Saturday, 01 July 2023 00:00

ሁሌም መማር አታቋርጡ!!

Written by 
Rate this item
(0 votes)

እውነቱ ምን መሰላችሁ? ከምትገምቱት በላይ  አዕምሮ፣ ችሎታና አስተዋይነት ተችሯችኋል - በቀሪው ዕድሜያችሁ  ልትጠቀሙበት ከምትችሉት በእጅጉ የላቀ፡፡ እናንተ ከምታስቡት በላይ  በእጅጉ ብልህ ናችሁ፡፡ የማታሸንፉት መከራ፣ የማታልፉት መሰናክል፣ የማትሻገሩት እንቅፋት የለም፡፡
የማትፈቱትም ችግር እንዲሁ፡፡ አዕምሮአችሁን ተጠቅማችሁ የማታሳኩት አንዳችም ግብ የለም፡፡
አዕምሮአችን ከጡንቻችን ጋር ይመሳሰላል፡፡ የሚገነባውና  የሚዳብረው ስንጠቀምበት ብቻ ነው፡፡ የሰውነት ጡንቻዎቻችሁን ለማዳበር ማንቀሳቀስ እንዳለባችሁ ሁሉ፣ አዕምሮአችሁንም ለመገንባት የአዕምሮ ጡንቻዎቻችሁን ማሰራት አለባችሁ፡፡
ብዙ በተማራችሁ ቁጥር የበለጠ የመማር አቅም ታዳብራላችሁ፡፡ ብዙ ስፖርት ስትሰሩ የተሻለ የአካል ብቃት እንደምትጎናጸፉት ሁሉ፣ ራሳችሁን የበለጠ ለህይወት ዘመን ትምህርት በሰጣችሁ ቁጥር፣ በቀላሉና በፍጥነት ብዙ የመማር ክህሎት ታዳብራላችሁ፡፡
በ21ኛው ክ/ዘመን ወሳኙ ነገር የማያቋርጥ ትምህርት ነው፡፡ በያዛችሁትም ሙያ ሆነ በሌላው ዘርፍ ስኬታማ ለመሆን ከእናንተ የሚጠበቀው ትንሹ ነገር፣ ራሳችሁን ለህይወት ዘመን ትምህርት ማዘጋጀት ነው፡፡ የሙያችሁ ተማሪ ለመሆንና በትምህርት ለመግፋት እንዲሁም በቀሪው ህይወታችሁ የተሻለ ብቃት ለማዳበር ዛሬውኑ ወስኑ፡፡
በህይወት ዘመናችሁ ሁሌም ከመማር እንዳትነጠሉ የሚረዱ ወሳኝ ተግባራትን እንመልከት፡፡ የመጀመሪያው ወሳኝ ጉዳይ፣ በእያንዳንዱ ቀን ከመኝታችሁ ስትነሱ ከ30 – 60 ደቂቃ ማንበብ ነው፡፡ የሰውነት እንቅስቃሴ ለአካል ብቃት እንደሚያስፈልገው ሁሉ፣ ንባብም ለአዕምሮ ብቃት እንዲሁ ነው፡፡
 በቀን ለአንድ ሰዓት ስታነቡ፣ በሳምንት አንድ መጽሐፍ አነበባችሁ ማለት ነው፡፡ በዓመት 50 መጻሕፍት ይሆናል፡፡ በአሥር ዓመታትስ?  500 መጻሕፍትን ጠጥታችኋል፡፡ አንድ አማካይ አዋቂ ሰው በዓመት ከአንድ መጽሐፍ በታች ስለሚያነብ፣ እናንተ በቀን ለአንድ ሰዓት ማንበብ ስትጀምሩ በሙያ ዘርፋችሁ የማይታመን ለውጥ ታመጣላችሁ፡፡
በቀን ለአንድ ሰዓት በማንበብ ብቻም በሙያችሁ እጅግ የተካናችሁ፣ ብቁና ከፍተኛ ደሞዝ ተከፋይ ትሆናላችሁ፡፡ የህይወት ዘመን ትምህርት ሁለተኛው ወሳኝ ጉዳይ፣ በድምጽ የተሰናዱ (Audio) ትምህርታዊ ፕሮግራሞችን ማዳመጥ ነው - በተለይ ከቦታ ወደ ቦታ በመኪና ስትዘዋወሩ፡፡
 አንድ አማካይ ሰው በዓመት ከ500 – 1ሺ ለሚሆኑ ሰዓታት በመኪናው ውስጥ ይቀመጣል፡፡ በሳምንት ከ12 – 40 ለሚሆኑ ሰዓታት ማለት ነው፡፡ ወይም ደግሞ ከሦስት እስከ ስድስት ወራት የሚሆን የሥራ ጊዜ በመኪና ውስጥ ያጠፋል እንደ ማለትም ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ከአንድ ወይም ከሁለት የዩኒቨርሲቲ የትምህርት ሴሚስተር ጋር እኩል ነው፡፡
እናም መኪናችሁን ተንቀሳቃሽ ዩኒቨርሲቲ ልታደርጉት ትችላላችሁ፡፡ ምንጊዜም በኦዲዮ የተሰናዱ ትምህርታዊ ፕሮግራሞችን ሳትከፍቱ መኪናችሁን ፈጽሞ አታንቀሳቅሱ፡፡ የህዝብ ትራንስፖርት ተጠቃሚ ከሆናችሁም፣ ስፖርትና ሙዚቃ በሞባይል ስልካችሁ  እንደምታዳምጡት ሁሉ፣ትምህርታዊ ፕሮግራሞችንም እንዲሁ ማድመጥ ትችላላችሁ፡፡
ለህይወት ዘመን ትምህርት ሦስተኛው ወሳኝ ጉዳይ፣ በሙያ መስካችሁ የተሻላችሁ ለመሆን የሚረዷችሁን ማናቸውንም ኮርሶች፣ ሴሚናሮች፣ ዎርክሾፖች መውሰድ ነው፡፡ መጻሕፍት፣ ኦዲዮ ፕሮግራሞችና ሴሚናሮች በመቶዎች የሚሰሉ ሰዓታትንና በሺዎች የሚገመቱ ብሮችን ያድናሉ፡፡ ተመሣሣይ የስኬት ደረጃን ለመጎናጸፍ ያስፈልግ ከነበረው የብዙ ዓመታት ልፋትና ድካምም ያተርፋሉ፡፡
የዕድሜ ልክ  ተማሪ ለመሆን ዛሬውኑ ቆርጣችሁ ተነሱ፡፡ በሙያ ዘርፋችሁ ላይ በሚያመጣው የላቀ ለውጥ በእጅጉ ትደነቃላችሁ፡፡

Read 1381 times