Saturday, 17 June 2023 00:00

ኢኮግሪን የተፈጥሮ ፈሳሽ ማዳበሪያ ማምረቻ ድርጅት ለምርቱ ተጠቃሚዎች ዕውቅና ሰጠ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

በአጋርነት ኢንቨስት ማድረግ ለሚፈልጉ ጥሪ አቅርቧል “በረከት ገበሬዋን” የብራንድ አምባሳደር አድርጎ ሾሟል


       ኢኮግሪን የተፈጥሮ ፈሳሽ ማዳበሪያ ማምረቻ ኃ.የተ.የግ.ማህበር፤ ከትላንት በስቲያ ሐሙስ ምሽት ለምርቱ ተጠቃሚዎች ዕውቅና ሰጠ፡፡
ድርጅቱ፤ ቦሌ ከሚሊኒየም አዳራሽ ፊት ለፊት ሉባባ ህንፃ 5ኛ ፎቅ ላይ ያስገነባውን አዲሱን ዋና መ/ቤቱን ባስመረቀበት በዚህ ምሽት፣ “በረከት ገበሬዋን” የብራንድ አምባሳደር አድርጎ ሾሟል፡፡
ላለፉት አስር አመታት የግብርናውን ዘርፍ ምርታማ ለማድረግ በትጋት እየሰራ እንደሚገኝ የተገለፀው ድርጀቱ፤ የተፈጥሮ ፈሳሽ ማዳበሪያ በማምረት ብቸኛ የፈጠራ መብት ማግኘቱ ታውቋል፡፡
ኢኮግሪን የተፈጥሮ ፈሳሽ ማዳበሪያ ማምረቻ ድርጅት፣ ከኬሚካል ነፃ የሆነ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለገበሬው በተመጣጣኝ ዋጋ ከማድረሱም በተጨማሪ አገሪቱ ለማዳበሪያ የምታወጣውን የውጭ ምንዛሬ በመቀነስ ለኢኮኖሚው ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ተገልጿል፡፡
የኢኮግሪን የተፈጥሮ ፈሳሽ ማዳበሪያ ማምረቻ ድርጅት መስራችና ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ከበደ ላቀው በምሽቱ ባደረጉት ንግግር፤ ከ16 ዓመት በላይ ከጥንሰሳው ጀምሮ ሃሳቡን መሬት ለማውረድ ሰፊ የምርምር ስራ ሲሰራ መቆየቱን ጠቁመው፤ በአሁኑ ሰዓት ምርቱን ከአገርም አልፎ ለአፍሪካ ኤክስፖርት የማድረግ ራዕይ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
ምርቱ በየክልሉ እየተዋወቀና ሰፊ ተቀባይነት እያገኘ መምጣቱን የገለፁት ዋና ስራ አስፈፃሚው፤ “ይህን የተፈጥሮ ፈሳሽ ማዳበሪያ በማምረታችን በአገሪቱ ያለውን የማዳበሪያ እጥረት እንቀርፋለን፤ የውጭ ምንዛሬ እናድናለን” ብለዋል፡፡
የክልል ግብርና ቢሮዎችና የህብረት ስራ ማህበራት ተወካዮች ኢኮግሪን የሚያመርተው የተፈጥሮ ፈሳሽ ማዳበሪያ አርሶ አደሩን ምርታማና ውጤታማ አድርገውታል ብለዋል፡፡
የቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ስራ አመራርን ወክለው በምሽቱ የተገኙት አቶ አህመድ ሸምስ ባደረጉት ንግግር፤ “ቡናችንን ከሌሎች አገራት ለየት የሚደርገው ኦርጋኒክ በመሆኑ ነው፡፡ በዚህ የተነሳ ምርታማነቱ ከሌላው አገር አንፃር አነስተኛ ነው፡፡ የምርታማነቱ ማነስ የመጣው ኬሚካል ማዳበሪያ ስለማንጠቀም ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ኢኮግሪን መፍትሄ ይዞልን መጥቷል” ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ እርሻ ከጀመረች 10 ዓመት እንደሆናት የተናገረችው “በረከት ገበሬዋ” በሚል ስያሜዋ የበለጠ የምትታወቀው በረከት  ወርቁ፣ ድርጅቱንና ባለቤቱን ከማወቋ በፊት ለረዥም ጊዜ ይህን ኦርጋኒክ ፈሳሽ ማዳበሪያ ስትጠቀምበት መቆየቷንና፤ ሌሎች ገበሬዎችም እንዲጠቀሙበት ማስተዋወቋን ገልፃለች፡፡
በኢኮግሪን የተፈጥሮ ፈሳሽ ማዳበሪያ በመጠቀሜ ምርታማና ውጤታማ ሆኛለሁ የምትለው “በረከት ገበሬዋ”፤ “እንደ አንድ አገሯን የምትወድ ኢትዮጵያዊና እንደ አንድ ገበሬ ከኬሚካል ነፃ የሆነውን ኢኮግሪን በመጠቀሜ ኩራት ይሰማኛል” ብላለች፡፡
በኬሚካል ማዳበሪያ የተነሳ ብዙዎች በከፋ በሽታ እየተጠቁ መሆኑን የምትናገረው “በረከት ገበሬዋ”፤ “እባካችሁ ጤናማ ምርት እናምርት” ስትል ጥሪዋን አቅርባለች-ኢኮግሪን በዚህ ረገድ እያበረከተ ያለውን በጎ አስተዋፅኦ በማድነቅ፡፡ኢኮግሪን በምሽቱ ምርቱን ለሚጠቀሙ ሞዴል አርሶ አደሮች፣ የህብረት ስራ ማህበራት፣ የክልል ግብርና ቢሮዎች፣ የክልል ህብረት ስራ ማስፋፊያ ኤጀንሲዎችና ኮሜርሻል ፋርመሮች የእውቅና ምስክር ወረቀት አበርክቷል፡፡
ኢኮግሪንን ለማስፋፋት በሚደረገው እንቅስቃሴ ላይ ፍላጎት ያላቸው በአጋርነት ኢንቨስት ያደርጉ ዘንድም በምሽቱ ተጋብዘዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት አምና ማዳበሪያ ከውጭ ለማስገባት የመርከብና ሌሎች የአስተዳደር ወጪዎች ሳይጨመሩ ከ50 ቢሊዮን ብር በላይ ማውጣቱ  ታውቋል፡፡


Read 985 times