Saturday, 12 August 2023 20:44

በመዲናዋ የግብረ-ሰዶም ተግባር ይፈፀምባቸዋል ተብለው በተጠረጠሩ ተቋማት ላይ እርምጃ እየተወሰደ ነው ተባለ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

“ግብረሰዶማዊነት በሀገራችን ህግ ፍጹም የተከለከና በህግ የሚያስጠይቅ ተግባር ነው”


የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ፣ በከተማዋ የግብረሰዶም ተግባር  ይፈፀምባቸዋል ተብለው በተጠረጠሩና ጥቆማ በተሰጠባቸው ሆቴሎች፣ ባሮችና ሬስቶራንቶች ላይ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን የገለጸ ሲሆን፤ ከህብረተሰቡ ለሚደርሰው ጥቆማ፣ ከአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ጋር በቅንጅት በመሥራትም ላይ እንደሚገኝ ጠቁሟል፡፡
ከነባሩ የሀገራችን ባህል፣ ወግ፣ የአኗኗር ስርዓትና ሃይማኖቶች ባፈነገጠ መልኩ የግብረ-ሰዶም ተግባር በሚያስፈጽሙ ሆቴሎች፣ ሬስቶራንቶች፣ ፔንሲዮኖችና መሰል የመዝናኛ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ላይ ከህብረተሰቡ በሚደርሰው ጥቆማ መሰረት፣ አስተማሪ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን ቢሮው አስታውቋል።
የአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ፣ የግብረ-ሰዶም ተግባር መፈጸምና ማስፈጸም በኢትዮጵያ በሥራ ላይ ባሉ ሕጎች የተከለከለ መሆኑን ገልፆ፤ ይህንን አስጸያፊ በሰውም በአምላክም ዘንድ የተጠላ ድርጊት በሚፈጽሙና በሚያስፈጽሙ የመዝናኛ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ላይ፣ ያለ አንዳች ርህራሄ  ከፖሊስ ጋር በመተባበር፣ እርምጃ መውሰዱን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አመልክቷል።
በዚሁ መሰረት በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 02 አስተዳደር ውስጥ በሚገኝ “አበባ ገስት ሐውስ” በሚባል የመዝናኛ አገልግሎት መስጫ ተቋም ላይ፣ ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ መሰረት  እርምጃ እንደተወሰደበት የጠቆመው ቢሮው፤ የተቋሙ ኃላፊም በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሎ  ምርመራ እየተካሄደበት  መሆኑን አመልክቷል፡፡
በተመሳሳይ፤የአዲስ አበባ ከተማ ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ፣ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ጋር በሰጡት መግለጫ፤”ሀገራችን በህብረ ብሄራዊነቷ የምትታወቅና የተለያዩ ባህሎችና ወጎች ያሏት ሀገር ስትሆን፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከማህበረሰቡ ወግና ባህል ያፈነገጡ ድርጊቶች እያጋጠሙ ነው” ብለዋል፡፡
ግብረሰዶማዊነት በሀገራችን ህግ ፍጹም የተከለከና በህግ የሚያስጠይቅ ተግባር መሆኑን የገለጸው ፖሊስ፤ በዚህ ተግባር ላይ በተሰማሩ ወገኖች ወይም ተቋማት ላይ መረጃን መሰረት አድርጎ፣ በህግ አግባብ እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቋል።
በዚህ ዓይነት ህገ-ወጥ ተግባር የሚጠረጠሩ ሆቴሎችና  ሬስቶራንቶች፣ የሀገሪቷን ህግ አክብረው የመስራት ግዴታ እንዳለባቸውም ‹ፖሊስ  አስጠንቅቋል፡፡
ከግብረሰዶም ፀያፍ ተግባር ጋር የተገናኘ መረጃና ጥቆማ ያለው ማንኛውም ሰው በአቅራቢያው በሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ በግንባር በመቅረብ፣ በነፃ የስልክ መስመር፡- 991 እና 987 እንዲሁም በ011-1- 11-01-11 እና 011-5-52-63-02 በመጠቀም መረጃና ጥቆማ መስጠት እንደሚችል የጠቆመው ቢሮው፤ አሁንም ህብረተሰቡ ይህንኑ  አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቋል።


Read 1641 times