Saturday, 01 July 2023 00:00

ዓለማዊና መንፈሳዊ፣ ኃይማኖትና ኑሮ ምንና ምን?

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ጉዳዩ የማስታረቅና የማቃረን ጉዳይ ብቻ ባይሆንስ?


ሳይንስንና ኃይማኖትን፣ እውቀትንና እምነትን ለማስታረቅ፣ ብዙ ፈላስፎችና ጥበበኞች ለዘመናት ተመራምረዋል፤ ላይ ታች ወርደዋል። በዚያው ልክ፣ እርስ በርስ እንደሚቃረኑ ለማሳየት፣ ቅራኔያቸውም እንደማይታረቅ ለማስረዳት የደከሙ አዋቂዎች ብዙ ናቸው። ኃይማኖትና ሳይንስ፣ አንዱ በሌላኛው መቃብር ላይ ካልሆነ በቀር፣ አብረው ሊዘልቁ እንደማይችሉ ለማሳመን እልፍ ትንታኔዎችን ያቀርባሉ- በየጎራው ተሰልፈው ይወራወራሉ።
ለሺ ዓመታት የጎረፉ ፍልስፍናዎችና ሐተታዎች ወደ እልባት ካላደረሱት፣… በጣም ከባድ ጉዳይ ቢሆን ነው። ግን ደግሞ፣ ነገርዬው “የማስታረቅና የማቃረን ጉዳይ” ብቻ ባይሆንስ? ድራማና ዜና፣ ግጥምና ንግግር፣… በሆነ ነገራቸው ተቃራኒ ወይም ተጣማሪ ናቸው ብሎ መከራከር ይቻላል።
ከግጥም ውስጥ መረጃና እውቀትነፍ፣ ከዜና ውስጥም ጥበብና የመንፈስ መዝናኛን ለማጥለል ሁለቱንም ለማስታረቅ መሞከር አያቅትም። ነገር ግን፣ በሰው ሕይወት ውስጥ የየራሳቸው ቦታ ያላቸው የተለያዩ ገጽታዎች መሆናቸው ላይ ማተኮርስ አያስፈልግም ወይ?
ዓለማዊና መንፈሳዊ፣ ኃይማኖትና ኑሮ፣ እምነትና እውቀት፣… ከሰው ሕይወት ገጽታዎች ጋር አዛምደን ብናያቸውስ? “የእግዚሄርና የሰው ግንኙነት” በሚለው ሃሳብ ዙሪያ፣ የተለያዩ ዓለማዊና መንፈሳዊ ገጽታዎችን ለመመልከት ብንሞክርስ? መቼም፣ “የእግዚሄርና የሰው ግንኙነት” ሲባል፣… ብዙ ገፅታዎችን፣ ብዙ ትርጉሞችን ያቀፈ ነው። “አሜን” እና “ፅድቅ” የሚሉ ቃላትም፣ እያንዳንዳቸው በርካታ ገፅታዎችን የሚያዛምዱ በርካታ ትርጉሞችን እንደሚዋህዱ እናያለን።
የተፈጥሮና የሰው የዘወትር ግንኙነት - በእግዚሄርና በሰዎች ግንኙነት ይመሰላል።
“አሜን” የሚለው ቃል፣ “አዎን እውነት ነው” የሚል ትርጉም አለው፡፡
የሰው አእምሮ ከተፈጥሯዊ እውነታ ጋር ምን ዓይነት ግንኑነት ሊኖረው ይገባል? ለዚህ ጥያቄ  “አሜን” የሚለው ቃል ነው አጭሩ መልስ፡፡
የሰዎች ድርሻ፣ ተፈጥሯዊውን እውነታ አስተውለው፣ በአዎንታ አሜን ብለው መቀበልና እያገናዘቡ እውቀት መገንባት ነው። ማንገራገርና ማማረር፣… ምን ትርጉም አለው? ከተፈጥሮ ሕግ መሸሽ፣ ከእውነታ ጋር መጣላት፣ የትም አያደርስም።
አየር መንፈሱ፣ አሸዋ መንሸራተቱ፣ አለት መጠጠሩ፣… የተራራው ከፍታ፣ የሸለቆው ዝቅታ አልወደድንላቸውም ብንል ለውጥ የለውም፡፡ የምርጫ ጉዳይ አይደሉም፡፡ ውሃ መፍሰሱ፣ የባህር ጥልቀቱ ባይዋጥልን፣ በቅሬታ ብዛት እንቀይረዋለን? ከንቱ ልፋት ነው። ከአለት ጋር ለመላተም፣ ገደል መቀመቅ ለመግባት፣ በጎርፍ ተጠራርጎ ከጥልቅ ባሕህ ውስጥ ለመስመጥ፤ በበረሃ አሸዋ ለመቀበር ካልሆነ በቀር፣ ሌላ ውጤት የለውም።
ይልቁንስ በተፈጥሯዊው እውነታ ውስጥ ነው የሕይወት ቦታ፤ የመልካም አማራጮች መገኛ።
የተፈጥሮ ሕግ ዘላለማዊ ነውና፣ እውነታውን ማስተዋልና በአዎንታ አምኖ መቀበል፣ ዝንፍ ሳይሉ የእውነትን መንገድ መከተል፣ የሰዎች የመጀመሪያው የመልካም ምርጫዎች ሁሉ መሠረት ነው። ለዘላለማዊ እውነታ ለተፈጥሮ ህግ የኛ ምላሽ የአዎንታ መሆን አለበት። አሜን እንበል።
አሜን ማለት “አዎን፣ እውነት ነው” ማለት ነውና። እሙን ነው ነገሩ። ፅድቅ ማለትም እውነት ማለት ነው፡፡ እውነታውን መመስከር፣ እውነት መናገር ነው ጽደቅ ማለት። የአማን እና የፅድቅ ሌሎች ተዛማጅ ትርጉሞችንም አንተዋቸውም። እናመጣቸዋለን።
የሁሉም መነሻ ግን፣ እውኑን ተፈጥሮ በአዎንታ በአመኔታ መቀበል ነው። ከተፈጥሮና ከእውነታ ውጭ ሕይወትም መልካምነትም የለም - ጥፋት እንጂ። እግዚሄርን በአዎንታ፣ በሙሉ ልብ፣ በሙሉ ሃሳብና በሙሉ መንፈስ አምኖ መቀበል፣ መውደድና ማክበር እንደሚያስፈልግ መፅሐፍ ያስተምራል። ለምን?
አንዱ ምክንያት፣ የእግዚሄርና የሰዎች ግንኙነት፣… እውነት ላይ መመስረት እንዳለበት ለመግለጽ ይሆን? የእግዚሄር ስም “ያለና የሚኖር” በሚሉ ቃላት ተገልጾ ያለ! እውን የሆነውን ደግሞ “አዎ፤ እውነት ነው” ብሎ መቀበል ያስፈልጋል። የተፈጥሮ ሕግና የሰዎች ግንኙነት በዚህ ይመሰላል- ግን ይህ ብቻ አይደለም።
የወላጅና የልጆች፣ የአስተማሪና የተማሪዎች ግንኙነትንም ይመስላል - የሰውና የእግዚሄር ግንኙነት።
ሃይማኖታዊ ትረካዎችን ተመልከቱ፡፡ እግዚሄር ይመክራል፣ ይገስፃል። ይቆጣል፣ ይቅር ይላል። ያደንቃል፣ ይወቅሳል - እንደ ወላጅና እንደ አስተማሪ። ያለ ወላጅ ፍቅር ወይም ያለ አሳዳጊ እንክብካቤ፣ ሕፃናት በጤናና በደህና ማደግ አይችሉም።
 ያለ አዋቂና ያለ አስተማሪ፣ ያለ ፍቅርና ያለ እንክብካቤ፣ የሕጻናት ሕይወት ምን ሊሆን እንደሚችል አስቡት። ሕፃናትን በፍቅርና በተግሳጽ፣ በእንክብካቤና በክትትል ማሳደግ፣ “ለአቅመ ሰው” ማብቃት፣ አንድ የህይወት መሰረት ነው። ይህን ፀጋ ከማክበር ጋር ይመሳሰላል- የሰውና የእግዚሄር ግንኙነት። ይህም ብቻ አይደለም።
የሰው ልጅ ከሌሎች ፍጡራን የተለየና እጅግ ድንቅ የመንፈስ ፀጋ ተሰጥቶታል። ሕይወቱ ከባዶ አይጀምርም። በእርግጥ አዋቂ ጀግና ሆኖ አይወለድም፡፡ እናም በባዶ እጅ ሕይወትን ይጀምራል ብንል አልተሳሳትንም፡፡ ነገር ግን፣ እንደሌሎች እንስሳትም አይደለም፡፡
በቀድሞ ጥበበኞች የተዘጋጁ ነባር ፀጋዎች እንደ መነሻና መንደርደሪያ ይሆኑለታል፡፡
አለበለዚያ ሕይወቱ ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ የዘመናት ድግግሞሽ ይሆናል፡፡
 ከቀድሞ ጥበበኞች ዘንድ፣ ነባር እውቀቶችን ካልተማረና ነባር ሙያዎችን ካልተላመደ፣… ወደ ላቀ እውቀትና ወደ ተሻለ ኑሮ የመራመድ አቅም አያገኝም። እንደ ሌሎች እንስሳት ዘላለሙን ከባዶ የሚጀምር ቢሆን፣ የሰው ልጅ… የታሪክ ቅርስ ሽራፊ ወይም ቅንጣት የተስፋ ጭላንጭል አይኖረውም ነበር። ከትውልድ ትውልድ፣ የሰው ኑሮ ተመሳሳይ በሆነ ነበር - እንደ ሌሎች እንስሳት።
ካለፈው ዘመን ተምሮ ወደ ፊት ተሻሽሎ የመራመድና ወደ ላቀ ከፍታ የመጓዝ እድል ከሌለ፣… ታሪክና ቅርስ፣ ራዕይና ተስፋ አይኖርም። ደግነቱ ከባዶ አይጀምርም፡፡ ከቀድሞ ትውልዶች መልካም መልካሙን መማር ጅምሮችን ማሳደግ ይችላል፡፡ ትክክለኛ ሃሰሳብ ተቀብሎ ችግኞችን ኮትኩቶ እንደ ማፅደቅ ቁጠሩት፡፡
ነባር እውቀትንና ሙያን፣ ባሕልና ልማድን፣ ወላጅ አሳዳጊዎችንና ጥበበኛ አስተማሪዎችን ማክበር ያስፈልጋል። አሜን (ተገቢ ነው ትክክል ነው የሚል ትርጉም አለው፡፡)
በእርግጥ፣ የቀድሞ ጥበበኞችና ነባር ትምህርቶች፣ እንደ ተፈጥሮ ሕግና እንደ እውነታ አይደሉም።
ጥበበኞች ሊሳሳቱ፣ አስተማሪዎች ሊያዛቡ፣ ወላጆች ሊያጣምሙ፣ አሳዳጊዎች ሊያበላሹ ይችላሉ። ይህም ጉዳት አለው። ነገር ግን፣ ስህተታቸውና ጥፋታቸው እጅግ ጎጂ የሚሆነው ለምን እንደሆነ አስቡት? ለሕይወትና ለእድገት፣ ለሰው ልጅ ታሪክና ለስልጣኔ ጉዞ በጣም እጅግ ውድ አለኝታ መሆን ስለሚችሉ፣ ከጎደሉብን ከተበላሹብን እጅግ ክፉ ጉዳት ይሆኑብናል። ባይጎድሉብንና ባይበላሹብን ምንኛ መታደል ነው! ውድ ጸጋ ስለሆኑም ነው ክብር የሚገባቸው። የወላጅና የልጅ፣ የአስተማሪና የተማሪ፣ የታሪክና የትውልድ ግንኙነት፣… መልካምና የተቃና፣ የፍቅርና የተግሳፅ ግንኙነት መሆን አለበት። በምሳሌያዊ ዘይቤም፣ የሰዎችና የእግዚሄር ግንኙነትን ይመስላል ልንል እንችላለን። ይህም ብቻ አይለም።
ሰውና ህሊና
ሰዎች፣ ሁሉንም ነገር በስውር ከሚያውቅ ህሊናቸው ጋር የሚኖራቸው የሁልጊዜ ግንኙነት ይመስላል - የሰውና የእግዚሄር ግንኙነት። ለክፉም ለደጉም፣ ሌላ ሰው ቢያይም ባያይም፣ አመስጋኝና ወቃሽ ታዛቢዎች ባይኖሩም፣… ጥሩ ወይም መጥፎ ነገር በስውር ብንሰራ፣ ሕሊናችን በስውር ያያል፤ ይፈርዳል።
ውስጣዊው የሕሊናችን ተፈጥሮ ተገልጦ ባይታይም እንኳ፣ በስውር እየተመለከተ ይዳኛል። መልካምነትህን አይክድብህም፤ ክፋትህንም አይሸፍንልህም።
ጥሎ አይተውህም፣ ሸሽተህ አታመልጠውም።
እግዚሄር በስውር ያያል፤ በስውር ይከፍላል እንደሚባለው ነው።
ሰዎች ቢያምኑንም ባያምኑንም፣ የሚያውቅልህ ወይም የሚያውቅብህ ሰው ባይኖርም፣ እውነት ወይም ውሸት የተናገርክ ጊዜ፣ አእምሮህ ወይም ሕሊናህ በስውር ያውቃል። ከሕሊና የተሰወረ ነገር የለም።
ታዲያ፣ የሰውና የሕሊናው የሁልጊዜ ግንኙነት፣… የሰውና የእግዚሄር ግንኙነት ይመስላል ብንል ምን ስህተት አለው? ይህም ብቻ አይደለም።
ሰዎችና ዳኝነታቸው - የፍቅርና የፍትሕ ግንኙነት
የሰዎች የእርስበርስ ግንኙነት፣ የመንግስትና የዜጎች፣ የከተማ ዳኛና የከተማ ነዋሪዎች… ከእነዚህ ግንኙነቶች ጋር ይመሳሰላል - የእግዚሄርና የሰው ግንኙነት። የፍትሕና የፍቅር አስፈላጊነት ላይ የተመሰረተ መሆን ይኖርበታልና ግንኙነታቸው።
የሰዎች ግንኙነት፣ መረጃና ሃሳብ የመለዋወጥ (የመማማር)፣ በስራና በኑሮ የመተባበር (የመረዳዳትና የመገበያየት)፣ በሕይወትም የራስ ሃላፊነትን የመወጣትና ራስን አክብሮ፣ የሌሎችንም ብቃት የማድነቅ፣ አርአያነትንም የማክበር የፍቅር ግንኙነት መሆን አለበት - በአንድ በኩል።
በሌላ በኩል፣ ራስን ጭምር፣ ሁሉንም ሰው፣ እንደየስራውና እንደየባሕርይው እንዳኛለን ማለት፣… የፍትሕ ግንኙነት ነው። በዚህ ይመሰላል- የሰውና የእግዚሄር ግንኙነት።
“የሕይወት መዝገብ” - ሁሉንም ነገር ይመዘግብልናል፤ ይመዘግብብናል!
የሰው እና የእግዚሄር ግንኙነት፣… በሰው እና “በሕይወት መዝገብ” መካከል ባለው ግንኙነት ጋር ይመሰላል።
በተፈጥሮ፣ የሰው አእምሮ፣… የእለት ተእለት ሃሳቡንና ተግባሩን ይመዘግባል። የግል አእምሯችን፣ እንደየ ምርጫችን የሕይወት ውሏችንን የምንዘውርበት፣ መንገዳችንን የምንነድፍበትና የምንጓዝበት መሣሪያ ነው። ግን ደግሞ፣ የሕይወት መዝገባችንም ነው - አእምሯችን። እንዳይመዘግብ ማድረግ አይቻልም። አእምሯችን መዝጋቢ ነው። መዝገብም ነው። መዝገብ ማጥፋት፣ በፎርጅድ መተካት፣ ባሰኘን ጊዜ መሰረዝ መደለዝ፣ ቆርጦ መቀጠል አይቻለንም ብለናል´ኮ።
copy - paste,… cut - replace,… undo - redo,… post - delete፣… የእለት ተእለት ሃሳብና ተግባር ላይ፣… እነዚህን አማራጮች መሞከር እንችላለን። ማሰብ አለማሰብ፣ ማድረግ አለማድረግ፣… የእያንዳንዷ የሕይወት ደቂቃና ቅፅበት ምርጫዎች ናቸው። መዝገብ ውስጥ መስፈራቸው ግን አይቀሬ ነው ተባብለናል።
ይመዘግብልናል። ሳይመዘገብልን የሚቀር መልካም ነገር አይኖርም።
ይመዘግብብናል። ሳይመዘገብብን የሚያመልጥ መጥፎ ነገር የለም።
ማሰብ አለማሳባችን፣ ማድረግ አለማድረጋችን፣ ከነምንነታቸው አእምሯችን መመዝገቡ፣ የምርጫ ጉዳይ አይደለም። ይመዘግባል።
በዚህም ማንነት ያንጻል ወይም ያፈራርሳል።
ባሕርይን ያጎድፋል ወይም ያነጻል፤ ያጣምማል ወይም ያቃናል።
የተጣመመውን ያደነድናል ወይም የተቃናውን ያጸናል።
ታዲያ፣ ይህ ድንቅ የሰው ተፈጥሮ፣ ግሩም የፍትሕ ፀጋ አይደለምን? የፈላስፋውን አባባል ጠቅሰን እንደነበር አስታውሱ። ቸመልካም ስራ፣… አንተ ብትረሳው እንኳ የሚመዘግብ አለ… ይላል ፈላስፋው ወልደሕይወት። “Sense of life” ትለዋለች ፈላስፋዋ፡፡ የሰራነውን ሁሉ ማስታወስ አንችልም ማለት ከመዝገብ ያመልጣል ማለት አይደለም፡፡ በከንቱ የሚባክንም የለም።
የሕይወት መዝገብ፣ ሁሉንም እየመዘገበ እንደየስራችን ማንነታችንን ያበለፅግልናል። እንዲህ አይነት ሰው ፃድቅ ይባላል፡፡ አሜን፣ ተገቢ ነው እንደ ማለት ነው፡፡
ክፋት ከሰራንም ከብዛቱ የተነሳ ብንረሳው እንኳ፣ ከመዝገብ ውስጥ አይጠፋም፡፡ በጥቁር ነጥቦች ብዛት የሕይወት ገፃችን ይጠቁራል፡፡
የሕይወት መዝገብ፣ ማምለጫ የሌለው የፍትሕ ዳኛ ነው - “የእጃችሁን ታገኟታላችሁ” የሚለን። አንድም ሳያመልጠው ይመዘግብብናል።
እንደየጥፋታችን ልክም የግል ማንነታችን ይረክሳል፤ የእኔነት መንፈሳችን ይሟሽሻል።
“ፈሪሀ እግዚሄር” የምንለው ሃሳብ ከዚህ ጋር የተዛመደ ገጽታ አለው። ፈሪሃ እግዚሄር  “የጥበብ መጀመሪያ ነው” ተብሎ የለ! የዛሬ ሃሳባችንና ድርጊታችን፣… ውሎ አድሮ፣ በነገ ማንነታችንና በነገ የአገራችን ባሕል ላይ፣ ለክፉም ለደጉም፣ ውጤትና መዘዝ እንደሚኖረው ካልተገነዘብን፣ ወደ ጥበብ ደጃፍ አልደረስንም።
ለእውነታ በመታመን፣ ሕይወትንም በማክበር፣ በየቀኑ በሃሳብና በተግባር የምናከናውናቸው ፍሬያማ ጥረቶችን የሚመዘግብ፣ በዚህም ላይ የየእለቱን እየጨመረ የሚገነባ የተፈጥሮ ፀጋ ባይኖረን ኖሮ፣… አስቡት።
አስቡት? አእምሯችን “መዝጋቢም፣ መዝገብም” ባይሆን ኖሮ፣ እንዴት ተደርጎ ይታሰባል? “መማርና ማገናዘብ”፣ “መለማመድና መፍጠር” የምንላቸው ነገሮች ትርጉም ያጣሉ። በየእለቱ ከባዶ የሚጀምር ደንዛዛ ወይም ቀበዝባዛ አዙሪት ይሆን ነበር - የሰው ሃሳብና ኑሮ። እውቀት፣ አስተዋይነትና ቋንቋ፣… የሙያ ልምድ፣ ብልኀትና ጥበብ የሚባል ነገር አይኖረንም - አእምሯችን የሕይወት መዝገብ ባይሆን ኖሮ።
የግል ማንነትና የእኔነት መንፈስ፣ የአገር ባሕልና ሥርዓት፣ ቀና አድናቆትና የወዳጅነት ፍቅር፣ የወደፊት ራዕይና ተስፋ፣ የሕይወት ትርጉምና ጣዕም የምንላቸው ነገሮች አይኖሩንም - አእምሯችን የየእለቱን ሃሳብና ተግባር የማይመዘግብ ቢሆን።
ደግነቱ፣ ይመዘግባል። መዝገብም ነው።
“የተፈጥሮ ፀጋ፣ የተፈጥሮ ፍትሕ” ብንለው አይበዛበትም - “የእግዚሄር በረከት፣ የእግዚሄር ፍትህ” እንደማለት።በዚያው ልክ፣ እያንዳንዷ ውሸትና ሽንገላ፣ የምንሰራት ሸፍጥና በደል፣ የምንፈፅማት ጥቃትና ጥፋትም ከመዝገብ አታመልጥም። አንዲትም ሳትሰወር፣ አንድም ተሸሽጎ ሳይደበቅ ሁሉም ይጻፋሉ። በዚሁም ላይ የየእለቱ እየተጨመረና እየተመዘገበ፣… አእምሮ ይደፈርሳል፣ ይወሳሰባል፣ ይጨልማል። ሕሊና ይዶለዱማል፤ ይጎድፋል። ማንነት ይበላሻል፤ ከጊዜ ወደ ጊዜም ጠማማው ይባስኑ እየተጠማዘዘ ይደነድናል። ማምለጫ የሌለው “የተፈጥሮ ዳኝነት፣ አይቀሬ ፍትሕ”፣… ልንለው እንችላለን። “የእግዚሄር ፍትሕና ዳኝነት” እንደማለት ነው።

Read 717 times