Saturday, 17 June 2023 00:00

ቅጥልጥል በማለዳ ድባብ

Written by  ድረስ ጋሹ
Rate this item
(7 votes)

 ቅጥልጥል በማለዳ ድባብ
                      
      «ዓይን ጆሮ ምላስ ለኑሮ ሳያንሰኝ
ምን በድዬው ጌታ አፍንጫ ለገሰኝ?»
እላለኹ ዘወትር።
ማየት ማመን ነው ብዬ አይቼ ፤ያየሁትን ሳላምነው ቀርቼ፣ ከአንዴም ሁለቴ በአየሁት ነገር ስቼ _አለሁ። ነገር በምላሴ እየቆላሁ፣ከራሴ አንደበት በወጣው ከራሴ ጋራ እየተጣላሁ፣ሽምግልና አይልኩበት ችግር ገጥሞኝ ...አሞኝ...አሞኝ ...ነቃሁ _ከአፍንጫ ጋር ፤ያውም ሽታን ጠረንን አውቅ ዘንድ።
  «የክንፌ ˙ርጋፊ
  አንድ የላባ ነዶ
  የአካሌ ቅራፊ
  የቀረ ተጎርዶ
 ተጠርጎ ሲወሰድ ፡ በጥሞና እያየሁ
ይኼው ቁጭ ብያለሁ። »
ይፈጥናል ኹሉም። ነገሮች ለዓይኔ ውልብታ መሆን ከጀመሩ ሰነበቱ። ተሰርተው ያየኋቸው ቤቶች ተሰልበው ፣ያልነበሩትም ወደ መኖር መጥተው አያለሁ። አካሌ መሬት አያያዙ የሚለቅ አይመስልም ።የያዙት እንደሚያመልጥ ፤የለኮሱት ሻማ እንደሚቀልጥ መገመት ግን አይከብድም። አይመስልም እንጅ ለዓይን ...አይመስልም እንጅ ለሰሚ የሚመጣው ኹሉ ለመኼድ ነው። የሚኼደው ኹሉስ ይመጣ?
         «አባዬ ብርኅን
         አባ የምሥራቅ በር
         ገመና ሸሻጊ ፥እንደ ካባ ገበር
 አባቴ ባትሆን ፥ምን ይውጠኝ ነበር?»
አንተን ሳስብህ ዓለምን ረሳለሁ _የኑሮን ጠረን ሳይቀር። ተቀምጬ ..ጊዜ የጎሪጥ እያየኝ ሲከንፍ ..«አይዞህ»የሚል ፅኑ ቃልህ አጠገቤ ቁጭ ብሎ ያጫውተኛል። ጨዋታችን መኼድ መምጣት ይበዛዋል። ውልብታ..ውልብታ ...ውልብታ!። አባ፤«ሲኼድ ጓያ ጭኖ ሲመለስ አተር»ን መቼ ልትተርትልኝ አሰብክ? ልጄ እያልክ  ራሴን የምታሻሸው መቼ ነው? ሰፋፊ የኮትህ ኪሶች፣ ረጃጅም የእግርህ ካልሲዎችህ ሳይቀሩ ከዓይኔ አልጠፉም። የጋረደን ደመና ተገፎ፣መለያየት በኪነ-ጥበቡ አልፎ ፣ዳግም ከጉያህ የምደበቅ መቼ ነው? በሕይወት መኖርህ ብቻ እያኖረኝ እንደሆነ አስረጂ ደብዳቤ ልላክ? ይኸው ትካዜ አብዝቼ  የተቀመጥኩበት መሬት ጎደጎደ። ስፈጠር ከመሬት ፣ስኖር በመሬት ፣ስሞት ለመሬት ..ሰው ነኝና!!
               «እኔ እወድሻለሁ
               እንደ መቅደስ ዕጣን
              እንደ አፍለኛ ሥልጣን
   እኔ ያንቺ ቡዳ ፤ያንቺ ልዝብ ሰይጣን »
አመጣጤ ለአንቺ እንደሆነ ገባኝ _ሕይወት። ልኖርሽ። ምናልባት ትኖሪኝ ጀመር? ወይስ እየተኗኗርን ነው? በአንቺና በእኔ መሐል ምን አለ?..ጥገኛነት..ተመጋጋቢነት፣ወይስ ኮመንሳሊዝም?_ብቻ እወድሻለሁ። ውልብታውን ቢለምዱት ይለመዳል። ወፍጮ ቤት ሥር የሚኖር ሰው የወፍጮውን ዳና እንደሚለምደው ፣ ነፍጠኛም ከጥይት ድምጽ ደስታ እንደሚያዋልደው_እንደዛ። ያጎደጎድኩትን መሬት ዞሬ አይ ዘንድ አንገት አለኝ።ደስታ ከመርካቶ እንደማይገዛ በገባኝ ጊዜ ፣መውደድም ከሰማይ ተጠቅልሎ እንደማይላክ ባወቅኩ ጊዜ ፣ ራሴው...በራሴው...ለራሴው ይሆነውን አደረግኩ። «ልብ አይገታም በሩ ፥ ልብ አይገታም መስኮት
 በዝግ ቤትሽ ገባሁ ፥ልክ እንደመለኮት»
አመጣጤ ሌባን መሰለ ፣ዳናዬ ድምጹ ሰለለ። እንደ ዝሆን ጆሮ ከ10 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በትንሽ ፍሪኴንሲ ይሰማል ጆሮሽ። የዕድገት ሰንሰለቶችን ቀጣጥለሽ፣አንድ ኗሪ አገኘሁ ብለሽ ፣ሽር ጉድ...ሰንዳ ሰንዳ...ሲያምርብሽ! ሰቨን ፖይንት ክራይሲስ ያዋቀረሽ፣ በሃምሌት መቋጫ ያበተሽ፣በካሊጉላ ከራስ በላይ ንፋስ ያሟሸሽ ለምን ይሆን? የሚጥም ኀዘን አለሽ ፣ወይንን የሆነ። አድሮ ሌላ _ውብ ማዕዛ። ኀዘን ሲለመድ ደስታን ይመስላል። ለቅሶ የለመደ ለሞተው ሁሉ ሲያደገድግ ይውላል። ለቅሶ የተለየ አንጀት ይጠይቃል። የኔ አንጀት ታዲያ ከምን ተሰራ?
«የኔ ውድ እንግዲህ ህልሜን እግሮችሽ ሥር ፥ከዘረጋሁ ወዲህ
ዝግ ብለሽ እርገጪ ፥ዝግ ብለሽ ኺጂ
ህልሜ ላይ ነውና ፥ የምትራመጂ»
ሕይወት፣እግር ማንሳቱን አንሺ፣መንገዱን መፈተን አይከፋም። ህልሜን አደራ!...በማር የተለወሰ መርዝ ታውቂያለሽ?...በጭቃ ውስጥ የተደበቀ እሾህስ? ምናልባት ፍጽምናን ፍጥረት ላይ መፈለግ ይከብዳል። አንቺም ፍጥረት ነሽ አይደል?፣ካለ ሥጋ፣ካለ ነፍስ ፣ካለ እስትንፋስ ምንም እንደሆንሽ ይሰማኛል። ከመኖሬ ጋር የኖርሽ ፣ከሞትም ጋር የሞትሽ እንደሁ ...መኖሬ በአንቺ  መኖር ተገልጦ ፣መሞቴም በአንቺ መሞት የተቋጨ እንደሁ...«ሁሉም ካለ እኛ ባዶ »።አለሽ ብዬ መመከቴ ይገርማል ...ምንም እንኳ እንደ አሞሌ ጨው ብትሟሚ ፣እንደ ተልባ ስፍር ከድርብብ ባታልፊ ....
            «ሁሉ ሲያዳልጠኝ
              ሁሉ ሲያዳክመኝ
              ቀሚስሽን ይዤ
              መትረፌ ገረመኝ»
«ተስፋ»ይሉት ስንቅ አለሽ። የተቋጠረበት አገልግል ምን ይገዝፍ ? ሁሌም ማለቅን አያውቅም። ምንም ነገር ተስፋ አለማድረግ እንዴት ይቻላል ?  I hope nothing..I am free የሚባለው ምን ዓይነት በራስ መተማመን ላይ ሲደረስ ነው?_እንጃ። «አለሁ ይለኛል ..ጠዋት» ማታ ቃሉን ባይደግምም። «አለሁ» እና «አይዞህ» ፈዋሽ መድኃኒቶች። ስለኖርኩ ብቻ ፣በአንቺ ምርኩዝ ድኩም ጉልበቴን ስለደገፍኩ ብቻ ፣ደስተኛ ነኝ።
           «ፀሐይ በገባዖን ላይ
           በጦርነት ሜዳ ሰማይ
          ቁማ ትቅር ከቶ አትልቅ
           ጀግና ቢሻው ይተላለቅ»
መኖርን የመሰለ የለም።«ፀሐይን አምኜ ኩራዜን አልሰብርም»ብሏልና...ከሞት ወዲያ ስላለ ሕይወት ሲባል የአሁንን ሕይወት መቅጠፍ አያስፈልግም።«ሞቼ ልረፍ»ይላል አባቴ። ሞቶ ማረፍ ይኖር? _ለእርሱ ይቅር። አባቴን ያስተዋወቀኝ መኖር ነው። ባይኖር አላውቀውም። አባት ይሉትን መከታ መኖር ከለገሰኝ ...ምን አነሰኝ? እናት ይሏትን እውነት ከሰጠኝ...ምን ጎደለኝ? ከሕይወት ጋራ ተቃቅፌ ፣ተራራ ሸሎቆውን አልፌ ፣ምድራዊ ገነትን አግኝቼ ፣ከለምለም ሳሯ ተኝቼ ፣ትንሽ ህልም ቢጤ አልሜ ፣ሕይወት ስትራመድ እንዳትረግጠው ነግሪያት ቀድሜ፣ ከፈጠረኝ ጋር በዝምታ ተነጋግሬ፣ቃል ሳልጭር ተረድቶኝ ፣የአባት አባትነቱ ገብቶኝ ፣ ልቤ በፍስኀ ተሞልቶ ፣ቤቴ በደስታ ተውጦ ፣ኀዘን አዝኖ አይቼው...ወቼው!
 «ምኞቴም በረደ ፥ ቁጣዬም አለፈ
  ከዕድሉ ጋር ታግሎ፥ማነው ያሸነፈ»
ማንም። «ይታደሉታል እንጅ አይታገሉትም »ቢሉ በዕድል የሚያምኑ ፤«አይታደሉትም ይታገሉታል እንጅ» ቢሉ ቀዋሚዎች ሕይወት እንደሁ ጅረት ናት። ለጥያቄዎች ሁሉ ፣ለመፈክራችን ሁሉ መልስ አትሰጥም። በግራ ጆሮዋ ሰምታ በቀኝ ጆሮዋ ታፈሳለች።ዕድል የሚለውን ቃል ደጋግሜ እጠቀማለሁ ..መኪና ለገዛ፣ቆንጆ ሚሽት ላገባ፣ስኮላርሺፕ ለደረሰው። ለዕድል ዝቅ ብዬ፣ከሥራ ጋር ታግዬ፣የሕይወትን ቀሚስ ጫፍ ይዤ ፣አባቴን እየወደድኩ ፣መኖርን እያወደስኩ ልዘልቅ ነው የተነሳሁ።
     «አይቦዝን አንቀልባው
     አይሞላም ጉድጓዱ
     ሺዎች ሞተው ሲያድሩ
     ሺ ዎች ተወለዱ።
    ይመሻል ይነጋል
    ያው እንደልማዱ »
ፈረቃው ጸንቷል። አለፈ ሲሉት አያልፍም። ለአባቴ መወድስ ይዤ ስነሳ ፣ለአባቱ ስለት ያነሳ_አውቃለሁ።የጤዛ ግብር የተጠናዎተው ሕይወት ፣ የዕጸ-ከንቱ ግብር ያሟሸው ፍርጃ አለ።እሳት የፈጃት ሴት ገላ ላይ ያየሁት ጠባሳ ደርቋል ፤የውስጥ ጠባሳ ግን ፈውሱ ከየት ነው?_መኖርን መልመድ ።«ጋን ቢሰበር ገል ፥ገልም ለጭስ ማጫሻነት የሚውል..ከከፍታው ቢወርዱም በወደቁበት ጥቅም መስጠትን» እሻለሁ። ሊመሽ ሊነጋ ቀኑ፣ዙሩ ላይደርስ የቁናው ውጥኑ ፣ ከ”ከ_እስከ” ቅንብብ ላልወጣ፣መኖርን የሚያስንቅ ላይኖር፣አባትን የሚተካ አባት ላይሰጠኝ ...አልለፋም። የተሰጠኝን አመስግኜ፣ጉልበቴን በሥራ ፈትኜ ፣የቻልኩትን ለመድረስ ፣ጠዋት ከእንቅልፌ ስወገስ፣በመውደቅም በኩል ድል እንዳለ ፣ለራሴ ደጋግሜ ነግሬው፣ ዕድሌን አቡክቼ ጋግሬው፣መድረሻዬን ከመነሻዬ አውቄ ፣ወገቤን በሦስት ዙር ቀበቶ ታጥቄ፣ እጄን ላልሰጠው ለሞት፣ በፍቅር ልወድቅ ከሕይወት ..የመረጥከኝ እኔ ማን ነኝ?





Read 697 times