Saturday, 12 August 2023 20:44

እስራኤል ዜጎቿን ከባህርዳርና ጎንደር እያስወጣች ነው

Written by  መታሠቢያ ካሣዬ
Rate this item
(0 votes)

 በአንድ ቀን ብቻ ከ200 በላይ ቤተ-እስራኤላውያን ወጥተዋል



በአማራ ክልል የተቀሰቀሰውን ግጭት ተከትሎ፣ እስራኤል በጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ ልዩ ትዕዛዝ ዜጎቿን ከባህርዳርና ጎንደር እያስወጣች ነው። እስራኤላውያኑን በማስወጣቱ ሂደት የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት፣ የእስራኤል የውጪ ጉዳይ ሚንስትር፣ የእስራኤል የደህንነት ምክር ቤት፣ የእስራኤል ኤምባሲና የአይሁዳውያን ተቋም እንደተሳተፉበት ታውቋል።
በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በመንግስትና በታጣቂ ሃይሎቹ መካከል ሲካሄድ በሰነበተው ግጭት ሳቢያ የየብስና የአየር ትራንስፖርት አገልግሎቶች ለቀናት ተቋርጠው የቆዩ ሲሆን ባለፈው ረቡዕ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አስፈጻሚው አካል፣ የፌደራሉ መንግስት ሃይሎች ስድስት ከተሞችን ከታጣቂዎች በማስለቀቅ መቆጣጠሩን ገልጾ፤ ሁሉም አይነት የትራንስፖርት አገልግሎቶች እንደሚጀመሩ አሳውቆ ነበር።
በዚህ መሰረትም በባህርዳርና ጎንደር ከተማ ከነበሩ ዜጎቻቸው ጋር ለ24 ሰዓታት ሲገናኙና ዜጎቹን ከባህርዳርና ጎንደር ለማስወጣት ከጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ ልዩ ትዕዛዝ የተሰጣቸው የእስራኤል የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴርና የአገሪቱ የደህንነት ምክር ቤት የስራ ሃላፊዎች፣ 174 ቤተ-እስራኤላውያንን ከጎንደር  ከተሞች ካሰባሰቧቸው በኋላ በጎንደርና በባህር ዳር አየር ማረፊያዎች ቀድመው በተዘጋጁ ልዩ በረራዎች አማካኝነት፣ ከትናንት በስቲያ አዲስ አበባ ከተማ እንዲገቡ ተደርገዋል። የአገሪቱ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደገለጸውም፤ ዜጎቹ ወደ እስራኤል ለመመለስ እስኪወስኑ ድረስ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ እንዲቆዩ ያደርጋል።
ይህ ቤተ-እስራኤላውያኑን የማስወጣት ተልዕኮ፣ በእስራኤል የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር መ/ቤት ውስጥ ባለ የመከታተያ ክፍል እገዛ እየተደረገለት የተከናወነ ሲሆን፤ ዲፕሎማቶች፣ የአይሁዳውያንን ተቋም ሰራተኞችና አማርኛ የሚችሉ የእስራኤል ሰራዊት አባላት፤ በቡድኑ ውስጥ መካተታቸው ታውቋል። የአገሪቱ  የውጪ ጉዳይ መ/ቤት ከዚህ ቀደም እንዳደረገው ሁሉ አሁንም ዜጎቹ ድጋፍ በሚፈልጉበት ጊዜ በማንኛውም የዓለም ክፍል የሚቻለውን አስፈላጊ ነገር ሁሉ እንደሚደረግ ገልጿል። እስራኤል ለዜጎቿ ባሉበት ሥፍራ ሁሉ ጥበቃ እንደምታደርግላቸው ታውቋል።
ለጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ “ባለፉት ቀናት፣ ግጭት በተቀሰቀሰባቸው የኢትዮጵያ አካባቢዎች የነበሩ ዜጎቻችን ከዚያ እንዲወጡ አዝዣለሁ” ብለዋል።
በኢትዮጵያ በተለይም በአማራ ክልል ውስጥ በርካታ ቤተ-እስራአኤላውያን የሚገኙ ሲሆን የእስራኤል መንግስትም  እነዚህን ዜጎች፣ በተለያዩ ሁኔታዎች ወደ እስራኤል በመወሰድ በአገሩ ውስጥ ካሉ ወገኖቻቸው ጋር እንዲቀላቀሉ ሲያደርግ ቆይቷል።


Read 1443 times