Monday, 03 July 2023 08:46

የአብደላ ዕዝራ ሂሶች ጠባያት

Written by 
Rate this item
(0 votes)

(ዕዝራ እንዳይረሳ - በሰባት ዓመቱ)
አብደላ ዕዝራ ከ1980ዎቹ መጀመሪያ አንሥቶ እስካረፈበት ግንቦት 2008 ዓ.ም. ድረስ፣ በተለያዩ የሥነ ጽሑፍ መድረኮች (በአብዛኛው መጽሔቶች እና ጋዜጦች) ላይ በሚያቀርባቸው ሂሳዊ ንባቦቹ የምናውቀው እና ሃያሲ የሚልን “ማዕረግ” ባልተጻፈ ስምምነት ከሰጠናቸው አንድ ኹለት ሰዎች መሐል የምናገኘው ሃያሲ ነበር፡፡
ባለቅኔ እና ሐያሲው ዮሐንስ አድማሱ ከ1933 -1960 በተጻፉ የአማርኛ የፈጠራ መጻሕፍት ላይ በብስጭት በጻፈው ትችት መግቢያ ላይ፣ “ኂስ ለሥነ ጽሑፍ ሕይወት መጠበቂያ ዓይነተኛውና ፍቱን መድኃኒቱ ነው፣” ይላል፡፡ ዕዝራ ይህንን ሥነ ጽሑፉን በሕይወት የማቆየት ሚና በገዛ ፈቃዱ መውሰዱን ከሂሳዊ ንባቦቹም ኾነ ከመጻሕፍት ዳሰሳዎቹ  እንገነዘባለን፡፡ ዕዝራ በርቅቀታቸው፣ በቋንቋ ውበታቸው፣ በምሰላቸው አንብቦ ያደነቃቸው ድርሰቶች ለምን ሂሳዊ ንባብ ተነፈጉ የሚለው ቁጭት ከሥነ ጽሑፍ ፍቅሩ ጋር ተደምሮ በየሳምንቱ በቸርነት ሂሳዊ ንባቦችን ለመጻፍ ያተጋው ይመስለኛል፡፡
በእዝራ የሂስ መርህ አንድን ሥነ ጽሑፍ በሕይወት የሚያቆየውም ይኹን ከተሳካለትም የሚያሳድገው፣ ደራሲው አብዝቶ ስላፈራው አረም ሲሸማቀቅ እና ሲጸጸት እንዲኖር መውቀስ ሳይኾን፣ በኩንታል አረም መሐል ያፈራትን ስንዴ ለከርሞ እንዲያበዛት ማበረታታት ይመስላል፡፡ ምንም እንኳን “ኂስ ጉድለትንም ጥራትንም መግለጫ ጥበብ” ቢኾንም ዕዝራ ግን የድርሰቶቻችንን ድክመት እያደበዘዘ፣ በቀጣይ ሥራዎቻችን ልናጎለብታቸው የሚገቡትን ጥቂት ብቃቶቻችንን አድምቆ ማሳየትን መርጧል፡፡
ዕዝራ የድርሰቶቻችን ብርታቶች ላይ ማተኮሩ በህትመት ያገኘናቸው የፈጠራ ድርሰቶች በቁጥር እንጂ በኪነታዊ ብቃታቸው የሚደነቁ አለመኾናቸውን አጥቶት አይደለም፡፡ ያም ኾኖ ዘጋቢዎቹ፣ የማይናደፉቱ (በፍዝ ቋንቋ የተጻፉቱ)፣ ወይም እሳቦቶቻቸው እንደ ተን ፈጥነው የሚጠፉብን ግጥሞች ላይ ጊዜውን፣ ስሜቱን ምናቡንም ሲያባክን አናገኘውም፡፡
ዕዝራ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎችን ከመመዘን ይልቅ መፈከርን በመምረጡ አመጸ ብንልም፤ ለግጥምም ኾነ ለዝርው ድርሰቶች የሚቀበላቸውን የሥነ ጽሑፍ ደንቦች ሲያጸናም እናገኘዋለን፡፡ ያም ኾኖ ግን ከጥራዝ ነጠቅ ንባብ ተነሥተን ግጥም እንዲህ መኾን አለበት፣ ልቦለድ እንዲያ መኾን የለበትም እንደምንለው እንዳብዛኞቻችን ድምዳሜ አይሰጥም፤ የሚጽፈው ደንቦቹ በየጊዜው፣ በየአውዱ ስለሚቀያየሩለት/በት የፈጠራ ሥራ እንደኾነ አይዘነጋም፤ ይልቅ በተዘዋዋሪ እንዲህ ቢኾን ይሻላል በሚል ትሕትና እና በድግግሞሹ ሥር በሥር ደንብ ሲያስተዋውቅ እና ሲያስለምድ ቆይቷል፡፡ ለምሳሌ፣ የግጥምን የትርጉም አሻሚነት (ambiguity) አንዱ ገጣሚ ጋ በማድነቂያነት፣ ሌላው ጋ በጉድለት መጠቆሚያነት በተደጋጋሚ ከማንሣቱ እና ከማስረዳቱ የተነሣ አሻሚነትን ገጣሚያን ሊያስቡበት የሚገባ የግጥም አላባ መኾን አለበት የሚል ደንብ ማበጀቱን እናያለን፤ እንዲያውም የግጥም የትርጉም አሻሚነት ግጥሙን አንባቢው ልብ ውስጥ ያከርመዋል የሚል አቋሙን ጽሑፎቹ ውስጥ ደጋግመን እናነባለን፡፡የእዝራ የሂስ ስልት የደራሲውን ተቋማዊ ህልውና ክዶ፣ የግጥሙንም ይኹን የልቦለዱን ትርጉም ከድርሰቱ ላይ ብቻ መፈለግ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ደራሲው ምን ለማለት ፈልጎ ነው ብሎ የድርሰቱን አቅም ከመገደብ ይልቅ ድርሰቱ ምን ይነግረኛል ብሎ ሥራውን የመመርመሩን አካሔድ እንደሚከተል ለመረዳት በተለይ ጥልቅ ሂሳዊ ንባቦቹን ማንበብ ብቻ በቂ ነው፡፡
ዕዝራ በዚህ ሂሳዊ አተናተን እንደተመሰጠ ከሚያሳዩን የሂሱ ጠባያት አንዱ አንድን ድርሰት ብቻውን ሲፈክረው አለማግኘታችን ነው፡፡ ብዙ ጊዜ የሚያተኩረው ግጥሞች ላይ እንደመኾኑ፣ አንድን ግጥም ሲተነትን ግጥሙን መድብሉ ውስጥ ካሉ ግጥሞች ጋር ያናብባል፤ ግጥሙን በዚያ መድብል ውስጥ ካልተካተቱ የገጣሚው ሌሎች ግጥሞች ወይም ዝርው ድርሰቶች ጋር እና ከሌሎች ድርሰቶች ጋር ያናብባል፡፡ የዕዝራ ሀያሲነት ከጥልቅ ንባብ የተገኘ መኾኑን ከምናይባቸው የሂሱ ጠባያት ይሄ አናባቢነቱ አንዱ ነው፡፡
በዕዝራ ሂሳዊ ንባቦች ላይ አልፎ አልፎ አንዱን ግጥም ከሌሎች የተሻሉ ግጥሞች ጋር በማናበብ ያንንን ግጥም በተሻሉት ግጥሞች ትከሻ ላይ አቁሞ ለማሳየት የመሞከር አዝማሚያ አይቻለኹ፡፡ ይህንን ማድረግ ደከም ያለውን ገጣሚ የተሻለ ነገር ይዞ እንዲቀርብ ያበረታታው ይኾናል፤ የዕዝራም ምክንያት ይሄ ይመስለኛል፤ ነገር ግን በተቃራኒው እንዲህ ያለው ሂስ ደካማው ደራሲ ደረጃውን አውቆ፣ ድክመቶቹን ለይቶ ለመሻሻል እንዲሞክር ከመገፋፋት ይልቅ ልቡን አሳብጦ እዚያው ድክመቱ ላይ እንዲከርም ሊያደርገውም ይችላል፡፡
ሌላው የዕዝራ ንባቦች ጠባይ፣ ሂሱ ከሥነ ጽሑፍ ሥራው ተነጥሎ እንዳይታይ ያሰበበት ይመስል፣ ለሂሳዊ ድርሰቶቹ ውበት መጠንቀቁ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ የእሱ ሂሳዊ ንባቦች ከሚተነትናቸው ድርሰቶች በላይ በዘይቤ በታሸ፣ ከሰርክ መግባቢያ ከፍ ባለ ቋንቋ እና በአመስጣሪው የላቀ ምናባዊነት ተጽፈው ይገኙና ከሂስነታቸው ይልቅ ወደ ፈጠራ ድርሰትነት ያዘነብላሉ፡፡ ለወትሮው ሐያሲን ፈራጅ፣ ደራሲን ተከሳሽ አስመስሎ የሚያሳየውን አካሄድ ትቶ፣
ራሱን የፈጠራ ሂደቱ አካል ማድረጉን ከጽሑፎቹ እንረዳለን፡፡በርግጥ ይሄ በፈጠራ  ሒደቱ የመሳተፍ ነገር መልካም ቢኾንም ሐያሲው ሚዛኑን ካልጠበቀ የሚያሔሳቸውን ሥራዎች ውበት ከማሳየት ይልቅ በራሱ ምናብ የመመሰጥ፣ ወይም ድርሰቶቹን አላቅማቸው የማንጠራራት አደጋ ሊኖረው ይችላል፡፡ ኹለቱንም ዓይነት ችግሮች አልፎ አልፎ በዕዝራ ሂሶች ውስጥ አላየኹም አልልም፡፡ (በአንባቢ ልቤ “ይሄ ዕዝራ አኹንስ አበዛው!” ብዬ የተበሳጨኹባቸው ሂሶች አሉ፡፡)
በአጠቃላይ፣ ዕዝራ ሂስ ጎድሎብን ሳለ፣ ተከታታይ የግጥም ሂስ ደግሞ ጠፍቶብን ሳለ ግጥምን ያክል አመጸኛ የድርሰት ዘውግ ለማጥናት እና ለመተንተን መነሳቱን አይተን፣ ለሥነ ጽሑፍ ፍቅሩ ሲል “”አዲስ ስርዓት” የመትከልን፣ ግጥሙን መልሶ የመፍጠርን ያህል ፈታኝ” ኃላፊነትን እንደወሰደልን ልንረዳ ይገባል፡፡ እዝራ ይህን የባህል እና ሥነ ጽሑፍ ተቋማት የሸሹትን ኃላፊነት በግሉ ወስዶ፣ ከማንም ሽልማትም ይኹን ክፍያ ሳይጠብቅ፣ በትጋት ይወጣልን ጀምሮ ነበር፡፡
ዕዝራን መዘከር፣ የዕዝራን የሂስ ትጋት፣ ለሥነ ጽሑፋችን ያለውን ምኞት፣ በሃያሲነቱ እና በሥነ ጽሑፍ ፍቅሩ ይዟቸው የነበሩትንም ዕቅዶች በከፊልም ቢኾን በማሳካት ቢገለጥ የሚሻል ይመስለኛል፡፡
በመጨረሻም፣ ዘመኑ የሂስ ባህል ያልዳበረበት እንደመኾኑ፣ እንዲህ እንደ ዕዝራ ያሉ ብርቅ ሐያስያን ሲገኙ፣ ሥራዎቻቸው የሂስ እና የምርምር ዕድል ሊነፈጉ ስለማይገባ፤ የሥነ ጽሑፍ ተማሪዎች እና ተመራማሪዎች ሂሱን ለመተንተንም ይኹን ለመሔስ (በሂስም ላይ ሂስ አለበትና) ሥራዎቹን አጥንተው የዕዝራን አስተዋፅዖዎች በጥልቀት ቢያሳዩን ደግ ነው ብዬ አምናለኹ፡፡ ለእዝራ ኅልፈቱ ዕረፍቱ እንዲኾንለት እመኛለኹ፡፡
(ቴዎድሮስ አጥላው)

Read 1281 times