Saturday, 17 June 2023 00:00

ሐይማኖትንና ፖለቲካን፣… ቤተ እምነትንና ቤተ መንግስትን…የሚያቀላቅል አደጋ አለብን

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

የአደጋ እጥረት የለብንም። ግን እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ አይደለም። በተለይ ደግሞ፣ ፖለቲካንና ሃይማኖትን የሚያቀላቅል የጥፋት መንገድ እየተባባሰ መጥቷል- ቁጥር 2 የአገራችን አደጋ ነው። ለመፍትሄ እንዲረዳን ልካቸውንና ድንበራቸውን ለማስመር ብሞክር ይሻላል።
በአንድ በኩል ሲታይ፣ ፖለቲካና መንግሥት፣… ከሰው ክብር በታች ናቸው። ከፖለቲካ በፊት የሰው ሕይወት ይቀድማል። የሰው ሕይወት፣… አየር መተንፈሱ ወይም የደም ዝውውሩ ብቻ አይደለም። አካሉን፣ አእምሮውንና መንፈሱን ሁሉ ያጠቃልላል። እነዚህን የሚገዛ ሳይሆን የሚያገለግል መሆን አለበት - ፖለቲካና መንግስት።
የሰው ኑሮ፣ አላማውና ተግባሩ፣… እውቀቱ፣ ሃሳቡና ንግግሩ፣… የግል ማንነቱ፣ የእኔነት ክብሩ፣ የሕይወት ትርጉሙ፣… ትምህርቱ፣ ሙያውና ሃይማኖቱም ጭምር፣… በአጠቃላይ፣… የሰው ሕይወት፣ ከፖለቲካና ከመንግስት ይቀድማል።
የመቅደም ጉዳይ ብቻ አይደለም። የፖለቲካና የመንግስት ክብራቸው፣… ለሰው ሕይወት በሚኖራቸው አገልግሎትና በሚያስገኙት ፋይዳ ልክ ነው።
“አትወቁ፣ አታስቡ፣ አትናገሩ” ብሎ የሚከለክል የፖለቲካ ሥርዓት ቢኖር አስቡት። ተነፈስክ፣ ተነቃነቅክ ብሎ የሚቆጣና የሚቀጣ መንግስት ቢመጣስ?… የምትጎርሱትን እንጀራና ዳቦ ልቆጣጠር፤ ጓዳችሁንና ጎተራችሁን፣ ኪሳችሁንና ቤታችሁን ልበርብር የሚል ፖለቲከኛ ይታያችሁ። ሃብትና ንብረት ለመውረስ በየእለቱ ህጎችን ሲያውጅ፣ ቢሮዎችን ሲያዋቅር አስቡት። እንዲህ አይነት ፖለቲካ፣ የራሱን ሥረ መሠረት እየናደ፣ የራሱን ክብር ያዋርዳል።
የሰውን ነጻነት፣ የሰውን ንብረትና ሕይወት ከመጠበቅ ይልቅ፣ ሰዎች የመንግስት አገልጋይ ለማድረግ የተቃኘ ፖለቲካ፣ “ተፈላጊነቱ” ምኑ ላይ ነው? ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ ይባል የለ! ለሰው ካላገለገለ፣… እርባና አይኖረውም። ጭራሽ ፀረ ሕይወት ይሆናል።
የሰዎችን የሃሳብና የሃይማኖት ነፃነት የሚለጉም የሚያፍን መንግስት፣… የሰውን ተፈጥሯዊ አእምሮ አምክኖ የራሱን ፋይዳ መና የሚያስቀር፣ የራሱን ክብር የሚያዋርድ ነው። “ኑሮ ለማሻሻል አታቅዱ፤ የሕይወት አላማ አታስቡ፣ ንብረት አታፍሩ” ብሎ መከልከል፣ ማደናቀፍ፣.. የሽፍቶች ስርዓት አልበኝነት ወይም የወንጀለኞች ጥቃት እንጂ፣ ከትክክለኛ የመንግስትና የፖለቲካ አገልግሎት ጋር አይገጥምም። ይጋጫል እንጂ።
ሰዎች አእምሯቸውንና አካላቸውን ተጠቅመው የመስራት፣ ኑሯቸውን በየራሳቸው ጥረት የማሻሻል፣ ንብረት አፍርተው የመገበያየትና የመረዳዳት አቅማቸው ነው - የሕይወት አለኝታቸው። ይህን ማክበርና ማስከበር፣ ከጥቃት መጠበቅና ጥፋተኛን መቅጣት ነው - ትክክለኛው የፖለቲካ ፋይዳ፣ ተገቢው የመንግስት አገልግሎት።
የሰው ተፈጥሮ በእለት ተእለት ሃሳብና በቀን ተቀን ተግባር ላይ ብቻ የተመሠረተ አይደለም። ዘመን በማይሽራቸው እውነቶችና እውቀቶች፣ ሁሉን በሚያቅፉ የሥነ ምግባርና የፍትሕ መርሆችም ጭምር እንጂ። ሰው በተፈጥሮው መንፈሳዊ ነው፡፡ ሰዎችን እንደየብቃታቸውና እንደየተግባራቸው እየዳኘ፣ የልህቀት አርአያዎችን ከልብ የሚያደንቅ፣ ጉድለትን የሚያሟላ፣ መጥፎነትን የሚያርቅ ቀና መንፈስን ይሻል። በዚህ መንፈሳዊ አኗኗር እየታነፀ ጭምር የሚበለጽግ ነው - የሰው ተፈጥሮ።
መንግስትና ፖለቲካ ከነዚህ ሁሉ በታች ናቸው። በአጭሩ የሰው ሕልውናን በመገንዘብ፣ የሰው ሕይወትን በማክበር ላይ የተመሰረተ ነው - የፖለቲካና የመንግስት አስፈላጊነት። ሥረ-መሠረታቸውን ለማጥፋት የተቃኙና የተነጣጠሩ ከሆኑ፣ ከእውነታና ከሕይወት ጋር ይጣላሉ። ፀረ-እውነት፣ ፀረ-ሕይወት ይሆናሉ።
ከዚህ አንጻር፣ መንግስትና ፖለቲካ፣… ከሳይንስና ከሃይማኖት፣ ከእርሻና ከፋብሪካ፣ ከኪነጥበብና ከክብረ በዓል በታች ናቸው።
የሰው ንግግርና የሰው ተግባር፣… አንዱ ሰው የሌላውን ሳያጠቃ፣ በሰላምና በነፃነት፣ በቤተሰብና በግል፣ በማኅበርና በየራሱ ሕይወቱን እንዲመራ፣… ታማኝ የጥበቃ ሰራተኛ መሆን ነው - የመንግስት ትክክለኛ ሥራ።
መንግስት የጥበቃ ስራውን ቅንጣት ሳይጨምርና ሳይቀንስ በአግባቡ እንዲያከናውን ትክክለኛ የጥበቃ አጥሮችን የተገነዘበ ውጤታማ አሰራርን የሚፈጥር ነው - ትክክለኛ ፖለቲካ።
መንግስት፣ ከጥበቃ ስራው እንዳይዘናጋና ወንጀለኞች አጥር እንዳይጥሱ፣…
ወይም ራሱ መንግስት አጥር እንዳይጥስና አለቦታው እንዳይገባ፣ በሰዎች ሕይወትና ንብረት ላይ አዛዥ አናዛዥ ለመሆን እንዳይቃጣ፣…
የመንግስትን ስልጣን ከነገደቡ የማበጀት ጥበብ ነው - ትክክለኛ ፖለቲካ።
በአጭሩ፣ ፖለቲካና መንግስት፣ ከሰው ሕይወትና ኑሮ በታች ናቸው - አገልጋዮች።
በሌላ በኩል ደግሞ፣ ማንኛውም ሰው፣ ማንኛውም የሰው ንግግርና ተግባር፣ ሳይንስና ሃይማኖት፣ እርሻና ፋብሪካ፣ ኪነጥበብና ክብረ በዓል ሁሉ፣… ከሕግ በታች ናቸው ማለት ይቻላል።ማንኛውም ሰው… አስተማሪም ሆነ ተማሪ፣ ባለ ፋብሪካም ሆነ የቀን ሰራተኛ፣ የሃይማኖት ሰባኪም ሆነ ሳይንቲስት፣…. ሕግን ማክበር ይኖርበታል። ሰዎች ህግ የሚዳኛቸው ሊሆኑ ይገባል።
እንዲህ ሲባል ግን፣ ከመንግስት በታች ናቸው ማለት አይደለም። የመንግስት አካላትና ባለስልጣናትም፣… ሁሉም ህግ አክባሪ መሆን አለባቸው። እንዲያውም የመንግስት ባለስልጣናት   “ለሕግ ተገዢ” መሆን ይኖርባቸዋል። ሕግን ከማክበር በተጨማሪ ሕግን የማስከበር ሃላፊነት አለባቸውና (የጥበቃ ሰራተኞች ናቸውና)።
ማንኛውም ተቋም፣… ዩኒቨርስቲም ሆነ የምርምር ማእከል፣ የሃይማኖትም ሆነ የኪነጥበብ ተቋም፣ ኢንዱስትሪም ሆነ ገበያ፣… ሕግን ማክበር ይገባቸዋል። ነገር ግን፣ የፓርቲም ሆነ የመንግስት ድርጅት፣ ሁሉም የፖለቲካ ተቋማት፣ ሕግ የሚገዛቸው ህግ አክባሪ መሆን ይኖርባቸዋል። በተለይ የመንግስት ተቋማትና ባለስልጣናት፣ ሕግ የማክበር  ብቻ ሳይሆን የማስከበር ግዴታና ሃላፊነትም አለባቸው (የጥበቃ ስራ ነውና አገልግሎታቸው)።
“እንዲህ መሆን አለባቸው”፣… “እንዲያ መሆን የለባቸውም”፣… “እንዲህ ማድረግ ይገባቸዋል”፤ “እንዲያ ማድረግ አይገባቸውም” ስንል፤… ትክክለኛ ድንበራቸውንና ልካቸውን መግለፃችን ነው። የድንበራቸውን መስመር፣ የልካቸውን ሚዛን ይዘን፣… አገራችን የገባችበትን የአደጋ ዓይነትና መጠን መመልከት እንችላለን።
በየጊዜው፣ በሃይማኖት ሰበብ እንዳሰኛቸው ሕጎችን ለመጣስ፣ ወንጀል ለመፈጸምና ፖለቲካውን ለመዘወር የሚሞክሩ አጥፊዎችን አይተናል።
ሁሌም አደጋ ናቸው።
ዛሬ ዛሬ ደግሞ ሃይማኖትን የመንግስት አገልጋይ የፖለቲካ ተገዢ የማድረግ ጥፋቶች እየገነኑ መጥተዋል። እነዚህም አደገኛ ናቸው። መንግስት አደገኛ አጥፊዎን ለመከላከል ይረዳ፡፡ መንግስት ራሱ አደገኛ አጥፊ ሲሆንስ ማን ይመልሰዋል? አደጋው የከፋ ይሆናል፡፡



Read 691 times