Monday, 03 July 2023 08:54

ሰማዕቱ ፓትርያርክ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ምድር፣በኢትዮጵያውያን
ጳጳሳት የተሾሙ ሁለተኛው ፓትርያርክ


የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስቀድሞ በቅዱስ ሐርቤ (፩ሺ፩፻፲፯-፩ሺ፩፻፶፯ ዓ.ም.) በኋላ በዐፄ ዮሐንስ ራብዓዊ (፩ሺ፰፻፷፫-፩ሺ፰፻፹፫ ዓ.ም.) ከሊቃውንቷ መካከል መርጣ ጳጳስ ለመሾም ለእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን ደጋግማ ያቀረበችው ጥያቄ፣ በ፳ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አጋማሽ ላይ መልስ አግኝቷል፡፡ በዚህም መሠረት ለመጀመሪያ ጊዜ በንግሥተ ነገሥት ዘውዲቱ ዘመን በ፲፱፻፳፩ ዓ.ም. ግንቦት ፳፭ ቀን ከራስዋ ሊቃውንት መካከል አራት አበውን መርጣ ካይሮ ላይ በቅዱስ ማርቆስ ካቴድራል በብፁዕ ወቅዱስ ዮሐንስ ፲፱ኛ አንብሮተ እድ እንዲሾሙ አድርጋለች፡፡ እንዲሁም በ፩ሺ፱፻፳፪ ዓ.ም. የግብጹ ፓትርያርክ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ስለ ዕጨጌ ገብረ መንፈስ ቅዱስን ሳዊሮስ ጳጳስ ብለው ሾመዋቸዋል።
ይህ በዚህ እንዳለ ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ለመያዝ እንዲሁም ቤተ ክርስቲያንዋንም ካቶሊክ ለማድረግ፣ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሊቃውንትንም ለማጥፋት ፲፱፻፳፰-፲፱፻፴፫ ዓ.ም. ኢጣሊያ ከአድዋ ሽንፈቱ ፵ ዓመት በኋላ በድጋሚ በኢትዮጵያ ላይ ወረራ አደረገ፡፡ በዚህም ጊዜ ብዙ አብያተ ክርስቲያናትና ቅርሳቅርሶች ተቃጠሉ፤ ንዋያተ ቅድስት ተዘረፉ፤ ጳጳሳት፣ ካህናት፣ መነኮሳትና ዲያቆናት ምእመናንም ተገደሉ፡፡
ይሁን እንጂ ቤተ ክርስቲያናችን ይህን የግፍ ዘመን በትዕግሥት አሳልፋና እንደገና ተደራጅታ ለሕዝቡ አገልግሎቷን ቀጥላለች፡፡ ከጠላት ወረራ በኋላም ቀደም ሲል ከተሾሙት አምስት ኢትዮጵያውያን ጳጳሳት መካከል ሦስቱ ከዚህ ዓለም በሞት ስለተለዩ በአንድ ጳጳስ ብቻም ብዙ መንፈሳዊ ተግባርን ማከናወን ስለማይቻል፣ እንደገና ሐምሌ ፲፰ ቀን ፲፱፻፵ ዓ.ም. ካይሮ ላይ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ዮሳብ ዳግማዊ አንብሮተ እድ አምስት ኢትዮጵያውያን ጳጳሳት ተሾሙ፡፡ ከሊቀ ጳጳስ ቄርሎስ ግብጻዊ ሞት በኋላም ጥር ፮ ቀን ፲፱፻፵፫ ዓ.ም. ብፁዕ አቡነ ባስልዮስ ሊቀ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ተብለው በፓትርያርክ ዮሳብ ዳግማዊ ተሠየሙ፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዚህ አኳኋን ከኀይል ወደ ኀይል ከእድገት ወደ ተሻለ እድገት እየተራመደች ቆይታ ፲፱፻፶፩ ዓ.ም. ሰኔ ፳፩ ቀን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ የኢትዮጵያ የመጀመሪያው ፓትርያርክ ሆነው ተሾሙ፡፡
እነሆ ይህ ራስን ችሎ በራስ የመተዳደር መብትና ሥልጣን ሊገኝ የቻለው በግርማዊ ቀዳማዊ ዐፄ ኀይለ ሥላሴ ከፍተኛ ጥረት በቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃውንት ድጋፍ፣ ፍላጎትና በእስክንድርያውያንም ስምምነት መሆኑ ምን ጊዜም ታሪክ የማይረሳው እውነት ነው፡፡
ብፁዕ አቡነ ባስልዮስ ጥቅምት ፫ ቀን ፲፱፻፷፫ ዓ.ም ከዚህ ዓለም ድካም ሲያርፉ ቅዱስ ሲኖዶስ መጋቢት ፳፰ ቀን ፲፱፻፷፫ ዓ.ም ላይ ባካሄደው የፓትርያርክ ምርጫ ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ተመረጡ፡፡
ግንቦት ፩ ቀን ፲፱፻፷፫ ዓ.ም በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ምድር በኢትዮጵያውያን ጳጳሳት፣ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ካህናት እና ምእመናን ጸሎት በተካሄደ በዓለ ሲመት ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ሁለተኛው የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ሆነው ተሾሙ፡፡
ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ከድቁና እስከ ፓትርያርክነት ቤተ ክርስቲያንን በመንፈሳዊ ቅናት፣ ትጋትና ተጋድሎ እያገለገሉ በነበሩበት ወቅት በ፲፱፻፷፰ ዓ.ም ታሰሩ፤ የደርግ ሥርዓተ መንግስት ለሦስት ዓመታት አስረው ካቆዪዋቸው በኋላ በ፲፱፻፸፩ ዓ.ም በፈፀሙባቸው ኢፍትሃዊ ግድያ ሐምሌ ፯ ሰማዕት ሆኑ፡፡
ስለብፁዕነታቸውን የመንፈሳዊ ሕይወት ተጋድሎ በዝርዝር ማቅረብ የሚቻል ቢሆንም የጽሁፌ መነሻ “ቀዳማዊ ቴዎፍሎስ ፓትርያርክ” የሚለው የአቶ ታምራት አበራ መጽሐፍ አትኩሮቴ ስለሆነ በጥልቀት ገብቼ ከመዘርዘር ተቆጥቤያለሁ፡፡
“ቀዳማዊ ቴዎፍሎስ ፓትርያርክ” በሚለው ርዕስ ስያሜ አጭር ፅሁፍ ለማዘጋጀት የፈለኩበት ምክንያት የመፅሃፉን ይዘት ለመገምገም ወይም ክፍተቱን ለመሙላት ወይም ጥንካሬውን ለመናገር ሳይሆን መፅሃፉ አሁን ላነሳነው ቅዱስነታቸውን በአካል ለማናውቀው ግን ሥራቸውንና ታሪካቸውን ለምናነበው ታናናሽ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች መፅሃፉ ከያዛቸው መሰረታዊ ቁም ነገሮች ውስጥ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስን ታሪክና ሥራዎች ማንበብ ብቻ ሳይሆን ለዚህ ሁሉ ሥራቸው መሰረታዊ መነሻ፣ ሃይማኖታዊም ይሁን አስተዳደራዊ፣ መዋቅራዊም ይሁን ቀኖናዊ መሠረት ምንድን ነው የሚለውን ጥያቄ እንድናነሳ መንገድ ስለሰጠን ነው፡፡
እርግጥ ነው መፅሃፉ “ብፁዕ  ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስን በጣም በቅርበት እንድናውቃቸው የሚያደርግ፣ ከስማበለው ወይም አሉታ ታሪክ ለየት ባለ መንገድ በቅርበት የሚያውቋቸው፣ አብረዋቸው የሠሩ፣ የቅርብ አማካሪዎቻቸውን መረጃ በማድረግ መጻፉ ተአማኒነቱንና ታሪካዊ ፋይዳውን ይጨምረዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ግን አሁን እኔ ቀጥዬ የማነሳቸውን ለምን እንዲህ ሆኑ፣ ለምን እንዲህ አደረጉ፣ ለምን እንዲህ ወሰኑ የሚሉ ጥያቄዎችን ከጽንሰ ሐሳባዊ መሰረት ለመዳሰስ የሚጋብዝ አቀራረብ አለው፡፡
ሰማዕታት ለምን መከራ ተቀበሉ ሲባል በጣም ቅርብ የሆነው መልስ በጣም ታማኝና ለእምነታቸው ጽኑ ስለሆኑ ነው የሚለውን እናገኝ ይሆናል፡፡ በዚሁ ሳንቆም በጥልቀት ከመረመርን ደግሞ ስለማያልፈው የመንግስተ ሰማያት ርስት ሲሉ፣ ስለ እውነተኛው የክርስቶስ ፍቅር ሲሉ፣ ስለ ትክክለኛ ኦርቶዶክሳዊ ሃይማኖታቸውና ቤተ ክርስቲያናቸው ሲሉ የሚሉ በርከት ያሉ መልሶችን እናገኛለን፡፡ ይሄም እንዲሁ ነው፤ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ለምን እንደዚህ ዘመን ተሻጋሪ ሥራዎችን በብዙ መከራዎችና እንቅፋቶች፣ ባልተደላደለ ሁኔታና በአስቸጋሪ ፈታኝ ወቅቶች፣ በአጭር ግዜ ውስጥ ሠሩ ሲባል መልሱ ሁሉንም ማሳተፉ አይቀርም፡፡ የእኔም አላማ አሁን ሁሉንም ለመመለስ ሳይሆን፣ በተለይ ለእኛ ለታናናሽ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ልዩ ትርጉም ስላለው፣ በዚሁ ጉዳይ እንድንጨነቅና እንድናስብ ለበለጠ አገልግሎትም እንድንተጋ ለማድረግ ነው፡፡
ከማንኛውም ሥራ በፊት ሐሳብ አለ፤ በተግባር የምናየው ሥራ የሐሳቡ ውጤት ነው፡፡ ሐሳብ የሌለውና ከተግባሩ ጋር ያልተገናዘበ ሥራ ምናልባት ወይ የተቀዳ ነው ወይም በግብታዊነት የሚሰራ የይስሙላ ድካም ነው፡፡ ከማንኛውም ምርጥ ተግባር ጀርባ ዕቅድ፣ ዲዛይንና መነሻ ምክንያት አለ፡፡ ያለእቅድ የተሰራ ቤት፣ ያለትልም የተዘራ ሰብል፣ ያለምህዋር የሚሄድ መርከብ መድረሻቸውም አይታወቅም፤ ሂደታቸውም ጥበብ የጎደለው ነው፡፡ ይህን ማለት የምንፈልገው የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ሥራዎች ጀርባ ለሥራው ሁሉ መነሻ አስደናቂ የሆኑ ጥበቦችና ዘመን የማይሽራቸው በኦርቶዶክሳዊ ተዋሕዶ እምነት ቀኖና፣ አስተዳደርና ዶግማ ላይ የተመሠረቱ አስተሳሰቦች እንዳሉ ለመግለጽ ነው፡፡ከሁሉ በፊት ግን የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ፓትሪያርክ የአስተዳደር ጽንሰ ሐሳብን ለማተት የሚከተሉትን መሰረታዊ መነሻዎች ማየት ተገቢ ነው፡፡
ቅዱስነታቸው ሁለተኛው ፓትሪያርክ የሆኑት በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ላይ መፈንቅለ መንግስት ከተደረገ በሁዋላ ንጉሡ በእርጅና እድሜያቸው በርከት ያሉ ተቃውሞዎች እየመጡ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ችግሮች እየሰፋ በነበረበት ወቅት ነው፡፡ምንም እንኳን ቤተ ክርስቲያኒቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በታሪኳ የሯስዋ የሆነ ፓትሪያርክ ከእርሳቸው በፊት ቢሾሙም አስተዳደሩ ከንጉሱ ሞግዚትነት አልወጣም፤ የታላላቆቹ አድባራትና ገዳማት ገበዞች ሹማምንት ነበሩ፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ በገንዘብም ይሁን በሰው ኃይል ያላትን ሀብት ለመጠቀም የአካባቢና የማእከላዊውን የንጉሠ ነገሥቱን መብት ጠብቃ ነው፡፡ በፓትሪያርክ ሥልጣኑም ቢሆን የንጉሠ ነገሥቱ ቀጥተኛ ጣልቃ ገብነት የተከበረ ነበር፡፡የመጀመሪያው ትልቅ እርምጃ የግብጻውያንን ቀጥተኛ ጣልቃ ገብነት በሹመታቸው አስወግደዋል፡፡ በዚህም በፓትሪያርክነት ሁለተኛው ፓትሪያርክ ይሁኑ እንጅ በሃገራቸው በመሾም የመጀመሪያው ፓትሪያርክ ናቸው፡፡ በመቀጠልም በልዩ ልዩ አጋጣሚዎች ዋና ሐሳቦች የነበሩት በሳቸው ግዜ የነበረችውን ቤተ ክርስቲያን ማገልገል ብቻ ሳይሆን የወደፊቱንም የማየት ብቃት ነበራቸው (ዶ/ር አግደው ረዴ)
እነዚህን ጉዳዮች በሚገባ ለማጤን ከዚህ ቀጥሎ ያሉትንና በአቶ ታምራት መጽሐፍ ከተጠቀሱት አንጻር ብቻ እናያለን፡፡ ቅዱስነታቸው፡-
የቤተ ክርስቲያን አንድ ወጥና ማእከላዊነቱን የጠበቀ ሆኖ በየቦታ ራስ ገዝ በመሆን ኃላፊነቱን የሚወጣ አስተዳደር በሐዋሪያት ሥርዓት ላይ የተመሰረተ “የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ” ሠርተዋል፤ ይህም የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ከማንም ሞግዚትነት የወጣ፣ ራሱን የቻለ፣ ምንም አይት አስተዳደራዊ ድርቶን (ደባልነት) የሌለው በጣም ብቁና ዘመናዊ የሆነ፣ ሁሉን አቀፍ በመሆን እንደተፈለገው መስፋትና መጥበብ የሚችል፣ ለሀብት ቁጥጥር፣ ለሰው ኃይል ሥምሪት ለመዋቅራዊ ወጥነት፣ ለአስተዳደራዊ ተጠያቂነት፣ ለሕዝባውያንና ለካህናት የቤተ ክርስቲያን ሁለንተናዊ ተሳትፎ (አሳታፊ) የሆነ ፍጹም መንፈሳዊ የሆነ መዋቅርን መሥርተዋል፡፡ የዚህ መዋቅር መሠረታዊ ጽንሰ ሐሳብ ቤተ ክርስቲያን በራሷ ብቁ የሆነች፣ የራስዋ የሆነ ሐዋሪያዊ መዋቅር ያላት፣ ከዓለማዊ አስተሳሰብ ነጻና የተደራጀች ዘመን የማይሽረው አደረጃጀት እንዳላት ከማመንና ያንንም ከመተግበር የተነሳ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ በተለይም ይህንኑ አደረጃጀት ወደ ተግባር ለመለወጥ የነበሩበትን ፈተናዎች በጽናት ለመለወጥ ያሳዩት ቁርጠኝነት፣ አሁን የምናየውን የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ለማትረፍና ቃለ ዐዋዲውን ለአራተኛ ጊዜ እንዲሻሻል ምክንያት ሆኗል፡፡
ቅዱስነታቸው ለዓለም አቀፍ ግንኙነት ልዩ ትኩረት ነበራቸው፤ አሁን እኛ በተለያየ ሁኔታ የቤተ ክርስቲያንን ዓለም አቀፍ ግንኙነት ለማሳካት ጥረት ሲደረግ ሁልጊዜ እንደ መነሻ የሚታየው የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ጥረት ነው፡፡ በእሳቸው ተሳትፎ ቤተ ክርስቲያን የበርካታ ዓለም አቀፍ ግንኙነቶች ንቁ ተሳትፎ ከመረጋገጡ ባሻገር በአንዳንዶቹ ዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ የመሥራች አባል በመሆኗ በኩራት እንድንናገር አድርጎናል፡፡
 ከዚህም አልፎ በተለይ በኦርቶዶክሱ ዓለም ውስጥ በነበሩት ዓለም አቀፍ ግንኙነቶች የመሪነት ወይም የአቻነት ሚና እንድትጫወት አድርገዋል፡፡
ቅዱስነታቸው ለወንጌል አገልግሎት እና ለአብነት ትምህርት ልዩ ቦታ ነበራቸው፡፡ ስብከተ ወንጌልና ሐዋሪያዊ ተልእኮ መቋቋም፣ ሐዋሪያዊ ድርጅት፣ የሬዲዮ ሥርጭት፣ የልዩ ልዩ ሕትመቶች ተጠናክሮ መኖር መሠረቱ እሳቸው ነበሩ፡፡ በዚህም ብዙ ልንል ብንችልም ዋናው ጉዳይ የቅዱስነታቸው አስተሳሰብ የቤተ ክርስቲያንን ተቀዳሚ ተልእኮ ማስቀደማቸውን ማየት ሲሆን፤ ይህም ዋናው ምንጩ ቀደም ሲል ለመግለፅ እንደተሞከረው ለቤተ ክርስቲያን ማዕከላዊ ተልእኮ የሰጡት ትኩረትና የቤተ ክርስቲያን ተልእኮ ለመንፈሳዊ ተልእኮ ቅድሚያ የሚሰጥ፣ መንፈሳዊው ተልእኮው ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ከሰጡት ትኩረት ነው፡፡
ቅዱስነታቸው የወጣቶችን የቤተ ክርስቲያን ተሳትፎ በተመለከተ ከሰንበት ትምህርት በወቅቱ ከነበሩ የወጣት እንቅስቃሴ አንፃር በርከት ያሉ ጉዳዮችን ልንማር እንችላለን፡፡ በየቦታው የነበሩ እንቅስቃሴዎችን መዋቅራዊ በማድረግ፣ ወጣቶች በቤተ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ሥርዓትና ቀኖና ጠብቀው እንዲሳተፉና በአብነት ትምህርት ቤቶች፣ በገዳማትና በገጠር አብያተ ክርስቲያናት ከሚማሩና ከሚደክሙ ወጣቶች በተጨማሪ በከተማ ያደጉ በዘመናዊ የትምህርት ተቋማት የሚማሩ ወጣቶች የቤተ ክርስቲያንን መዋቅር አውቀው፣ የቅዱሳት መጻሕፍት ሚስጥር፣ የቅዱሳንን ገድልና ድርሳናት፣ የቤተ ክርስቲያንን ታሪክ መሠረተ እምነትና ቀኖና እንዲያውቁ ለማድረግ ብዙ ደክመዋል፡፡ ውጤቱም ዛሬ በመላው ኢትዮጵያና በመላው ዓለም የተዘረጋው የሰንበት ትምህርት ቤቶች መዋቅር ነው፡፡ የዚህ ተግባር መሰረታዊ ፅንሰ ሐሳብም አንደኛው ቤተ ክርስቲያን ተተኪ ትውልድን ያለማቋረጥ እንድታፈራ፣ ያም ትውልድ መዋቅሯንና አስተዳደሯን የሚያውቅ፣ የሚጠብቅና የሚያስጠብቅ፡፡ ከቅጥሯ ሳይርቅ የሚማር እንዲሆን ለማድረግ ሲሆን በተለይ ከዘመናዊ ትምህርት ተጽዕኖ ራሱን ጠብቆ በዘመናዊውም በመንፈሳዊውም ትምህርት የበለፀገ ትውልድ ለመቅረጽ የተደረገ ነው፡፡ቅዱስነታቸው ቤተ ክርስቲያን የራሷ ገቢ እንዲኖራት፣ በልመና እንዳትተዳደር፣ በማህበራዊ ግልጋሎት ንቁ ተሳታፊ እንድትሆን የገቢ ምንጭና የልማት ተቋማትን በመገንባት ለገዳማትና ለአብነት ትምህርት ቤቶች ድጋፍ እንዲሆኑ በማድረግ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ ለዚህም የቤቶች ግንባታ፣ የልዩ ልዩ የልማት ተቋማት እንደ ጎፋ ዕደ ጥበባት ያሉ የትንሣኤ ማተሚያ ቤት ያሉ ተቋማት መመሥረታቸው ነው፡፡ የዚህ ተግባር ዋና ፅንሰ ሐሳብም ቤተ ክርስቲያን ራሷን ካልቻለችና በዓለማውያን አስተሳሰብ ቅኝ ግዛት ከወደቀች፣ ግለሰቦችና ቡድኖች ወይም የዓለማዊ አስተሳሰቦችና የቁሳዊ ግንዛቤዎች ጥገኛ እንዳትሆን ለማድረግ ነው፡፡
ቅዱስነታቸው ቤተ ክርስቲያን በሀገራዊ ልማት፣ በስደተኞች፣ በማህበራዊ ግልጋሎት ቀጥተኛ ተሳታፊ እንድትሆን አድርገዋል፡፡ በዚህም ከሀገራቸው መንግስት ጋር ብቻ ሳይሆን ከዓለም አቀፍ መንግሥታዊ የሆኑ (እንደ የተባበሩት መንግሥታት)፣ መንግሥታዊ ካልሆኑ እንደ ልዩ ልዩ የበጎ አድራጎት ተቋማት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዲኖራት በማድረግ፣ ከመንፈሳዊ ግልጋሎቷ ጎን ለጎን ማኅበራዊ ተሳትፎዋም ጉልህ እንዲሆን አድርገዋል፡፡ ለዚህም የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን የመሰሉት ተቋማት መቋቋምን ስናይ በዋናነት ግን ቤተ ክርስቲያ ባለችበት ኅብረተሰብ ውስጥ ተጽዕኖ ፈጣሪ የምትሆነው በአባላት ብዛትና ባላት ሀብት ብቻ ሳይሆን፣ በምታደርገው ታማኝነት ያለው ማኅበራዊ ተሳትፎም ጭምር መሆኑን ያሳዩ ናቸው፡፡
የቅዱስነታቸው አስተዳደራዊ የመዋቅርና የአደረጃጀት ጽንሰ ሐሳብም ከወቅቱ ጋር አብሮ የሚሔድ፣ ታዳጊና ሒደቱ በግልጽ የሚታይ፣ ተጠሪነቱና ተጠያቂነቱ በግልጽ የታወቀ፣ ከነቀፋ የራቀና ለቁጥጥርም ይሁን ለማንኛውም ግምገማ የማያሻማ፣ የሥራ ድርሻውና የሥራ ክፍሉ ተጠሪነት በግልጽ ተለይቶ የታወቀ፣ ተደራሽና ገስጋሽ የሆነ ድርብርብ ወይም ድግምግሞሽ የሌለው፣ ለዐሠራር የማያስቸግር፣ እርስ በርሱ ተደጋጋፊ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሉዓላዊና የራሱን ክብር የጠበቀ፣ መፍትሔ ሰጪነት (መፍትሔ ፈላጊነት ሳይሆን)፣ በራሱ ባለቤትነት የጸና፣ ለሙያ ትኩረት የሰጠ፣ የቤተ ክርስቲያንን መንፈሳዊም ሆነ ማኅበራዊ፣ ልማታዊና ሀገራዊ ድርሻ በአግባቡ እንድትወጣ፣ አስተዳደሯና መዋቅሯ በምንም አይነት መለኪያ አንድን ተግባርም ሆነ ኃላፊነት ለመወጣት ብቁ የሆነ ሆኖ ራሱን ከወቅታዊ ሁኔታዎች ጋር በማገናዘብ መጠንከርና ከተለዋዋጩ የዓለም መመሪያ ራሱን ጠብቆ በመንፈሳዊ ሕልውና መቆም የሚችል መዋቅርን ሠርተዋል፡፡
በአጠቃላይ የአስተዳደር መመሪያቸው የሚያሳየው ቅዱስነታቸው ያላቸውን ጥልቅ መንፈሳዊነት፣ የመንፈሳዊ አመራር ብቃትና ያላቸውን የቀኖና ዕውቀት ነው፡፡ ከዚህም ባለፈ ያላቸውን መንፈሳዊ ልምድና ዕውቀት ወደ ተግባር ለመለወጥ የሚፈጥሯቸው መንገዶችም ይህንኑ ብቃታቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ ለማጠቃለል፤ የቅዱስነታቸው የመዋቅርና የቤተ ክርስቲያን አስተዳደርና የመዋቅር አስተሳሰብ መርሆዎች የቤተ ክርስቲያንን ማዕከላዊነት የጠበቀ፣ ለቤተ ክርስቲያን ጥቅምና እድገት ያደላ፣  የቤተ ክርስቲያንን ሉዓላዊነት ያስከበረ፣ ለስብከተ ወንጌልና ሐዋሪያዊ ተልእኮ፣ ለመንፈሳዊ ተጋድሎ የሚያደላ፣ ራስን በመቻል ላይ ያተኮረ፣ ሁለንተናዊነት፣ ሉዓላዊነት፣ አሳታፊነት ሁሉን አቀፍነት ያለው፣ ወቅታዊነት ወይም የወቅቱን የዓለምን ሁኔታ በማየት ለዓለማዊ ወይም ዘመነኛ ሞገድ የማይበገር፣ የወደፊቱን መተንበይ የሚችል፣ ፈጣንና ተደራሽ የሆነ፣ የቤተ ክርስቲያንን መንፈሳዊም ሆነ ጥበባዊ ሀብት፣ ትውፊትና ቅርስ በመጠበቅ ላይ የተመሠረተ፣ ከግል አስተሳሰብ ወይም ከግል ጥቅም የጸዳ፤ የተለየ ነው ለማለት ይቻላል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ራስዋን ችላ በራስዋ ፓትርያርክ መተዳደር ከጀመረችበት ጊዜ ጀምሮ ስድስት ፓትርያርኮችን ሾማለች፡፡
 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአሁኑ ጊዜ በሀገር ውስጥ ፶፭ አህጉረ ስብከት ያሏት ሲሆን፣ በውጭ ሀገርም ፴ የሚሆኑ አህጉረ ሰብከትን በኢየሩሳሌም፣ በካሪቢያን ደሴቶችና በላቲን አሜሪካ፣ በአሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ በአፍሪካ፣ በካናዳና በሌሎችም አሏት፡፡ በአጠቃላይ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሌለችበት የዓለም ክፍል የለም። የተከታዮችዋ ምእመናን ቍጥርም ከሀገሪቱ ከፍተኛ የሕዝብ ብዛት የያዘ ሲሆን በርካታ ገዳማት አድባራትና አብያተ ክርስቲያናት፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እንዲኖራት መሰረት ከጣሉ የቤተ ክርስቲያን አንጋፋና የቁርጥ ቀን አባቶች መካከል ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ - ሰማዕቱ ፓትርያርክ ዋነኛው ናቸው፡፡ የሰማዕቱ የብፁዕ አባታችን በረከታቸው ረድኤት ከሁላችን ጋር ይሁን!!! አሜን፡፡
(መምህር ዳንኤል ሰይፈሚካኤል)

Read 2059 times