፍርፍር ልክፍተኛ ትሆንና ወደ ቤቷ ስትመለስም እናቷን ያንን መሳይ ፍርፍር ውለጂ ብላ ትበቅታታለች። እናት በልጇ ብቀታ ሰላሟን ታጣለች። የተባለውን ፍርፍርም መሥራት ያቅታታል። ሙከራዋ ሁሉ ይከሽፋል።
(ሎሚ የልጇን የሰርክ ጥያቄ “ትበቅተኛለች” ብላ ነው የምትገልፀው። መበቀት (ብቀታ) ደግሞ ከጭቅጭቅም ከፍ ያለ መፈናፈኛ የማሳጣት ደረጃን ይገልፃል። ለዚህም ሎሚ ይህንን ቃል የተጠቀመችው ጭቅጭቁ ሰላሟ እንደነሳት ለመግለፅ ነው።)
አንድ ቀን ግን ሳባ ጥፍር ውስጥ የተደበቀ ፍርፍር ታይና የልጇን እጅ ታሸታለች። (ገጽ 28) ጣእሙን አሽትታ ስታገኘው ትሰራዋለች።
ሎሚ የልጇን እጅ አሽትታ በሰራችው ፍርፍር ከልጇ ብቀታ ትድናለች። እዚህ ጋር ነው ፍርፍር የሰላም ምንጭ ሆኖ የሚከሰተው።

አመዘነች በሳባ እጅ ተሳፍራ የቀድሞ ሀገሬ ወደምትለው ኢሊባቡር ትዝታዋ ትሄዳለች። አመዘነች ከናፍቋቷ ዳነች ማለት እንችል ይሆን?
 ~ ፍርፍር እንደ ድህነት ምንጭ
ሎሚን ከልጅ ብቀታ አድኖ የሰላም ምንጭ የሆነው፤ አመዘነችን ከናፍቆት ያፋታው ፍርፍር ታምሩ በዚህ አያልቅም።
ሎሚ የአመዘነችን ፍርፍር ጣእም ከልጇ እጅ ላይ አሽትታ ስትወስደው አመዘነች የፍርፍሯ ጣእም ይጠፋባታል። ብዙ ቅቤና ቋንጣ ብትፈጅም የፍርፍሯን ጣእም መመለስ ግን አልሆነላትም ነበር።
አመዘነች ታማ ልትሞት ስታጣጥር ሎሚ ፍርፍር ሰርታ ስታቀምሳት ትድናለች። ከላይ የሰላም ምንጭ ሆነ ያልነው ፍርፍር እዚህ ጋር የድህነት ምንጭ (source of healing) ሆኖ ይከሰታል።
ኤልሳ ፍርፍርን የሰላምም የድህነትም መንጭ አድርጋ ስታቀርበው ታጓጓለች እንጂ እንዴት ሆነ የሚል ጥያቄ አይነሳባትም። ጎበዝ ተራኪ ስለመሆኗ ምስክር አንድ።
ሎሚ በሞት አፋፍ ላይ ያለችውን አመዘነች ፍርፍር አቅምሳት፣ ስትድንና ስትናገር ፍርፍር የያዘውን ሳህን ትለቀዋለች። ሳህኑ መሬት ከመድረሱ በፊት አመዘነች ትይዘውና ለከፈን የተዘጋጀው አቡጀዴ ላይ ታስቀምጠዋለች።
በዚህን ጊዜ የፍርፍሩ ቅባት አቡጄዴው ላይ የሰራው ምስል አመዘነች ጭንቅላት ውስጥ ምንነቱ በውል ሳይገለፅ ሲያዳክራት ይቆያል።
ከሁለት ዓመት በኋላ በስቅለት ቀን ክርስቶስ ሰምራ ቤተክርስቲያን ውስጥ አመዘነች ለስግደት ሄዳ ሰዐሊው... የሳለውን የክርስቶስን ስዕል ታያለች። በዚህ ጊዜ ሁለት ዓመት ውሉ ሳይገለፅላት የቆየው አቡዠዴው ላይ የተሳለው ስዕል ይከሰትላታል። ውስጧ የነበረው ስዕል የክርስቶስ ሾህ አክሊል ነበር። (ገጽ 30)
እዚህ ጋር ፍርፍር በነገረ ስጋዌ በኩል የድህነት ምንጭ ሆኖ ይመጣል። (የክርስቶስ አክሊል ከክርስቶስ ሰው መሆንና ስቃይ ጋር ይገናኛል። የክርስቶስ ስቃይ ደግሞ ለሰው ልጅ ድህነት መሆኑን ልብ ይሏል)። በጣም የሚያስገርመው ግን ወደ ዘላለማዊ ድህነትነት የተቀየረው በከፈን በኩል መሆኑ ነው። ከፈን የድህነት ሳይሆን የሞት፣ የመሻር ሳይኖህ የዝለት ምልክት ነው።
ለአመዘነች ከፈን ተጋጅቶ የነበረው አቡጀዴ  አመዘነች ስትድን የፍርፍር ጠረኑን አንደያዘ ልብስ ሰፊው ገብረ ሃና ጋር ይደርሳል። ገብረ ሃና ሊሸጠው ከሰቀለበት ወልዱ ለተባለ ሟች መገነዣነት ይሸጥና ይሄዳል። ወልዱ ተከፍኖ ሊቀበር እረግዶ ተይዞ ከሳጥኑ ውስጥ ይነሳል። ድህነቱ ለወልዱም ይደርሳል።
ይህን ሁሉ የታዘበው ልብስ ሰፊው ገብረሃናም
“ከአሳዳሪዋ ምህረት የተረፈ በጨርቁ ይዛ የመጣችው ፈውስ፤ ለወልዱም ተርፎ ሞትን ድል ሲነሳ አይቻለሁ” ይላል። (አፅህኖት ከኔ) (ገጽ 62)
ኤልሳ ሞተ የተባለውን ወልዱ ሲገነዝ ሲለቀስ ሞትን (??) ድል አድርጎ ሲነሳ ስትተርክልን፣ እንዴት ሆነ ብለን አንጠረጥራትም። ይልቁንም ጥሩ ተራኪነቷ ወደ ጉዳዩ ይበልጥ ያቀርበንና ስንጨነቅ ስንገረም እንገኝ ይሆናል እንጂ... እንሆ ስለ ጥሩ ተራኪነቷ ሌላ ምስክር።
ከወልዱ ድህነት በኋላ ነው እንግዲህ፣ ተስፋዬ የተባለ መምህር (የሳባ አባት) ገዝቶ የክርስቶስን ስእል የሳለበት።
~ መንደሪን
ሌላኛው የሳባ የልጅነት ጠረን መንደሪን ነው። መንደሪንም በሐምራዊ ተረኮች ውስጥ በልዩ ልዩ መልክ ተስሏል።
መንደሪን እንደ ልጅ
“መንደሪን የትርንጎ ልጅ ይመስለኛል” ትላለች ሳባ። ቆይቶ ምክንያቱን በምንጠቅሰው መንገድ፤ ትርንጎ መንደሪን ከጓሮዋ ሲበቅል አንዲህ ትላለች
“አንዱን ፍሬ ቀጥፌ ወደ አፍንጫዬ አስጠጋሁት። እኔን እኔን ይላል።  በሁለት እጆቼ አንከብክቤ ይዤ ደረቴ ላይ እቅፍ አድርጌው ተንሰቅስቄ አለቀስኩ። እንደ ትኩስ አራስ፤ እንኳን ማርያም፣ ማረችሽ ብላ አዋላጇ የምታቅፈውን ልጅ እንዳቀበለቻት”። (ገጽ 49) (አፅእኖት የኔ)
መንደሪኑ የሰው ቅርፅ ይዞ የተከሰተው በትርንጎ ዘንድ ብቻ አይደለም። እነሳባም መንደሪን የትርንጎ ልጅ እንደሆነ ያስባሉ። (ገጽ 50)
“ትርንጎ መንደሪኖቹን ከየት እንደምታመጣቸው ታውቂያለሽ?”
“እንጃ አላውቅም፤ ከየት ነው?”
“ልጆቿ ናቸው፤ ወልዳቸው ነው።” (ገጽ 54)
በዚህም መንደሪን ከተክልነት ዘሎ የሕያውነት ቅርፅ ይዞ ተከስቷል።
መንደሪን እንደ ትንግርት መከሰቻና መከሰቻ (“ከ” ላልታ)
ትርንጎ አይነ ስውር ናት። አይንዋን ያጣችው ደግሞ ከድንጋ ጋር ተቆጥሮ ለቆቅ በተወነጨፈ መንደሪን ተመታ ነው። (ገጽ 43) ብርሃኗን ስታጣ አስቀድመው እጇን ስጡን እያሉ ሲመላለሱ የነበሩ “ልጅህን ለልጄ” ባዮች ሁሉ እግራቸው ያጥራል። አባቷ በብስጭት ከአልጋ ይውላሉ። አይኗን ያጠፋው መንደሪን የሰውነቷን ጠረን ይቀይረውና መንደሪን መንደሪን ያስብላታል።
“የመንደሪን ጠረን በሄድኩበት፣ በደረስኩበት ሁሉ እንደ ጥላ የሚከተለኝ፤ በዙሪያዬ እንደ ጉም የሚያረብብ ሆነ።” (ገጽ 44)
ይህንን ያየ ካሳ የሚባል አልፎ ሂያጅ አግብቶ ወደ ሌላ ስፍራ ይወስዳታል። አርግዛ ሳለች አፈር አምጣ ትለውና አፈሩን ሊያመጣ ሲሄድ ወድቆ ይሞታል። በዚህ ብስጭት ተሰዳ ጫጫ የተባለች ከተማ ትገባለች። (ጫጫ የመጽሐፉ ዋና - የት - ነው)
ጫጫ ከአገሬው ተጎራብታ ስትኖር የባሏ ናፍቆት እያገረሸባት፣ ስታለቅስ አይኗን ያጠፋችው መንደሪን በእንባ ተገፍታ ትወጣለች። (ገጽ 47)
ከዚህ በኋላ መንደሪን መንደሪን መሽተቷ ሳይቀር አይቀርም። ቆይቶ ያንን ጠረን ምታገኘው ከአይኗ በእንባ የተገፋው መንደሪን ከጓሮዋ መብቀል ሲጀምር ነው። መንደሪኑም ደርሶ መንደሪን ይበቅላል ተብሎ በማይታሰብበት የአየር ንብረትና መልክአ ምድር ላይ በቅሎ ለገበያ ይቀርባል። (ገጽ 49)
 ሲጠቃለል
ኤልሳ ይሄንን ሁሉ ስትተርክልን ቃላት ደንቀፍ አያደርጓትም። ታሪኮችን የማውዛትና ተቀባይ የማድረግ አቅሟም ከፍ የለ ነው። በታሪኩ መሀል አልፎ አልፎ ያለ አግባብ ከረዘሙ ውስን ተረኮች ውጪ የጎረበጠኝ ነገር የለም።
በመጽሐፉ ውስጥ በምሳሌነት ያስቀመጠቻቸው በፍካሬ የሚደረስባቸው ብዙ ጉዳዮች ያሉ ይመስለኛልና የዘርፉ ተመራማሪዎች እዩት።
ማፈትለኪያ
እንደ ጥቆማ Nostalgic literatureን Symbolismን ለመጽሐፉ እንደ ማያ እናደርጋለን ያለ ሰው ብዙ የሚያገኝበት ይመስለኛል።

Read 685 times