Saturday, 24 June 2023 20:36

ሕዝብ አይጥላህ! አይውደድህ!

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

   ሕዝብ ሲወድህ አንከብክቦ ያነሳሃል። ከመሬት ያላቅቅሃል። አየር ላይ ያንሳፍፍሃል። ለጊዜው ያስደንቃል። ከላይ ሆነህ ዙሪያህን ሁሉ ከዳር እስከዳር የማየት አዲስ እድል  ይሰጥሃል። የስጋት ሽውታ የሚነፍስብህ በቀስታ ነው።
አዎ፣ በእግሮችህ መቆም አትችልም። ከመሬት አንስተው ከፍ አድገውሃል። ምንም ብትሆን፣ ምንም ቢገጥምህ፣ የሕዝብ አፍቃሪ እጆች ያቅፉሃል። በህዝብ መዳፍ ውስጥ ገብታለች-ሕይወትህ።
በእርግጥ የሕዝብ ፍቅር በደስታ የማስከሩ ያህል፣ እንደ ጣፋጭ ሕልም በየመሃሉ ድንገተኛ ፍርሃቶችንም ይቀላቅላል። አየር ላይ ስትሆን ከምድር  ስትርቅ፣ ካሁን ካሁን ወረወሩኝ፣ ካሁን አሁን ፈጠፈጡኝ የሚል የስጋት ስሜት ከስር ይነካካሃል። ቅዝቃዜውም ግራ ቀኝ ወደ ውስጥ መስረግ ይጀምራል። የጥርጣሬ ጠብታዎች እየዋሉ እያደሩ እየጠጠሩ ይሻክራሉ። ይቆጠቁጣሉ።
አንዳንዴ የሕዝብ ነገር እንደ አውሎ ነፋስ ነው። ከምኔው ተነስቶ አካባቢውን ሁሉ እያሾረ፣ እንዴት ሰማይ እንደሚነካ ሲያዩት ያስደንቃል። ግን እንደ አነሳሱና እንደ አመጣጡ ድንገተኛ ፍጥነት፣ የመሄጃ አቅጣጫውም ለግምት ያስቸግራል። አገር ምድርሩን እንደ እንዝርት እንዳላሽከረከረ፣ ትንሽ ቆይቶ ፀጥ ረጭ ይላል። አካባቢውን ጥሎ ከወዲያ ማዶ ከአድማስ ጀርባ ይሻገራል። ያንሳፈፈውን ሁሉ አራግፎ ሌሎችን ደግሞ ያስነሳል።
ሕዝብ የወደደህ ጊዜ የእድልህ ብዛት ቁጥር የለውም። ግን ከነአደጋው ነው። ከመሬት አንስቶ ከፍ ያደረገን ጊዜ፣ ከደስታና ከፌሽታ ጋር ጥርጣሬና ስጋት ቢፈጥርብን አይፈረድብህም። እንዳንሳፈፈኝ ቢያራግፈኝስ እንላለን። ማለትም አለብን።
ግን፣ በጣምም አንጨነቅ።
በህዝብ የመውደድ እድል ብርቅ ነው። ከተገኘ በኋላም አምልጦ እንዳይሄድ መስጋት  ብልህነት ነው። ነገር ግን፣ ተወዳጅ የመሆን ረሃብ ቢኖርብሽ እንኳ፣ ሕዝብም አንቺን የመውደድ ረሃብ አለበት። የሕዝብ ፍቅር ቢያጓጓህ፣ በሕዝብ ጉያ መታቀፍ ቢናፍቅህ እንኳ፣ የሕዝብ እጆችም አንተን እንደሚፈልጉ አትርሳ።
መዳፋቸው ባዶ ሲሆን አይወዱም። ሽቅብ እንደ ባንዴራ አንግበው የሚያመጥቁት ነገር ካላገኙ፣ የሕይወት ትርጉም የጠፋባቸው ያህል የባዶነት መንፈስ ያጠላባቸዋል። የሚያወድሱት ሰው ካጡ፣ያቃዣቸዋል። የሚያንከበክቡት ነገር ይፈልጋሉ፡፡ የሚያደንቁትና የሚተማመኑበት ሰው ለማግኘት ያልማሉ፡፡
የሚመኙት ዓይነት እፁብ ድንቅ፣ የሚያስቡት ያህል የበቃና የላቀ አስገራሚ ሰው ባያገኙ እንኳ ችግር የለውም፡፡ ትንሽ ምልክት ትንሽ ፍንጭ አሳያቸው፡፡ ከዚያ በኋላ፣ ድክመትህን ቸል የማለት፣ በይቅርታ የማለፍ፣… አይተው እንዳላዩ የመሆን ችሎታቸው ወሰን የለውም፡፡
ጥንካሬህንና ብቃትህን ደግሞ፣ እጥፍ ድርብ አግዝፈው፣ ከተራራው አናትም በላይ አሳልፈው አግንነው ያዩልሃል፡፡ በምናባቸው ያነፁሃል፡፡ በምናባቸው ክንፍ ያወጡልሃል፡፡ ያከንፉሃል፡፡  
ይሄውና በረረ ይሄውና መጠቀ ይሉልሃል። ከመሬት ላይ ስንዝር ታህል ንቅንቅ ባትልም ችግር የለውም። በእልልታ በመዳፋቸው ከመሬት አላቅቀው አየር ላይ ያንሳፍፉሃል፡፡
እንዳያራግፉህ መስጋት አስተዋይነት ቢሆንም፣ ከዚህ የባሰ ሌላ አደጋና ፈተና አለ፡፡
አሎምፒያ ተራራ ላይ ሲያደርሱሸ፣ አንተን ደግሞ ክንፍ ሲያወጡልህ፣ ፀሃያችንና ኮኮባችን እያሉ ሲያወድሱሽ፣… የአነጋገር ለዛ ይመስላል። ግን አይደለም። ከልብ አምነህ እስክትቀበል ድረስ እረፍት አይሰጡህም።
ለጊዜው፣ ለዛሬ ብቻ፣ ፍቅራቸውን ለመግለፅ ያህል እንጂ ከምር በራሪ መጣቂ ሆኜ አይደለም ብለሽ ታስቢ ይሆናል። በምሳሌያዊ ዜይቤ ለመናገር ፈልገው እንጂ፣  ፀሀያችንና ከኮባችን ነህ ማለታቸው ከምር አይደለም ብለህ ማሰብህ አይቀርም፡፡ የሕዝብ ውዳሴዎች አጀማመራቸው ሁልጊዜ እንደዚያ ነው፡፡ በምሳሌያዊ አነጋገር ነው።
ነገር ግን የዛሬ ምሳሌያዊ ዘይቤ፣ ነገ ቃል በቃል የሚታመንበት መፈክርና ውዳሴ እየሆነ ይመጣል፡፡ አምነህ እስክትቀበል ድረስ፡፡ አሜን እስትያቸው ድረስ የሕዝብ አንደበቶች እረፍት የላቸውም። ቀላል ፈተና አይደለም፡፡ ባለክንፍ ነኝ ብለሽ እስከምታምኚ ድረስ፣ ለመብረር እስክትንደረደር ድረስ፣ ከእጃቸው ላይ ተስፈንጥረሽ አየር ላይ እስክትንሳፈፊ ድረስ፣... ያሳምኑሻል፡፡
… ክንፍ ስለሌለህ ቁልቁል እስክትወርድ ድረስ ያሳምኑሃል።
ህዝብ አብዝቶ ሲወድህ የዚህን ያህል ነው ፍቅሩ።
 በሕዝብ የተወደዱ ሰዎች አቤት ፈተናቸው።
ህዝብ ያወደሳቸው ገዢዎችና ተቃዋሚዎች፣ የተዘመረላቸው ባለስልጣናትና የተዘፈነላቸው ሽፍቶች፣ መሪዎችና ረዳቶች፣… ጠንቃቃና ጨዋ ቢሆኑ እንኳ፣ ሕዝብ በከፈተላቸው ቦይ ውስጥ መግባት አይቀርላቸውም። ታዲያ የሕዝብ ፍቅር የዛሬ የዘመናችን ፈጠራ አይደለም። ድሮም ጥንትም ነበረ።
የዳዊትን ታሪክ ካስታወሳችሁ ጎልያድን አሸንፎ እንደጣለ ትዝ ይላችኋል።
ንጉሡ ሳኦል የዳዊትን ጀግንነት በማየት ሹመት ሰጠው። ጦርነቱ በድል አድራጊነት ተጠናቀቀ። ከድል መልስ፣ “ጉሮ ወሸባዬ” ተዘፈነ። አገሩ ደመቀ። በየከተማው ሁሉ ድል አድራጊውን ንጉሥ አፄ ሳኦልን ለመቀበል ሰማይ ምድሩ በሴቶች እልልታ ተንቆጠቆጠ። ትረካውን ተመልከቱ።
እየዘመሩና እየዘፈኑ፣ እልል እያሉ፣ ከበሮና አታሞ ይዘው፣ ንጉሡን ሳኦል ሊቀባበሉ… ወጡ።
… ሳኦል ሺህ፣ ዳዊትም አስር ሺህ ገደለ” እያሉ እየተቀባበሉ ይዘፍኑ ነበር።
“ሳኦልም እጅግ ተቆጣ። ይህም ነገር አስከፋው። ለዳዊት አስር ሺህ ሰጡት። ለኔ  ግን ሺህ ብቻ ሰጡኝ። ከንግሥና በቀር ምን ቀረበት?” አለ።
ከዚያ ቀን ጀምሮ ሳኦል ዳዊትን ጠምዶ ያዘው።
የሕዝብ ፍቅር፣ የሕዝብ መዝሙር፣ የወይዛዝርት ዘፈን ምን ያህል ሞገደኛ እንደሆነ ተመልከቱ።
ሳኦል ዳዊትን ስንቴ ሊገድለው እየሞከረ፣ ዳዊት ስንቴ ለትንሽ እያመለጠ ይዘለቃል? ወደለየለት ጠላትነት ገቡ። ሳኦልና ዳዊት፣ አሳዳጅና ተሳዳጅ፣ ገዢና ተቃዋሚ፣ ንጉሥና ሽፍታ ሆነው ለአመታት ተዋግተዋል።
አገርን የሚያተራምስ የዓመታት ጦርነት፤ “ሞቼ እገኛለሁ፤ ወይ አንተ ወይ እኔ” በሚል ስሜት ተጀምሮ፤ እስከ መጠፋፋት ደረሰ። ንጉሡ ሳኦል ሞተ፤ ሽምቅ ተዋጊው ዳዊት ነገሰ።
የዚህ ሁሉ መነሻ፣ የአድናቂዎች ዘፈን ነው። የጦርነቱ መንስኤ ባይሆን እንኳ መነሻ ነው። የሕዝብ ፍቅርና ውዳሴ ነው ሰበቡ። ለዚያውም ሳኦልና ዳዊት፣ “ተወዳጅ” ለመሆን የፖለቲካ ቅስቀሳ አላካሄዱም። የሕዝብ ውዳሴ በራሱ ጊዜ ነው የመጣባቸው። ወደ ጦርነት ከገቡ በኋላ ነው ተቀናቃኞቹ ተዋጊዎች በየፊናቸው፣ ቅስቀሳውንና ፕሮፖጋንዳውን ያሟሙቁት። የዳዊትና የሳኦል ዲስኩሮችን መመልከት ትችላላችሁ።
ሳኦል በጦር አውድማ እንደሞተ ዳዊት ሲሰማ አልጨፈረም። ለቅሶ ተቀመጠ። የድል አድራጊነት ሳይሆን? የሀዘን አዋጅ አስነገረ። የሀዘን መዝሙርም አውጥቷል።
የሳኦልን ጀግንነት እያወደሰ፣ የእስራኤል ክብር ዛሬ ወደቀ ብሎ ተቀኝቷል። የዳዊት ፍላጎት፣ በሀዘን አዋጁና በሀዘን መዝሙሩ አገሬውን ለማዳን ነው። ግን፣ ሰፊ ተወዳጅነትና ተቀባይነት ለማግኘትም ነው። አገርን በጎራ የሚከፋፍል ተቀናቃኝነትን ለማብረድ ነው የዳዊት ጥረት። ከሁሉም ጎራ ድጋፍ ለማሰባሰብም ነው።
“የዳዊት ወገን የይሁዳ ነገድ ነው”፣ “የሳኦል ወገን የቢንያም ነገድ ነው” የሚል የዘረኝነት ስሜት እንዳይቀጣጠል የታሰበ ነው- የሐዘን አዋጁና የሐዘን መዝሙሩ። በዘር እየተቧደኑ ገሚሱ እንዳይጨፍር፣ ገሚሱ በቁጭት እንዳያምፅ ነው- የዳዊት የፖለቲካ ቅስቀሳ።
ተወዳጅነትን ለማትረፍና ዝና ለማግኘት የተነጣጠረም ነው። በዚህ በዚህ ግን አቤሰሎም አቻ የለውም- “የፖለቲካ ቅስቀሳ ኤክስፐርት” ሆኗልና። አቤሴሎም፣ የዳዊት ልጅ ነው። ዙፋን ለመውረስ በርካታ ዓመታትን የመጠበቅ ትዕግስት አልነበረውም። ስልጣን አስረከበኝ ብሎ አባቱን ለማሳመን አልሞከረም።
“ወደ ሕዝቡ ወርዶ፣ የልብ ትርታቸውን ማዳመጥ”፣… በዚህም አማካኝነት የልብ ትርታቸውን መቃኘት ጀመረ አቤሴሎም።
የቤተመንግሥት ሽኩቻ ውስጥ አልገባም። ይልቅ ከቤተመንግስት ውጭ ከህዝቡ ጋር ትከሻ ለትከሻ  ይተቃቀፍ ጀመረ። ተራ ተርታውን ሰው እያቀፈ ይሳሳማል። ዳዊት  ንጉሥ ሳኦልን ያሸነፈው ከቤተመንግስት ርቆ፣ ከመናገሻ ከተማ ሸሽቶ፣ በረሃ ገብቶ በሽምቅ ጦርነት ነው።
አቤሴሎም ግን በተቃራኒው፣ በእርቅ ከስደት አገር ተመልሶ ወደ  መዲናይቱ ከተማ ከመጣ በኋላ ነው “ሕዝባዊ ትግል” ጀመረው። ለዚያውም በቤተመንግስቱ ደጃፍ። ትረካው እንዲህ ይላል።
አቤሴሎም፣ ሰረገላና ፈረሶች፣ ከፊቱ የሚሮጡ ሰዎች አዘጋጀ። በማለዳ ተነሥቶ በበሩ አደባባይ ይቆም ነበር። ከንጉሡ ፍርድ ለማግኘት የሚመጡ ባለጉዳዮችን ሁሉ እየጠራ ያነጋግራቸዋል።
“አንተ ከወዴት ከተማ ነህ? ብሎ ጠይቃል። ባለጉዳዮች ከየት እንደመጡ በትህትና ይናገራሉ። አቤሴሎም በአዘኔታ ያጽናናዋል።
“ጉዳይህ እውነትና ቅን ነው። ነገር ግን ከንጉሡ ተመድቦ ጉዳይህን የሚሰማህ የለም” ይላል- በሃዘኔታ። ያለ ዳኝነት የተጉላሉ ባለጉዳዮች ይህን ሲሰሙ ምን አይነት ስሜት እንደሚፈጥርባቸው አስቡት። በቁጭት ይንገበገባሉ። በንጉሥ ዳዊት ላይ ቂል ይይዛሉ። ለአቤሴሎም ፍቅራቸውን ይሰጣሉ። አቤሴሎም  እንዴት የሰዎችን ስሜት ለራሱ አላማ ማነሳሳት እንደሚችል ያውቃል። እንዲህ ይላቸዋል።
ጉዳይና ሙግት ያለበት ሰው ሁሉ ወደ እኔ እንዲመጣ፣ በቅን ዳኝነትም እንድፈርድለት፣ በአገር ላይ ዳኛ አድርጎ ማን በሾመኝ?  ይላል አቤሴሎም።
ለሕዝብ ምንኛ ተቆርቋሪ ነው! ያስብላል።
ይህም ብቻ አይደለም። የንጉሥ ልጅ ልዑል አይደል? ሰዎች  ጎንበስ ብለው ሰላምታ ሲያቀርቡ፣ አቤሴሎም እንደዘመድ እንደጓደኛ እጁን ዘርግቶ ያቅፋቸዋል፤ ይስማቸዋል። ወደ ንጉሡ ለስምታ ለአቤቱታ የመጡ ባለጉዳዮችን ሁሉ እየተቀበለ እንዲህ ያስተናግዳቸው ነበር። አቤሴሎምም የእስራኤላውያ ልብ ሰረቀ።
የአባቱን አገዛዝ እያጥላላ፣ የራሱን የለውጥ ምኞትም እየገለፀ፣ ሕዝብን እያቀፈና እየሳመ ለአራት ዓመታት በቤተመንግስቱ ዙሪያ ቀሰቀሰ። ተወዳጅነትን አተረፈ።
የሕዝብ ልብ ወደ አቤሴሎም ሸፈተ። ከአራት ዓመት “ሕዝባዊ ቅስቀሳ” በኋላ፣ ደጋፊዎቹን ሰብስቦ ራሱን አነገሠ።
በዳዊት ላይ ዘመተ። ዳዊት ላይ ሕዝቡ ተነሥቶበታል። ከቤተመንግስቱ ወጥቶ ሸሸ። ከከተማዋ ወጣ። ከአገሩ ተሰደደ። ግን በዚያው አልቀረም። ዳዊት ብዙም ሳይቆይ፣ በውጊያ ጥርሳቸውን የነቀሉ የራሱን ወታደሮች አደራጅቶ ከአቤሴሎም “የሕዝብ ጦር” ጋር ተዋጋ። አቤሴሎም ተገደለ።
የአቤሴሎም “ሕዝባዊ ጦር” የውጊያ  ልምድ አልነበረውም። የአቤሴሎም ተዋጊዎች ተበታተኑ። ብዙም ሳይቆይ ብዙ ሕዝብ የተሰበሰበው፤ ዳዊትን ለመቀበል ነው።
መቼ ካሁን በኋላ በህዝብ ላይ መተማመን ለዳዊት ዘበት ነው። በምን ያህል ፍጥነት እንደሸሹት አይቷል። አሁን ሕዝብ ተሰብስቦ ሲመጣለት በልቡ ቢጠራጠር አይገርምም።
ሕዝብ ግን ዝም አይልም። ታማኝነቱንና ድጋፉን ለመግለጽ የመፎካካሪያ ዘዴ አያጣም።
ለሁለት ጎራ ተከፍለው፣ “ንጉሡ ለእኛ ይቀርባል፣ ንጉሡ የኛ ወገን ነው” እያሉ አንደኛ ቲፎዞ መሆናቸውን ለማሳየት ይሽቀዳደማሉ። በዘር በነገድ ይቧደናሉ። በዚህ ምክንያትም ኩርፊያና ቂም ይፈጠራል። በዘር በነገድ የመቧደን በሽታ እንዳይባባስ በብርቱ ይጥር የነበረው ዳዊት፣ አሁን በዝምታ ከማየት ከመስማት ውጭ ምንም አላደረገም። ከመዘዙም አላመለጠም።
ንጉሡ ገና አዲስ የሕዝብ ድጋፍ አጣጥሞ ሳይጨርስ፣ ወደ መናገሻ ከተማው ሳይደርስ፣ አዲስ አውሎ ነፋስ ይፈጠርበታል። በቅሬታና በኩርፊያ ስሜቶች ላይ መጋለብና መሾፈር የሚችሉ ድንገተኛ መሪዎች ከመቼው እንደሚመጡ አይታወቅም። ግን ይመጣሉ።
ሳቤዔ የተባለ ከዚያ በፊት የማይታወቅ ሰው ድንገት ገነነ። የአዋጅ ድምጽ አስተጋባ። ከዳዊት ዘንድ ምንም እድል ምንም ድርሻ የለንም፤ እስራኤል ሆይ ወደ የድንኳንህ ተመለስ ብሎ አወጀ። በየፊናቸው ወደየመጡበት አካባቢ ተበታትነው እንደሄዱ ሲያውጅ፣ ሕዝቡ ግን ተሰብስቦ ተከተለው። ህዝቡ ከዳዊት ወደ ሳቤዔ ጎረፈ። ሳቤዔ በአንድ ጀምበር የሕዝብ ሰው የሕዝብ መሪ ሆነ። እምቢ ለማለት ቢፈልግስ ማን ይፈቅድለታል? ህዝብ ከወደደህ አታመልጥም። የአመፅ መሪውን እንዲያሳድዱ፣ የዳዊት ወታደሮች እንደገና ለጦርነት እንዲዘምቱ ተነገራቸው።ከረዥም መንገድ በኋላ፣ የሆነ ከተማ ላይ ደረሱበት። ያው የድሮ ከተሞች በግንብ የታጠሩ ናቸው። በቀላሉ መግባትና ማሸነፍ  አይቻልም። በዚያው ልክ የድሮ ጦርነት፣… እልቂትና ምህረት የለሽ ጭካኔ የበዛበት ነው። አፈራርሶ፣ ዘርፎ፣ አቃጥሎ፣ አመድ እስኪሆን ድረስ አገሩን የሚያጠፋ ነው የድሮ ጦርነት።  ለነገሩ ዛሬም ከዚያ ያልተነሳሱ ጥፋቶችን እያየን ነው።
የሆነ ሆኖ፣ አንዲት ብልጥ ሴት፣ የከተማዋ አጥር ግንብ ላይ ወጣች።
የዳዊት ወታደሮች ከተማዋን ለመውረር ተዘጋጅተዋል። ሴቲቱ ለወታደሮቹ መሪ እንዲህ አለችው። “በእስራኤል ዘንድ ሰላምንና እውነትን የምወድ እኔ ነኝ። አንተ የእስራኤል እናት ከተማን ለማፍረስ ትሻለህ” አለችው። ለምን ከተማዋን ማጥፋት ትፈልጋህ ብላ ጠየቀችው።
እሱም መለሰለት። ማጥፋት ከኔ ይራቅ… ሳቤዔ የሚባል አንድ ሰው ግን በንጉሡ በዳዊት ላይ እጁን አነሳ። እሱን ብቻ ስጡኝ። እኔም ከከተማይቱ እርቃሁ አላት።
ሴቲቱም፣ ጭንቅላቱን በግንብ አጥር ላይ እንጥልልሃለን አለችው።
እንዳለችው ሆነ። ሕዝቡ በሰፊ ድጋፍ የተከተሉትን መሪያቸውን ሳቤዔን ገድለው፣ በአጥር በኩል ወረወሩት።
ሕዝብ ያነግሳል፤ ይወረውራል። ንጉሡ ዳዊት ለጊዜው አሸነፈ። ግን ሰላም አላገኘም። የራሱ ልጆች፣ የራሱ ባለስልጣናት ይነሡበታል- የሕዝቡን የልብ ትርታ እየተከተሉ።



Read 822 times