Saturday, 15 July 2023 20:48

ኃሰሳ ሀዲስ አለማየሁ (ክፍል ሁለት)

Written by  አብዲ መሐመድ
Rate this item
(2 votes)

  “--ቀን መኝታዬ ላይ እውልና ማታ ነው የማነበው፡፡ ጀምበር ከጠለቀች በኋላ ቁጭ ብዬ በየዕለቱ የሚወጡትን ጋዜጦች አነባለሁ። አንድ ወዳጄ አለ በእድሜም ይበልጠኛል። ጤና ስላለው ካዛንቺስ አካባቢ ወጣ ብሎ አንዱ ጥግ ቁጭ ብሎ አላፊ አግዳሚውን ሲያይ ይውላል፤ አሁን እርሱን ሳስብ ያንን እድል ባለማግኘቴ ይቆጨኛል፡፡ ከእኔ ጥርሶች መካከል አንዱም የሉም፡፡ እንዲህ በወተት እያራስኩ ነው የምመገበው፡፡ ባለፈው ጥቅምት 92 ዓመት ሆነኝ፡፡ የአንድ ሰው እድሜው መርዘሙ ማለፊያ የሚሆነው ለራሱም ለወገኑም የሚበጅ ሲሆን ነው፡፡ በግሌ ብዙ ምዕራፍ ሮጫለሁ፡፡ ጤና ስለሌለኝ አሁን ማረፍ ነው የምሻው፡፡ ዘመዶቼ ሁሉ አርፈዋል፤ እኔ ብቻ ነኝ በህይወት ያለሁት። ከዚህ በኋላ የምፈልገው በፀጥታ ኖሮ ማለፍ ነው፡፡…“ (አይ ፐሲዜ ገጽ.37)
 ደራሲ ሀዲስ አለማየሁ ዕድሜ ተጭኗቸው ከቤት መውጣት አቁመው በነበረበት የዘመን አመሻሽ መዳረሻቸው ወቅት እንደመታደል ሆኖ፤ እድል ገጥሟቸው ልምዳቸውን ለመጋራት ከመኖሪያ እልፍኛቸው ዘልቀው በግንባር የጎበኟቸው የዚያን ጊዜ ወጣት ደራሲያን ጥቂት አይደሉም፡፡ ከእነዚህ መካከል ዘነበ ወላ አንዱ ሆኖ በተዋበ ብዕሩ “አይ ፐሲዜ” ውስጥ ትውስታውን አኑሮልናል፡፡…ሀዲስን መፈለግ ቀላል ኃሰሳ አይደለም፡፡ መዳፌ ላይ ያሉ ሁለት ስራዎቻቸውን ተመርኩዤ “ታላቁን ደራሲ ፍለጋ“ ብሎ በይፋ ማወጅ፤ ለአፋልጉኝ ቀርቶ በወጉ ለመንጠላጠል እንኳን ዋስትና አይደለም። ለድፍረት የቀረበ አጓጉል ቅኝታዊ ቅርበት በሚል ሊያስተችም ይችላል፡፡ ከልቦለዶቻቸው ባሻገር የትዝታ ፍለጋቸውን፣ የተረት አሻራቸውን ተከትለን ብንሄድ የሚተውት ዱካ አጥጋቢ ቅሪት ሆኖ በሙላት እሳቸውን አያሳይም፡፡ ምንም እንኳን ትዝታ እውነተኛ ታሪክ ቢሆንም፣ የአርበኝነት ገድላቸው አመዝኖ የህይወት ታሪክ ለመሰኘት የሚጎድሉት ብዙ መሰረታዊ፤ ግለ-ታሪካዊ የአወቃቀር ጉድለቶች አሉት፡፡ ስለዚህ ሰውየውን ሀዲስን በይበልጥ ለመጠጋት የሌሎች ከያንያንን ትውስታ መቆፈሩ ሳይሻል አይቀርም። ቢያንስ ከማፈግፈግ ታድጎ ዳሰሳችንን ለማዋዛት ያገለግለናልና፡፡
የዘነበን  የወግ ስብስብ እዚህ መግለጥ እሚበጀውም ለዚህ ነው፡፡ በዚያ ላይ የቅርብ ጊዜ ነውና በቀዳሚነት ሁነኛ ግብአት ሆኖ እንደ ማመሳከሪያ ሊወሰድና ሊጠቀስ የሚበቃም ነው፡፡ ሀዲስ በ1906 ዓ.ም በጎጃም ክፍለ ሀገር፤ በደብረ ማርቆስ፣ በጎዛምን ወረዳ እንዶዳም ኪዳነ ምህረት መወለዳቸው ይነገራል፡፡ የቤተ-ክህነትን ትምህርት እዚያው በእንዶዳም እያሉ እስከ ፆመ ድጓ ዘልቀዋል፡፡ የቅኔውን ትምህርት በደብረ ኤልያስ ከአባታቸው ዘመዶች አካባቢ በመቀመጥ ከተማሩ በኋላ ወደ ደብረ ወርቅ እንዲሁም ወደ  ዲማ በማምራት ትምህርታቸውን አጠናቅቀዋል። በመቀጠልም አዲስ አበባ በዘመናዊ ትምህርት፣ በመምህርነት፣ በአርበኝነት፣ በግዞትና በዲፕሎማትነት… አገራቸውን በማገልገል ዘልቀዋል፡፡ ዘነበ በ1984 የወጣችውን “ፍካሬ” መጽሔትን ዋቢ አድርጎ እንዳሰፈረው፤ ሀዲስ ውብ ልጅነታቸውን በመጽሔቷ የመጀመሪያ ዕትም እንዲህ አውስተዋል፡፡…“በዚህ በእረኝነት እድሜያችን ነው ትልልቆቹ የሰሩትን እያስመሰልን የምንጫወተው፡፡ የእርፍ አያያዝን፣ የጠመንጃ አጎራረሱንና አጣጣሉን፤ በአጠቃላይ የማህበራዊ ተሳትፎን በየገጹ እንደቴአትር ሚና ይዘን እየሰራን መጪውን ህይወት ሆነን የምንገኘው!”::…
በርግጥ ሀዲስ የፖለቲካው አካል ሆነው በመስራት፤ ቢሮክራሲው ከልጅነት እስከ እውቀት ብዙ ዘመናቸውን ወስዶባቸዋል፤ በአያሌውም በድሏቸዋል፡፡ ይህም በስነጽሁፍ ጉዟቸው “… የላቀ ደራሲ እንዳልሆን አግዶኛልም- ገድቦኛልም“ ብለው ያምኑ ነበር፡፡ ይሁንና ግን ከደራሲ ሰዋዊ አዛኝ ማንነታቸው ይልቅ ፖለቲካዊ ሰውነታቸው ያን ያህል የሚጫናቸው ምሁር አይደሉም፡፡ ለዚህም ነው በአንድ ወቅት እንደ ዘነበ ሁሉ ገጣሚ ታገል ሰይፉም፣ ኢህአዴግ ወደ አዲስ አበባ የገባ ሰሞን ሊጠይቃቸው ጎራ ብሎ እንዲህ ሲሉ ምክር መለገሳቸው፤...“ታገል ይኸውልህ እኔ አሁን በሰራሁበት ስራ ላይ የላቀ ደራሲ እንዳልሆን ያገደኝ፣ በቢሮክራሲው ውስጥ ገብቼ የፖለቲካው አካል ሆኜ መስራቴ ነው፤ በአያሌው በድሎኛል፡፡ አሁን እነዚህ ሰዎች ገቡ (ኢህአዴጎችን ነው) የርዕዮተ ዓለማቸው ማራመጃ የሚያደርጉት ወጣቱን ትውልድ ነው። አንተ ደግሞ ተስፋ ያለህ ደራሲ ስለሆንክ እንዲች ብለህ የፖለቲካ ድርጅታቸው አባል እንዳትሆን፤ ከሆንክ አንደኛውን ለተሰጥኦህ ሙሉ ጊዜ ሳይኖርህ ማለፍ አለ” …
ፖለቲከኛው ሀዲስ፣ በወረራው ሳቢያ ሞሶሎኒ ከሂትለር ጋር ለመተባበርና  ለማባበል ኢትዮጵያን እንደ እጅ መንሻ መስዋዕት አድርጎ ማቅረቡን በማስረጃ አስደግፈው ለመንግስታቱ ማህበር አጋልጠዋል፡፡ የአለም መንግስታት ማህበር የሚባለው ሀያላን መንግስታት ወደየግባቸው ለመድረስ የፖለቲካ ጨዋታቸውን የሚጫወቱበት ሜዳ መሆኑንና አለም-አቀፋዊ ህግ የሚባለውም እንደ ብሄራዊ ህግ ስልጣን ላላቸው ሀይለኞች ብቻ የፖለቲካ መሳሪያ መሆኑን እንዲሁ ተንትነውና አመሳክረው አሳይተዋል፡፡…“ቆይ ግን አሁን ከሞላ ጎደል ማህበሩ ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በጦርነት ይዛ ቅኝ ግዛትዋ ለማድረግ እንዴት መብት ይሰጥዋታል። እነዚህ የተባሉት ምክንያቶች መብት የሚሰጡ ከሆነ ከኢጣሊያ የተሻለ የጦር መሳሪያና የበዛ የጦር ሰራዊት ያላቸው አገሮችም ኢጣሊያን በጦር ሀይል ይዘው ቅኝ ግዛታቸው ለማድረግ መብት ይኖራቸዋል ማለት እኮ ነው! ወይም በሌላ አነጋገር አለማችን ደካማው ከብርቱ፣ ትንሹ ከትልቁ ጋር የሰው ማህበር መስርተው የሚኖሩበት መሆኑ ቀርቶ ደካማውን ብርቱው፣ ትንሹን ትልቁ የሚበላሉበት ያራዊት ማህበር ይሁን ማለት ነው!”(ገጽ.31)!”…ስመጥሩ መምህር ክቡር ዶክተር ሀዲስ አለማየሁ፤ ዘመናዊ ሰው፣ ዘመናዊ አስተሳሰብ የነበራቸው ዲፕሎማትና ደራሲም እንደመሆናቸው…በሀገርና ህዝብ ጉዳይ ላይ ካላቸው ግንዛቤ አንፃር፣ አገራዊም ሆነ አህጉራዊ ችግሮችን ቀድመው የተረዱም፣ የሚረዱም ምሁር ነበሩ፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና ም/ሚኒስትር ሆነው በሰሩባቸው ወራት እያደገ የመጣው የአሜሪካና የሌላ አገር ጥገኛ መሆን ሀገሪቷን ለአደጋ እያጋለጣት መሆኑን በግልጽ በመናገራቸው በስፍራው አልቆዩም፡፡ በይበልጥ ለውጥ ያሳዩበታል ተብሎ በነበረው የትምህርት ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስቴርነታቸው…ዓመት እንኳን አልቆዩበትም። በኢትዮጵያ ት/ቤት ውስጥ ያሉት ተማሪዎችን ብዛት፤ ከአብዛኛው የአፍሪካ ሀገራት ቁጥር ማነሱን በግልጽ አሳውቀሀል! ተብለው ይህን ለመቀየር ያወጡት እቅድና በጀት ተሰርዞ፣ እሳቸውም ከስፍራው መነሳታቸው ተዘግቧል፡፡ ሀዲስ በስልጣን በቆዩበት ዘመን አያሌ ያልተሳኩ ሙከራዎቻቸው በአጥኚዎች በቂውን ያህል ተተንትነዋል፡፡ ሌሎችም በሀገሪቷ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ ከፍተኛ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ ሀሳቦቻቸውና ምክራቸው ሰሚ በማጣቱ ብቻ ሀገሪቷ በሂደት ለመመሰቃቀል በቅታለች፡፡ ለሀገራቸው ነጻነትና ደህንነት፣ ለህዝቡ የተሻለ ህይወት ከመታገል ባሻገር ሀሳባቸውን በአሰራርና በአመራር ብቃት የሚተረጉሙ ተራማጅ ምሁር ነበሩ፡፡ ስለሆነም የትምህርት ተቋማት እንዲከፈቱ፣ የጥበብ ማህበራት እንዲበራከቱ፣ እየረዱም-እያበረታቱም…እሚችሉትን ሲያደርጉም ሆነ ሲያግዙ መቆየታቸው የቱን ያህል አገራቸውን ይወዱ እንደነበር  በጉልህ የሚያሳይ ነው፡፡ የባዕድ ተገዢ መሆን ያለውን የከፋ ቀንበር ጠንቅቀው የሚያውቁት ሀዲስ፣ ይህንንም በትያትሮቻቸው፣ በተረቶቻቸው ህዝቡ እንዲገባው በማድረግ አንድም ሲታገሉ፣ አንድም ሲያታግሉ…ሲያነቁም ሆነ ሲያነቃቁ ኖረዋል፡፡
በዚህ በክፍል ሁለት ተረቶቻቸውን በ“ተረት ተረት የመሰረት” ውስጥ ከመመልከታችን በፊት በትያትሮቻቸው ያደረጉትን አስተዋጽኦ  ከነበረው ተጨባጭ የዘመኑ ፖለቲካዊ ሁነት አንፃር እንዲሁም ከወረራው ክስተት ጋር አዛምደን ጥቂት እንቃኝ፡፡… ኢትዮጵያ በወረራው ዚቅ ውስጥ ተዘፍቃ ሳለች ከሹማምንቱና ከመኩዋንንቱ ጋር በመምከርና በመነጋገር፣ ለዚህ እንደ አንድ አማራጭ ወሳኝ ሆኖ ያገኙትና የተስማሙበትም፤ ቴአትር በማዘጋጀት ህብረተሰቡን ለመቀስቀስ በመሳሪያነት ከማዋል ባሻገር ለልዩ-ልዩ አላማ፣ ለታሰበው ግብ ሊሆን በሚችል መልኩ ህዝቡን ማንቃት ነበር፡፡ ይህ በታቀደበት ጊዜ ሀዲስ በቂና የተለያዩ የቴአትር ጽሁፎች በእጃቸው ነበር፡፡ ደራሲው ቀደም ሲልም አብረዋቸው ከነበሩት የወቅቱ ባለስልጣናት ራስ እምሩ ሀይለስላሴና ወልደጊዮርጊስ ወልደ ዮሐንስን መሰል ባለስልጣናት መካከል በአዲስ አበባ ቴአትር ሰርተው በማሳየት በቂ ልምድና ተሞክሮ ስለነበራቸው፣ ይህንን እውቀትና ክህሎት ኢትዮጵያ ለገጠማትና ለገባችበት አስከፊ ውጥረቶች፣ ለተፈጠረው ፈታኝ ሁኔታ እንዲስማማ አድርገው፣ በቂ የማሻሻያ ለውጦች አድርገውለት በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚደርስና ለእይታ የሚበቃ ቴአትር በማሰናዳት ተጠቀሙበት፡፡ ቴአትሩ ወቅታዊነት እንዲኖረውና እንዲላበስ ከሽነውና አሻሽለው ለተፈጠረው ሁኔታ እንዲስማማ አድርገው፤ ባማረ መልኩ ከይነውና አስጠንተው አስተውነውታል፡፡ ይህ ሲመደረክ ሀዲስ ከመኳንንቱ ባሻገር የጦር አለቆችን፣ ወታደሮችን ጠርተው በየመሃል ከተማው፤ ህዝብ በሚሰበሰብባቸው ገበያና ሜዳማ ቦታዎች ላይ እንዲታይ ያደርጉ ነበር፡፡ በዚያው መጠን ከቴአትሩ ጎን ለጎን የሚያነቃቃ ንግግር እያዘጋጁ፣ እግረ መንገዳቸውን ያስደምጡም ነበር፡፡ ለአብነት በዚህ ጊዜ ለሙከራነት “ያበሻና የወደ ሁዋላ ጋብቻ” የተሰኘ ቴአትራቸውን ሲያስመደርኩ በግጥምና በልዩ-ልዩ የፍቅር አገላለፆች የተሞላ ሆኖ ግና ኢትዮጵያ ወደ በኋላ ላይ ከሌሎች አገራት ጋር ወዳጅ ሆና፣ በመልካም ግንኙነት በሚመስል አብሮነት ተሳስራና ተጣምራ ስትኖር በዘፈን፣ በሆታና በጭፈራ ተዋህዶ ቀርቦ የሚታይበት ተስፋ ፈንጣቂ ቴአትር ነበር፡፡ ሀዲስ በዋናው ገጸባህሪ አእምሮ በተባለ አስተዋይ ሽማግሌ በኩል ልጆቿን ሰብስቦ እናታቸው (ኢትዮጵያ) እንዲያ ስትንገላታ ዝም ብለው በመመልከታቸው ወቅሶ፣ ለወደ ኋላ እንዲያለያዩዋት ይመክራቸውና፤ የሀበሻ ልጆች በአንድነት ሆነው እናታቸውን በሰላም አልፈታም ስላለ፣ ምርኮዋቸው እሱን ገድለው እናታቸውን ነፃ ሲያወጡና እያቅራሩና እየፎከሩ ሲደሰቱ ይጠናቀቃል፡፡ ቴአትሩ ህዝቡ ላይ በፈጠረው መነካትና ባልጠበቁት ምላሽ ግለቱ ተጋብቶባቸው የተደሰቱት ሀዲስ፣ ይህን ስሜታቸውን የገለጹት እንደሚከተለው ነበር።…“አቤት ያን ጊዜ የተሰማን ደስታ! ያን ጊዜ የተሰማንን ደስታ ሊገልጹት የሚችሉ ቃላት አይገኙም፡፡ ያን ጊዜ የሩቅ አላማችንን የመታን መስሎ ተሰምቶን የምስራቹን ለማህበርተኞቻችን ለመንገር በደስታ እየፈነደቅን ሄድን፡፡ እኔ ለታሰበው ስራ ሊሆን እንደሚችል ከማሻሻያው ጋር አንድ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ለዚያ ተጨማሪ የሚሆን አጠር ያለ ቴአትር አዘጋጅቼ አደረስሁ፡፡ መቼም ያ በጥቂት ቀናት ውስጥ የተደረሰው ቴአትር የሰውን ስሜት ቀስቅሶ ለማሸለልና ለማስፎከር ያክል የሚበቃ ከመሆን አልፎ በኪነት መልኩ ሲታይ ከቴአትር ተራ ገብቶ የሚቆጠር ነበር ለማለት አያስደፍርም!”… ሀዲስ በዚያው መጠን ያገር ፍቅር መቀስቀሻ፤ የሚያነቁና የሚያነቃቁ ንግግሮችን ህዝብ በሚሰበሰብባቸው ስፍራዎች እንዲነገርና እንዲከየንም ያደረጉባቸው አጋጣሚዎች ጥቂት አይደሉም፡፡ በግጥም መልክ ደርሰው፣ በመዝሙር ስልት ደርድረው ካስወረዱት “ተነሱ ታጠቁ” የተሰኘው ይገኝበታል፡
እናት ኢትዮጵያ ውዲቱ ውዲቱ
በሶስቱ ቀለሞች የተሸለምሽቱ
ነፃነት የሚዳፈር ቢመጣብሽ ብርቱ
ደማችን ይፈሳል አይቀርም በከንቱ
በረከትሽን ይንሳው እስከ እለተ ሞቱ  
ኢትዮጵያ አገራችን፣ ስለነፃነትሽ ይፈሳል ደማችን”
ሀዲስ በ“ተረት ተረት የመሰረት” ወደ ኤዞፕ ሳያቀኑ ከእንስሳቱ ውስጥ አንጥረው በመመልመል በምሳሌ አዋዝተው መግለጽ የጀመሩት ቀደም ባሉት ሌሎች ስራዎቻቸው ውስጥም ነበረ፤ በ“የህልም እዣት“፣ በ“ወንጀለኛው ዳኛ“፣ በ“ትዝታ“…ከመሳሰሉ ስራዎቻቸው ውስጥ ነቅሶ ማሳየት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ በአንድ ተረታቸው ያስተላለፉት መልእክት፣ ንጉሱ የፋሽስት ወረራን የአለም መንግስታት ማህበር እርዳታን ተስፋ ከማድረግ ይልቅ በህዝባችን ጀግንነት ተስፋ ማድረግ ነው የሚገባን! በሚል የንጉሱን ሽሽት በእንስሳቱ መስለው እንዲህ ተቃውመዋል፡፡…“መሪ የሌለው ሰራዊትና እረኛ የሌለው ከብት አንድ ነው! እንደሚባለው ነው፡፡ እረኛ የሌለው ከብት አውሬ ቢመጣበት፣ ሁሉም ከመበላት ለመዳን በየፊናው ይፈረጥጣል እንጂ፣ እንኩዋንስ ተባብሮ አውሬውን ሊቃወም ባንድ ተሰብስቦ እበረቱ መግባት አያውቅም፡፡ አስተባብሮ የሚመራው የሌለው ሰራዊትም እንደዚያ ነው” ይላሉ!… ይቀጥላል፡፡  




Read 695 times