Saturday, 08 July 2023 00:00

የድምፃዊ ብስራት ሱራፌል “ማለፊያ” አልበም ሀምሌ አጋማሽ ላይ ይለቀቃል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 “ወጣ ፍቅር ወጣ” በተሰኘው የመጀመሪያ ነጠላ ዜማው በአጭር ጊዜ ውስጥ ተቀባይነትን ያገኘው ድምፃዊ፤ የግጥምና ዜማ ደራሲ ብስራት ሱራፊል አበበ ሁለተኛ ስራ የሆነው “ማለፊያ” አልበም ሀምሌ 14 ቀን 2015 ዓ.ም ለአድማጭ እንደሚቀርብ ተገለፀ፡፡ ይህንን የገለፀው በሙዚቃ ኢንዱስትሪው በስፋት የሚንቀሳቀሰውና የብዙ ሙዚቀኞችን ስራ በማስተዋወቅ የሚታወቀው “ኤላ ቲቪ” ከድምፃዊው ብስራት ሱራፌልና ከግጥምና ዜማ ደራሲው ዓማየሁ ደመቀ ጋር በመሆን በትናንትናው ዕለት ረፋድ በሀገር ፍቅር ቴአትር በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው፡፡ በቀደመው የመጀመሪያ አልበሙና እንደ “ሆንሽብኝ የቤት ስራ” ባሉት ነጠላ ዜማዎቹ እንዲሁም ለተለያዩ አንጋፋና ወጣት ድምፃዊያን በሰራቸው ግጥምና ዜማዎቹ ተቀባይነትና አድናቆትን ያገኘው ብስራት ሱራፌል አልበሙን ሰርቶ ለማጠናቀቅ 4 ዓመታትን እንደወሰደ ገልፆ በአጠቃላይ የአልበሙ ስራ ላይ በርካታ እውቅ ባለሙያዎች መሳተፋቸውም አብራርቷል፡፡ በቅንብሩም አበጋዝ ክብረወርቅ ሺዎታ፤ ታምሩ አማረ፤ ሚኪ ሀይሌ፤ ሱራፌል የሺጥላ፤ ፋኑ ረዳቦና ስማገኘሁ ሳሙኤል፤ የተሳተፉ ሲሆን በግጥም በኩል ዓማየሁ ደመቀ ፍሬዘር አበበ ወርቁ፤ ምልዕቲ ኮሮስ፤ ወንደሰን ይሁብ እና አብዲ ሲሳተፉ ሁሉንም ዜማ ራሱ ብስራት ሱራፌል መስራቱም ተገልፃል፡፡ አርቲስት ብስራት ሱራፌል አዲሱን አልበሙን ካስመረቀ በኋላ በአዲስ አበባ፣ በክልል ከተሞችና በተለያዩ የውጪ ሀገራት ኮንሰርቶችን በመስራት ከአድናቂዎቹ ጋር በመድረክ እንደሚገናኝ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ተብራርቷል፡፡

Read 1676 times