Saturday, 01 July 2023 00:00

ቡዳፔስት 2023

Written by  ግሩም ሰይፉ
Rate this item
(0 votes)

• ለኢትዮጵያ ቡድን የተመረጡ ዕጩ አትሌቶች ታውቀዋል
• የመስተንግዶው እድል ወደ አውሮፓ ያጋድላል፣ በአፍሪካ አንዴም አልተዘጋጀም
• ለሐንጋሪ 200 ሺ በላይ የስታድዮም መግቢያ ትኬቶች ተሸጠዋል
• በ2002 አሬጎን ላይ ከ241.5 ሚ.ዶላር በላይ ተንቀሳቅሷል
• በ2017 ለንደን ላይ ከ700 ሺ በላይ ትኬቶቹ ተሸጠዋል
• በ2025 ቶኪዮ፣ በ2027 ቤጂንግ/ለንደን፣ በ2029 ኬንያ?
• መስተንግዶ በጀት ከ75-80 ሚ.ዶላር


በሐንጋሪ ቡዳፔስት ለሚካሄደው 19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና 50 ቀናት ቀርተዋል፡፡ በሻምፒዮናው ለሚሳተፈው የኢትዮጵያ ቡድን የተመረጡ እጩ አትሌቶች ሰሞኑን ታውቀዋል። በእጩ አትሌቶቹ ዝርዝር ከማራቶንና ከ10ሺ ሜትር ርቀቶች ውድድሮች እስከሚዘኑ ድረስ በሚመጣው ውጤት የደረጃ ማስተካከያ እንደሚደረግ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታውቋል። የዓለም ሻምፒዮን ሆነው በቀጥታ የገቡ 4 አትሌቶች ናቸው።  ከዓመት በፊት በኦሬጎን በተካሄደው ሻምፒዮና ላይ ሜዳልያና ዲፕሎማ ያሸነፉ የሚገኙበት ሲሆን አዳዲስ አትሌቶች ተካትተዋል። ፌዴሬሽኑ በቀጣይ ሳምንታት ሙሉ ቡድኑን  ካሳወቀ በኋላ  ወደ የመጨረሻው የዝግጅት ምዕራፍ  እንደሚገባ ይጠበቃል።
ለዓለም አትሌቲክስ  ማህበር  WORLD ATHLETICS የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዋና ውድድሩ ነው።  በምርጥ አትሌቶች ተሳትፎና የፉክክር ደረጃው ከኦሎምፒክ ቀጥሎ ይጠቀሳል። በሻምፒዮናው ዙርያ የተሰራ ጥናት እንደሚያመለክተው  በዓለም ዙርያ በአትሌቲክስ ስፖርት ከ3.5 ሚሊዮን በላይ አትሌቶች ተመዝግበዋል። የዓለም አትሌቲክስ ማህበር የ214 አገራት አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖችን በስሩ አሰባስቧል።   በየዓመቱና በየሁለት ዓመቱ የሚካሄዱ ከ30 በላይ ዓለምአቀፍ ውድድሮችን በበላይነት ያስተዳድራል።  አትሌቲክስ በታላቁ የኦሎምፒክ መድረክ ከሚካሄዱ ስፖርቶች ዋናው እንደሆነም ይታወቃል። የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የመስተንግዶ ደረጃ ከዓለም ዋንጫና ከኦሎምፒክ ጋር ይስተካከላል።  በሩጫ፤ በርምጃ ፤ በዝላይና በውርወራ ስፖርቶች የዓለም ምርጦችን ያሳትፋል።
  ከ1ኛው ጀምሮ እነማን አዘጋጅተዋል?
የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለመጀመርያ ጊዜ የተዘጋጀው በ1983 እ.ኤ.አ በፊንላንድ ፤ ሄልሲንኪ ነበር፡፡ አጀማመሩ  ላይ በየአራት አመቱ እንዲካሄድ ተወስኖ ስለነበረ በ1987 እኤአ ላይ ሁለተኛው በጣሊያን፤ ሮም እንዲሁም  በ1991  እኤአ ላይ ሶስተኛው  በጃፓን ፤ቶኪዮ ተዘጋጅተዋል። በ1993 እኤአ ላይ በጀርመን፤ ስቱትጋርት  4ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ተዘጋጅቶ በየሁለት ዓመቱ የሚካሄድ ዓለም አቀፍ ውድድር ሆኗል፡፡ በ1995 እኤአ በስዊድን ጉተንበርግ፣ በ1997 እኤአ በግሪክ አቴንስ፣ በ1999 እኤአ  በስፔን ሴቪላ፣ በ2001 እኤአ በካናዳ ኤድመንተን፣ በ2003 እኤአ በፈረንሳይ  ፓሪስ፣ በ2005 እኤአ በፊንላንድ ሄልሰሂንኪ (ለሁለተኛ ጊዜ) በ2007 እኤአ በጃፓን ኦሳካ፣ በ2009 እኤአ በጀርመን በርሊን፣ በ2011 እኤአ  በደቡብ ኮሪያ ዴጉ፤  በ2013 እኤአ በራሽያ ሞስኮ ፤ በ2015 እኤአ በቻይና ቤጂንግ  ፤ በ2017 እኤአ ላይ በእንግሊዝ ለንደን ፤ በ2019 እኤአ በኳታር ዶሃ ከ5ኛው እስከ 17ኛው  የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች በሁለት ዓመት ልዩነት በቅድም ተከተል አከናወነዋል። በ2021 እኤአ ላይ በኮሮና ሳቢያ ሻምፒዮናው  በ1 ዓመት ተሸጋሸገ። ከዚያም በ2022 እኤአ በአሜሪካ  ኦሬጎን 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ተካሂዷል።  በ2023 እኤአ ላይ 19ኛው  የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናን የምስራቅ አውሮፓዋ ሐንጋሪ  በቡዳፔስት የምታስተናግደው ይሆናል።
ሐንጋሪ ከሻምፒዮናው በኋላ ኦሎምፒክን ለማዘጋጀት ትፈልጋለች
ሐንጋሪ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናን በቡዳፔስት ለማስተናገድ ከፍተኛ ዘመቻ አድርጋለች፡፡ ሻምፒዮናው በምስራቅ አውሮፓ ሲካሄድ የመጀመሪያው ሲሆን ከ200ሺ በላይ የስታዲዮም መግቢያ ትኬቶች ተሸጠዋል። ሃንጋሪ  በ2024 እኤአ ላይ ኦሎምፒክን ለማስተናገድ የነበራት ጥረት ባለመሳካቱ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው በእልህ የገባችበት መሥተንግዶ ነው፡፡ ኦሎምፒክ የማዘጋጀቱን እቅድ ከ250ሺ በላይ ሃንጋሪያውያን ባሰባሰቡት የተቃውሞ ፊርማ አሰናክለውታል። የዓለም ሻምፒዮናው በአውሮፓ ለ12 ጊዜያት ተዘጋጅቷል። የኤሺያ አህጉር 5 ሻምፒዮናዎትን ሲያስተናግድ በሰሜን አሜሪካ ደግሞ በሁለት አገራት ተከናውኗል። የአፍሪካ አህጉር ተራ መቼ ይሆን? የኦሎምፒክ መስተንግዶውን ከሻምፒዮና ስኬታማ መሥተንግዶ በኋላ የምትመለስበት ይመሥላል።
 ከቡዳፔስት በፊት ኦሬጎን ላይ የተገኘው ውጤት
የዓለም አትሌቲክስ  ባዘጋጀው ሪፖርት እንደተጠቀሰው  በ2022 እኤ ላይ በአሜሪካ ኦሬጎን በተከናወነው 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ 180 አገራትን የወከሉ ከ1700 በላይ አትሌቶች ተሳትፈዋል። 81  አገራት በፍፃሜ ውድድሮች መሳተፋቸው ፤ 49 አገራት የሜዳልያ ሰንጠረዥ ውስጥ መግባታቸውና 29 አገራት 1 እና ከዚያ በላይ የወርቅ ሜዳልያ ተጎናጽፈዋል። በሌላ በኩል ሻምፒዮናው ለአዘጋጁ አገርና ከተማ ብዙ ውጤቶችን አስገኝቷል። የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና  ኢኮኖሚ በማነቃቃት፤ በስፖርት ዓለምን በማስተሳሰር፤ በገፅታ ግንባታና ዓለምአቀፍ ተቀባይነት ያስገኛል።
የዓለም አትሌቲክስ ማህበር ሻምፒዮናውን አስመልክቶ ባዘጋጀው ሰነድ እንደገለፀው በኦሬጎን ተካሂዶ በነበረው የዓለም ሻምፒዮናው  ላይ  ከ241.5 ሚሊዮን ዶላር በላይ በኢኮኖሚው ተንቀሳቅሷል። በኦሬጎን ግዛት ኢኮኖሚ ላይ በድምሩ ከ153 ሚሊዮን ዶላር በላይ ፈሰስ ሆኗል፡፡ ለዓለም ሻምፒዮናው አጠቃላይ ዝግጅት 29.6 ሚሊዮን ዶላር በቀጥታ  ወጭ ተደርጓል ። በሆቴልና የመስተንግዶ አገልገሎት 45 ሚሊዮን ዶላር፤ በምግብና መጠጥ እሰከ 10 ሚሊዮን ዶላር፤ በትራንስፖርት አገልግሎት 4.3 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም በተለያዩ የንግድ እንቅስቃሴዎችና የመዝናኛ አገልግሎቶች 7.4 ሚሊዮን ዶላር ነው ገቢ ሆኗል፡፡  በሚዲያው መስክ የተንቀሳቀሰው ገንዘብም ከ89.3 ሚሊዮን ዶላር በላይ ነው፡፡ በቴሌዥን ስርጭትና ተያያዥ የብሮደካስት መብቶች 59.3 ሚሊዮን ዶላር፤ በኦንላይን ፕሬስ 19.3 ሚሊዮን ዶላር፤ በህትመት ውጤቶች  3.5 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም በማህበራዊ ሚዲያዎች ከ7.3 ሚሊዮን ዶላር በላይ  ተገኝቷል፡፡
በአካባቢ ጥበቃ ዙርያ የአሬጎን የዓለም አትሌቲክስ  ሻምፒዮናው ያገኘው ስኬትም ይጠቀሳል፡፡  140ሺ ኪሎ ዋት ታዳሽ ሃይል ጥቅም ላይ መዋሉ፤ የካርቦን ልቀቱ በ3263.1 ቶን መቀነሱ፤ ከ325 ሺ በላይ የዉሃ ፕላስቲኮች እንዳይሠራጩ መደረጉ በማስረጃነት ቀርቧል።   ለዓለም ሻምፒዮናው ከ3000 በላይ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ተጋብዘው ከ85 በመቶ በላይ ተሳትፎ ማድረጋቸውም ተወስቷል፡፡ በተለይ በማህበራዊ ሚዲያው ሻምፒዮናው አስደናቂ ትኩረት ያገኘ ሲሆን ስለዓለም ሻምፒዮናው በተለያዩ ሚዲያዎች የተሰራጩት ከ5570 በላይ ልጥፎች ለ37.2 ሚሊዮን ሰዎች መድረሳቸውም ተገልጿል፡፡
የመስተንግዶ ተምሳሌት የሆነው ለንደን በ2017
የዓለም አትሌቲክስ ማህበር በ2017 አኤአ ላይ 15ኛውን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ያስተናገደችውን የለንደን ከተማ በሻምፒዮናው የመስተንግዶ ደረጃ ተምሳሌት ያደርጋታል፡፡ ከ6 ዓመት በፊት በለንደን ከተማ የተከናወነውን ሻምፒዮና ለመታደም ከ700ሺ በላይ የስታድዬም መግቢያ ትኬቶች ተሸጠዋል። ከ335ሺ በላይ አትሌቲክስ አፍቃሪዎች ከመላው ዓለም ተሰባስበው የዓለም ሻምፒዮናውን ለመታደም መብቃታቸው በታሪክ የመጀመርያው ነው፡፡ በዓለም ሻምፒዮናው ለንደንንን ለመጎብኘት ከበቁት ከ69 በመቶ በላይ ከተማዋን በድጋሚ ለመጎብኘት ጠይቀዋል፡፡ ከ81 በመቶ በላይ የሚሆኑት የዓለም ሻምፒዮናው እንግዶች ደግሞ የከተማዋን የቱሪስትና የንግድ መናሐርያዎች ጎብኝተዋል፡፡ ከ90 በመቶ ላይ የሻምፒዮናው ታዳሚዎች የከተማዋን መስተንግዶ በአድናቆት መስክረዋል፡፡
ከቡዳፔስት በኋላ
በ2025 እኤአ  20ኛውን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የምታስተናግደው ቶኪዮ ናት። ጃፓን በ1993 እና በ2007 እኤአ ደግሞ በኦሳካ የዓለም ሻምፒዮናውን ካሄደች በኋላ ለሶስተኛ ጊዜ በማዘጋጀት ልዮ ክብረወሠን ያስመዘገበችበት ነው። ከ21ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በተያያዘ ደግሞ በይፋ የተጠቀሱት በቅርብ ዓመታት ሻምፒዮናውን ያስተናገዱት ቤጂንግና ለንደን ናቸው። የቻይና አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በ2015 እኤአ ላይ 15ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የተሳካ ዝግጅት በመመካት በ2027   በታዋቂው የወፍ ጎጆ ስታዲየም የማዘጋጀት እቅዱን አስታውቋል። በ2017 እኤአ ላይ 16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ያዘጋጀችው ለንደንም መስተንግዶውን በ2027 ለመድገም ፍላጎት አላት። የዓለም አትሌቲክስ ማህበርም ከ6  ዓመት በፊት የተካሄደውን የለንደን መስተንግዶ በተምሳሌት ይጠቅሰዋል።
ኬንያ በ2029
 21ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናን  ለማስተናገድ ሞክራ ያልተሳካለት ኬንያ በ2029 እኤአ ላይ 22ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናን በማስተናገድ በአፍሪካ የመጀመርያው አገር ለመሆን አቅዳለች። የኬንያ ስፖርት ሚኒስትር በናይሮቢ ከተማ በሚገኘው ካሳራኒ ስታድየም የዓለም አትሌቲክስን ለማስተናገድ ጥረት እናደርጋለን ብለዋል። በ2020 የዓለም አትሌቲክስ ወጣቶች ሻምፒዮና ያካሄደችው ኬንያ አለም አቀፍ ውድድሮችን ወደ ናይሮቢ እየሳበች ሲሆን በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ታሪክ 66 የወርቅ ፤ 55 የብርና 44 የነሐስ ሜዳልያዎች በመሠብሠብ ከአፍሪካ እስከ 2029 እኤአ ለማዘጋጀት የአፍሪካ ግንባር ቀደም መሆኗ ይታወቃል። አህጉር እድል ያላት ይመስላል። ከኬንያ ባሻገር ሌሎችም የአፍሪካ አገራት ጥረት ካደረጉ እድሉ ይፈጠራል፡፡ በርግጥ ከሰሜን ሞሮኮ፤ ከደቡብ ደቡብ አፍሪካ፤ ከምእራብ ናይጄርያ ከምስራቅ ኢትዮጵያና ኬንያ በተናጠል ወይም በጋራ ለመስተንግዶው መፎካከር ይጠበቅባቸዋል፡፡ ኬንያ በ2007 እኤአ ላይ እንዲሁም ኡጋንዳ በ2017 የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮዎችን አዘጋጅተዋል።
የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናን ማዘጋጀት
የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናውን የሚያዘጋጅ አገርና ከተማው አስደናቂ እድሎች ይፈጠሩለታል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ የስፖርት መዲና ሆኖ መጠቀስ ፤ የስፖርት ባህልን ማስተዋወቅና ገፅታን መገንባት ይቻላል፡፡ የገቢ ምንጮቹም ከመስተንግዶ የበጀት ድጋፍ፤ ከአገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ስፖንሰሮች፤ ከትኬት ሽያጭ፤ ከተለያዩ ንግዶች፤ ከምግብና መጠጥ አቅርቦት፤ ከሆቴልና ከንግድ ማስታወቂያዎች የሚገኙ ናቸው፡፡ የዓለም አትሌቲክስ ማህበር በሰራው ጥናት የዓለም አትሌቲክሰ ሻምፒዮናን ለማዘጋጀት ከ75 እስከ 80 ሚሊዮን ዶላር በጀት ይጠይቃል፡፡ 30ሺ ተመልካች የሚይዝና የኦሎምፒክ ደረጃ የሚያሟላ  በአትሌቲክስ መሰረተ ልማት ደረጃ 1 ሰርተፍኬት የተሰጠው ስታድዬም ያስፈልጋል። ባለ 6 መም የማሟሟቂያ ትራክ፤ ለጎዳና ውድድሮች ምቹ የሆነና በዓለም አትሌክስ ማህበር እውቅና የሚሰጠው የመወዳደርያ ጎዳና ማዘጋጀት ግድ ይሆናል።
የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናን የሚያስተናግደውን አገርና ከተማ የሚመርጠው የዓለም አትሌቲክስ ማህበር ምክር ቤት ነው። የአዘጋጅ አገር ምርጫ አስቀድሞ እንደነበረው ማመልከቻ አስገብቶ በመወዳደር አይደለም፡፡ ማስተናገድ የሚፈልግ አዘጋጅ አገር ጋር የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር ልዩ ምክርቤት በሚያደርገው ውይይት እና መግባባት መስተንግዶው ይፈቀድለታል፡፡ የዓለም አትሌቲክስ ማህበር በ2027 እኤአ የሚካሄደውን 21ኛ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ማስተናገድ ለሚፈልጉ የዝግጅት መመርያ ሰነድ በይፋ ያሰራጨው ከሰባት ወራት በፊት ነው። የአመልካች አገራት ምዝገባ ደግሞ ቀነ ገደቡ ከ3 ወራት በፊት አብቅቷል። ሻምፒዮናውን ለማስተናገድ የሚፈልጉ ከተሞች የመወዳደርያ ሰነዳቸውን እስከ መስከረም አጋማሽ ለዓለም አትሌቲክስ ማህበር ማስገባት አለባቸው።
ለሻምፒዮናው ድምቀት የሆኑ በጎፈቃደኞች
የዓለም አትሌቲክሰ ሻምፒዮና በበጎ ፈቃደኞች አገልግሎት ከፍተኛ ድምቀት እያገኘ መጥቷል። በ2017 እኤአ ላይ በለንደን 2913፤ በ2019 በዶሃ ኳታር 3000፤ በ2022 በኦሬጎን አሜሪካ 1585 በጎ ፈቃደኞቸ አለም ሻምፒዮናውን አገልግለዋል፡፡ በ19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ከ2000 በላይ በጎ ፈቃደኞች እንደሚሰማሩ ይጠበቃል።

Read 968 times