Saturday, 22 July 2023 00:00

የሀዲስ አለማየሁ ተረት፣ እንደ ሥነጽሁፍ ዘውግ

Written by  አብዲ መሐመድ
Rate this item
(0 votes)

   ”--ደራሲው ዝም ብለው አንድን ተረት ተርተው ሲያበቁ፣ በደፈናው በባዶ ወግ ብቻ አይሞሉንም፡፡ እውነቱ ከተረቱ አመዝኖ ውስጣችን እንዲቀር የሚሄዱበት ርቀት ረጅም ነው፡፡ ተረቶቻቸው ከንቱ አስተሳሰቦችን ሰብረው፣ ወንዝ እማያሻግሩ ትብታቦችን በጣጥሰው ለመውጣት እንዲሁም ለማሳመን በእጅጉ የሚጥሩ ናቸው፡፡ ጎጂ ልማድን ዘበት ለማድረግ አያንቀላፉም፡፡--”
        

        ደራሲ ሀዲስ አለማየሁ ከነጻነት በኋላ ከሰባት አመታት በላይ በጣሊያን ሀገር ተግዘው ከረሙ፡፡ በርግጥ እስራታቸው ከሌሎች የዩጎዝቭ ግዞተኞች አንፃር ሲታይ ቀላል ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በሲሲሊዋ ሊፓሪ ደሴት ውስጥ መሄድ የሚችሉባቸው ወይም እንዲሄዱ የተፈቀዱላቸው ቦታዎች ውስን አልነበሩም፡፡ ያሻቸውን ለመሆንም ነጻነቱን አልተነፈጉም፡፡ የውሃ ዋና፣ ንባብና የእግር ጉዞን መሰል ሌሎችም መዝናኛዎች ተፈቅዶላቸው ነበር፡፡ ከሀዲስ ጋር ሌሎች አንቱ የተባሉ ሹማምንትም አብረዋቸው ነበሩ፤ ክቡር ራስ እምሩ፣ ደጃዝማች ታዬና ልጅ ይልማን የመሳሰሉ፡፡ ታዲያ የግዞት ዘመናቸውን ለእስር የቀረበ መራር እንዳይሆን ካቀለሉላቸው ተቀዳሚ ሳይሆን ተደማሪ ምክንያቶች ሌላኛው፤ ተሰባስበው የሚያደርጓቸው የክርክርና  የጭውውት …ተናፋቂ ጊዜያቶች ነበሩ፡፡ ሀሳባቸው በአብዛኛው የሰፊው ህዝብ፣ የሰፊው አለም ቁም ነገሮች ነበሩ፡፡ አብሮነታቸው አሰልቺ እንዳይሆን በእጅጉ ያሟሹላቸውም ነበር፡፡ ክርክርም-ምክክርም የማያጣው  ውይይታቸው ታዲያ በይበልጥ አጓጊ ያደረገው ደግሞ ትምህርት አዘል መሆኑም ጭምር ነበር። (አስተሳሰብ በውይይት ይሳላል ያሉት ፕሮፍ፣ ለዚህ ሳይሆን ይቀራል?)
ውይይትና ክርክራቸው በሁለት ጎራ የተከፈለ ነበር፡፡ በነባሩ አስተሳሰብና ያሰራር ስልት የሚያምኑና የማያምኑ!...ከመሀላቸው ምንም እንኳን ጥንታዊውንና ቀዳሚውን አመለካከትና እምነት ጨርሶ ዋጋ ባያሳጡትም እንኳን፣ ለዘመናዊው አስተሳሰብም ቢሆን ዋጋና ክብደት የነፈጉም አልነበሩም፡፡ ሀዲስ በክርክሩ በሚነሱ ጉዳዮች ላይ ያላቸው የሀሳብ የበላይነት በንጉሱ ፓርላማ በፀደቀ ህግ የተደነገገ ባይሆንም እንኳን፣ በራሳቸው ምዕናብ ተረቅቆ ያለው ተፅዕኖ ለችግሮች ከሚያቀርቡት ሁነኛ መፍትሄ የመነጨ ነበር፡፡ ስለሆነም በመንግስታዊ አስተዳደር ውስጥ ካላቸው ተሞክሮ በመነሳት እንዲሁም በሙያ ከገነቡት የካበተ የልምድ ብቃትና ትጋትም ተጨምሮ ከመሰሎቻቸው መሀል ተሰሚነታቸው ከፍ ያለ ነበር፡፡ ሀዲስ የደሴቱ አስተዳዳሪዎች ተቀይረው ቆይታቸውን የስቃይ ሳያደርጉባቸው በፊት እነዚያን ውብ ጊዜያት እንዲህ ያስታውሷቸዋል።…”ኑሮዋችን በግዞተኞች ኑሮ አይን ሲታይ በውነቱ ደህና ነበር። አንዳች የምናማርረው ነገር አልገጠመንም። ቀን ከሆነ በደሴቱ ውስጥ በፈለግነው ጊዜ ወጥተን የፈለግነውን ያክል ሽርሽር ለማድረግ እንችል ነበር፡፡ ከነሱ ጋር መውጣት ስንፈልግ ካልሆነ አይከተሉንም፡፡ የፈለግናቸውን መጻሕፍት ከውጭ አገር አዝዘን አስገብተን ማንበብም እንችል ነበር፡፡ ሬዲዮ ገዝተን እቤታችን ውስጥ የአለም ወሬ ያለ ተቆጣጣሪ መስማት እንችል ነበር፡፡ ታዲያ አንዳንዴ በፀጥታ ሌሎቹ ሲከራከሩ ልጅ ይልማና እኔ አብረናቸው ተቀምጠን መስማት ደስታን ብቻ ሳይሆን ትምህርትንም ጭምር ይሰጠን ነበር”፡፡
“በተረት ስም”
ከልቦለድ ባሻገር የሞከሯቸው ሥነጽሁፋዊ ዘውጎች ጥቂት አይደሉም፡፡ ስነ-ግጥም አንዱ ሆኖ ተውኔት እና ተረት ይከተላሉ፡፡ ሀዲስ በአለማችን ገናና ተረቶችን ያበረከቱ ስመጥር ደራሲያንን አስተዋውቀውን ሲያበቁ፤ የኛን ጥንታዊ ተረቶች ከነለዛቸው እንደ አዲስ በማቅረብ እንዲሁም በመፍጠር ረገድ በእጅጉ ተክነዋል፡፡ ይህን ክህነት በ“ተረት ተረት የመሰረት” ሰንደው እነሆ ለትውልድ አሻግረውልናል፡፡ ተረቶች በሞራል ግንባታ ረገድ የበዛ ፋይዳ አላቸው፤ ወይም እንዳላቸው በተረት ሀያስያን ዘንድ ይታመናል፡፡ ሀዲስ ከልቦለዱ ባልተናነሰ በተረት ፈጠራ ላይ የተዋጣላቸው ጠቢብ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ለተባበሩት መንግስታት ማህበር ተጠባባቂ የኮሚቴ ተካፋይ እንዲሆኑ ታዘውና ተጋብዘው በሄዱበት ወቅት፤ ስለቅኝ አገር አስተዳደር ያደረጉትን ንግግር ያስረዱት፣ በአይጥና ድመት መስለው እራሳቸው የፈጠሩትን ተረት በማቅረብ ነበር፡፡ እንደ ልቦለድ እና ጥናታዊ ሰነድ ሁሉ የተረት ታላቅነትም በጊዜ እና በቦታ አይወሰንም። ጥንት የተጻፈውም ቢሆን ዛሬ ላለው ሁነትም ሆነ ክስተት…ሁነኛ ምሳሌና ተምሳሌት መሆኑ ተረትን ልዩ ያደርገዋል፡፡…ፍርድ አያጓድልም፣ ደሀን አይበድልም፣ ለሀብታም አያጎበድድም፡፡ በሀሰት አይፈርድም፣ በክፋት አያዳላም፣ ሌላ-ሌላም፡፡
ሀዲስ ይሄ እውነታ ቀድሞ ገብቷቸው ኖሮ በተረት ስም ዱሩንም መንደሩንም እያሰሱ፣ የእንስሳቱን አለም በምዕናባቸው እየቃኙ፤ መነሻቸውን ካሳደጉን የአፍላነት ተረቶች በ“የጅብ ፍቅር እስኪቸግር” ይንደረደሩና በ“ሳታመካኝ ብላኝ” ብዕራቸውን ያሟሹና፣ “ብርቱዎች ከደካሞች ጋር በሚኖሩበት አለም፣ ብርቱዎች ደካሞችን ለማጥፋት ሲሉ ቢበቃም-ባይበቃም ለሚሰሩት የአጥቂነት ስራ መሸፈኛ የሚሆን ከንቱ ምክንያት የሚፈልጉ መሆናቸው” ልክ አለመሆኑን ይኮንናሉ፡፡ ፍትህን በተረቶቻቸው ሊያሰፍኑ አብዝተው ይታትራሉ፡፡ (ማን ነበር? የሰው ልጅ  የማስተዋል ደረጃው ሲወርድ ነው ህግ የሚረቀቅለት ያለው!) አለፍ እያሉ ደግሞ “በቀበሮ ስጋ ቤት” የፈጠራ ተረታቸውን ተርከው ሲያበቁ፤ “አምላክ ሲቆጣ በበሽታ እንጂ በሞት አይቀጣ” እና “አገር የሚፈለገው ሲቸግር ነው እንጂ፤ ሲመችማ የሰው አገርም አገር ነው፤ ባዕድም ዘመድ ነው”! የመሳሰሉ መልእክቶችን ያስተላልፋሉ፡፡ ግላዊ ፍልስፍናቸው የረቀቁና ሊተነተኑ የሚገባቸው…በራሳቸው ሰም ለበስ ቅኔዎች ናቸው፡፡
 በመሰረቱ የተረት ታሪኮች ለህፃናት የታዘዙ የእንቅልፍ እንክብሎች ብቻ አይደሉም፡፡ ለንባብ ቀላልና ምቹ ይሁኑ እንጂ ለአዋቂዎችም የጠጠሩና የነጠሩ ከመሆናቸው ባለፈ ለቤተሰብ፣ ለማህበረሰብ ኑሮ ተምሳሌት የሆኑ አያሌ ጠቃሚ አስተምህሮቶችን ያቀፉም ናቸው፡፡ በአማርኛ ስነጽሁፍ ውስጥ የተረት መድበል፤ ሀዲስን በመሰሉ ነባር ደራሲያን ፈር ቀዳጅነት በስፋት ይተዋወቅ እንጂ፣ በአለማችን ከጥንታውያን ኤዞፕ ተረቶች ባሻገር ገና በማደግ ላይ ባሉ አገራትም እጅግ ገኖ የታወቀ ዘርፍ ነው። ዛሬ-ዛሬ በቦሊውድ ኢንዱስትሪ ውስጥ በገቢ ረገድ ክብረ ወሰን የሰበሩ የአኒሜሽን ካርቱን ፊልሞች፣ መነሻ ታሪካቸው፣ ጽንሰ ሀሳባቸው…ተሰንደው የቆዩላቸው ነባር ተረቶቻቸው መሆናቸውን እዚህ ጋ መጥቀስ ግድ ይላል፡፡ አዳም ረታ፣ ያልተጣራ የመንደር ወሬ አምኖ፣ ከሰማይ የወረደ ፍርፍር ፍለጋ ከማክዳ የሞቀ እቅፍ ወጥቶ ሲገሰግስ የባጀው ገጸባህሪውን የመለመለው፣ ከሀገር በቀል የተረት ባህር ጠልቆ አንዱን በማስገር ነው። በውጭው አለም በተለይ በምዕራባውያን ዘንድ ተረቶች በስፋት ለንባብ ፍጆታ መዋላቸው ይስተዋላል። ከዚህ ባለፈ ደግሞ በየትምህርት ተቋማቱ በጥልቀት መጠናታቸው በእጅጉ ያብሰለሰላቸው ሀዲስ፤ በኢትዮጵያ ምንም እንኳን ደራሲያቸው ባይታወቁም ተጽፈው የኖሩ ብዙ ተረቶች እኮ አሉ! ሲሉ ይቆጫሉ፡፡ ይሁንና እንዲህ ያሉ በውስጣዊ ሀሳባቸው የረቀቁ፣ ረቂቅ ሚስጥራትን የሰነቁ፣ የሀገርን ጥንታዊ ስልጣኔ ያቀፉ፣ ምሳሌዎችን የሚገልጹ…አንድ ላይ ሰብስቦና መልክ ሰጥቶ የሚያሳትም ሰው ቢገኝ፣ ለሀገር ብቻ ሳይሆን በጠቅላላው ለሰው ዘር ትልቅ አገልግሎት ያላቸው መሆኑን በመግቢያቸው ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡ ደራሲው በተረት ተረት የመሰረት ውስጥ እምነትን፣ ፍቅርን፣ ሰብአዊነትን፣ ሀቀኝነትን፣ ነጻነትን…በ“ጥጋብ ስስትን ያገባ እንደሆነ ረሃብን ይወልዳል”፤ በ“የወለደውን የማያከብር የሚያከብረውን ልጅ አያገኝም”፣ በ“የአህያ ደግ ዋጋው ጭነት መጨመር ነው”…በኩል በበቂ አብራርተዋል። እንዲሁም “ዞሮ-ዞሮ አለም ለዝንጀሮ፣ አንበሳ ንጉስ አራዊት” በተሰኘ ተረታቸው ደግሞ፣ ስልጣንን ያለ ተጠያቂነት፣ በማን አለብኝነት፣ በይሉኝታ ቢስነት …ያለአግባብ የመጠቀም አባዜ፣ አገርና ህዝብን ለውጥንቅጥ አመቻችቶ፣ ዜጎችን ለኑሮ ምሬት የሚዳርግ መሆኑን በእንስሳቱ በኩል ተንትነው አሳይተዋል፡፡ (በተለይ በአሁኑ ወቅት ነባሩን ከማሻሻል ይልቅ ማፍረስ የቀለላቸው፣ የህዝብ እንባ መጥፊያቸው መሆኑ የተዘነጋቸው፣ ሀገሪቱ ለገባችበት የኑሮ ምስቅልቅል ስልጣንን የሙጥኝ ብለው እራሳቸውን ከተጠያቂነት ነጻ ለማድረግ የሚለፉ፤ የህዝብ ባላደራ ተሹዋሚ ባለስልጣናት በተረት መልክ በልካቸው የተሰፋ መማሪያቸውም ይመስላል!)
ድመትን፣ ውሻን፣ ጦጣን፣ አንበሳን…እንደ አንድ ሉአላዊ ገጸባህሪ በማስወከልም፣ በማስመሰልም ለሦስተኛው አለም ማህበረሰቦች ለአፍሪካ ብሎም እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ኋላቀር አገራት እንደ ህዝብ የሚተውትን፣ የሚያደርሱትን ሥነልቦናዊ ተፅእኖ “አማኝ ውሻውን የከዳ ውሻ ይሆናል” በሚል በምሳሌ አዋዝተው ባሰፈሩት ተረታቸው፣ ባልተንዛዛና በተቆጠበ መልኩ እየገሰጹ እንዲህ አመላክተዋል፡፡…”እናንተ በጠገባችሁ መጠን መብላት ትፈልጋላችሁ፤ ባገኛችሁ መጠን ሌላ ያምራችኋል፤ በውሻና በሰው ዘር መሀከል ያለው አንዱ ትልቅ ልዩነት ይህ ነው፡፡ እኛ አመላችን የሚከፋና ጥል የምንፈልግ ሲርበን ነው፤ እናንተ ስትጠግቡ ነው፤ እኛ ከጠገብን ተኝቶ ማረፍ ነው የምንፈልግ፤ የተረፈንን ማንም ቢበላ ግድ የለንም፤ እናንተ ግን ስትጠግቡ እንዲያውም የሌላውን ልትቀሙ ትሄዳላችሁ፤ ስለዚህ አለምን የመከራ ቦታ ታደርጉዋታላችሁ፡፡”(ገጽ.55)… ሀዲስ በተረቶቻቸው ነባሩን የልማድ ትብታብ ለመበጣጠስ አብዝተው ይታትራሉ፡፡ ኋላቀሩ ባህል ውስጥ የስልጣኔን ቅንጣት ለመለኮስ አብዝተው ይደክማሉ፡፡ ደራሲው ዝም ብለው አንድን ተረት ተርተው ሲያበቁ፣ በደፈናው በባዶ ወግ ብቻ አይሞሉንም፡፡ እውነቱ ከተረቱ አመዝኖ ውስጣችን እንዲቀር የሚሄዱበት ርቀት ረጅም ነው፡፡ ተረቶቻቸው ከንቱ አስተሳሰቦችን ሰብረው፣ ወንዝ እማያሻግሩ ትብታቦችን በጣጥሰው ለመውጣት እንዲሁም ለማሳመን በእጅጉ የሚጥሩ ናቸው፡፡ ጎጂ ልማድን ዘበት ለማድረግ አያንቀላፉም፡፡ ለምሳሌ በአንድ ምዕራፍ ውስጥ በነገር ለታመመና ለተወጋ ልብ ጠበሉ የሽማግሌ ምክር ነው የሚባለውን የጋፋቶችን ምሳሌ ተከትለው፣ የተረቱ ዋና ገጸባህርይ በሆነው በቡሌ አህያው በኩል ዘመን የማይሽራቸውን ምክሮቻቸውን እንዲህ በማለት ይለግሱናል፡፡ “ቁጣ ክፉ ነው ወገኖቼ፤ ቁጣ በደቂቃ ያፈረሰውን ትዕግስት በአመት አይሰራውም፡፡ ለደግ ነገር መቸገር በህሊና ደስታ ስለሚክስ ችግር አይባልም፡፡ ቅንነታችሁን ሁሉ በአንድ ላይ ማሳየት አይገባችሁም፡፡ ያላችሁን በጎነት ሁሉ በአንድ ላይ ከምትሰጡ እየቆጠባችሁ በመስጠት ሰዎች ገንዘባቸው እንዲያደርጉት አስችሏቸው፡፡”(ገጽ.24)
የአለማየሁ ሰለሞንና የደስታ አለሙ ጋብቻ ካስገኘው አንድ ፍሬ ወደዚህ ምድር የመጡት ሀዲስ፤ ጥቅምት 7 ቀን 1902 ዓ.ም ነው የተወለዱት፡፡ በወጣትነታቸው ከአያታቸው ቤት ፊደልን ቆጥረዋል፤ ዳዊትንም ደግመዋል፣ ዜማንም እንዲሁ ተምረዋል፡፡ እንደ ልጅ ተጫውተውም ያደጉት እዚያው ነበር። …ሩሲያውያን ልክ ለአቅመ አዳም ወይም ለአቅመ ሄዋን እንደ ደረሱ የቶልስቶይን “አና ካረኒና” ወይንም “ዋር ኤንድ ፒስ” የተሰኙ ዝነኛ ልቦለዶችን ያነብቡና ሀገራቸውን በተወሰነ መጠን ሳይሆን በምልአት ይገነዘቧታል፡፡ ከኛ አገር ደግሞ የነባርዋን ኢትዮጵያ ወግና ስርአቷን፣ ባህልና እምነቷን፣ የህዝቧን ስነልቦና እና ንጉሳዊ አስተዳደር… በተጨባጭ ስዕል ከሚያሳዩልን፣ ከሚያስገነዝቡልን የአገር ባለውለታዎቻችን መካከል ዛሬም ሀዲስ አለማየሁ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ደራሲ ናቸው። ገና በየትውልዱ ሲነሱም ሆነ ሲወሱ የሚኖሩ አይረሴ ምልክታችንም ጭምር ናቸው፡፡ 

Read 667 times