Saturday, 19 August 2023 20:04

“ሁሉንም ዕንቁላልህን አንድ ቅርጫት ውስጥ አታስቀምጥ” “ገና ሳይፈለፈሉ ጫጩቶች መቁጠር አትጀምር”

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ሁለት መንገደኞች ራቅ ወዳለ አገር ለመሄድ ጉዞ ጀምረዋል፡፡ ሁለቱም የተለያየ ጠባይ ያላቸው ናቸው፡፡
አንደኛው፤ በህይወቴ ሙሉ ዕውነት ፈፅሞ ተናግሮ የማያውቅ ነው፡፡
ሁለተኛው ደግሞ ዕድሜውን በሙሉ ውሸት የሚባል ነገር ፈፅሞ ተናግሮ የማያውቅ ነው፡፡
ሁለቱ መንገደኞች ብዙ ከተጓዙ በኋላ፣ ወደ ዝንጀሮዎች አገር ይደርሳሉ፡፡ የዝንጀሮዎቹ ንጉስ መንገደኞች መምጣታቸውን ይሰማና፣ ወደ ዙፋኑ እንዲቀርቡ ያዛል፡፡ ግርማ - ሞገሱንና ታላቅነቱን ይረዱ ዘንድ ዙፋኑ ላይ በክብር ይቀመጥና፣ ሌሎቹን ባለሟሎቹንና የበታች ሹማምንቱን በግራና በቀኝ እንዲኮለኮሉ ያደርጋል፡፡ ከግራ ከቀኙ የተደረደሩት ዝንጀሮዎች ረዥም መስመር ሰርተዋል።
መንገደኞቹ ዙፋኑ ፊት ቀርበው ለጥ ብለው እጅ ሲነሱ፤ የዝንጀሮዎቹ ንጉስ፤
“ረዥም መንገድ ላይ እንዳላችሁ ሰማሁ፤ ዕውነት ነው?” አሉ፡፡
ዕውነት የሚናገረው ሰውዬ፤
“አዎን ንጉሥ ሆይ፤ ገና ሁለት ቀንና ሌሊት ተጉዘን ነው ወደ አሰብንበት አገር የምንደርሰው” አለና መለሰ፡፡
“ለምን ጉዳይ ነው የምትሄዱት?”
“የምንሄድበት አገር ያሉት ሰዎች እጅግ የሰለጠኑ ናቸው ይባላል፡፡ እኛ ገና አላየናቸውም። ከነሱ ትምህርት በመውሰድ ያገኘነውን አዲስ ነገር፣ ወደ አገራችን አምጥተን እኛም እንደነሱ ለመሰልጠን አስበናል” አለ፡፡
ንጉሱም፤ “መልካም፡፡ ሃሳባችሁ የተቀደሰ ነው፡፡ ጥሩ ነገር እንዲገጥማችሁ እመኛለሁ፡፡ አሁን ያስጠራሁዋችሁ ስለ እኔና ስለ ባለሟሎቼ ምን እንደምታስቡ እንድትነግሩኝ ነው”
ይሄኔ ውሸት የመናገር ጠባይ ያለው መንገደኛ፤
“ንጉሥ ሆይ፤ ማንም እርስዎን ያየ ሰው እጅግ የተከበሩና ኃያል ንጉስ መሆንዎን አይስተውም።”
“ባለሟሎቼንና ሹማምንቴንስ እንዴት ታያቸዋለህ?”
“እነሱማ አንዳቸውም ከእርሶ ጋር አይተካከሉም፡፡ እርሶ እዚያ አናት ላይ፤ እነሱ ደግሞ እዚህ ታች እግርጌ ናቸው፡፡ የጌታቸውን ክብርና አዋቂነት ይፈራሉ”
የዝንጀሮዎቹ ንጉስ በጣም ተደሰተ፡፡ መደሰቱ እስከሚታወቅበት ድረስ እየተቅበጠበጠ በባለሟሎቹ ፊት ወዲያ ወዲህ ሲል ቆይቶ፤
“እንዳንተ፤ ሁሉ ሰው ዕውነቱን ቢያውቅ የት በደረስን፡፡ እንዳንተ ያሉ ሰዎች ይህቺን ዓለም ቢሞሉዋት የእኛ ሀገር ብቻ ሳትሆን፣ ጎረቤቶቻችንና ከዚያም የራቁት ሀገሮች የት በደረሱ፡፡ በል እንካ ይህን የከበረ ስጦታ ውሰድ፡፡ ስለተናገርከው እውነት ማስታወሻ ይሁንህ” አለና ስጦታውን አበረከተለት፡፡
ይህንን ያስተዋለው ሁለተኛው መንገደኛ በሆዱ እንዲህ አሰበ፡-
“ጌታው፤ አንተስ ስለእኔና ስለባለሟሎቼ ያለህ አስተያየት ምንድን ነው? እንዴት አገኘኸን?” ዕውነት ተናጋሪው መንገደኛም፤
“ንጉስ ሆይ እርሶ ግሩም ነዎት፡፡ ባለሟሎዎችም ግሩም ናቸው፡፡ በምንም አትተናነሱም፡፡ በምንም አትበላለጡም፡፡ ሁላችሁም አንድ አይነት ናችሁ” አለ፡፡
የዝንጀሮዎች ንጉስ ቱግ አለ፤  ተቆጣ፡፡ እጅግ ከመናደዱም የተነሳ፤
“በዝንጀሮዎቹ ጥፍር እየተቧጠጠ እየተሰቃየ እንዲሞት!” ሲል ትዕዛዝ ሰጠ፡፡
***
ንጉሶች፣ መሪዎችና አለቆች ሁሌም ከሌሎች ባለሟሎችና አጋሮቻቸው እንዲሁም የሥራ ባልደረቦቻቸው እኩል ናችሁ እንዲባሉ አይፈልጉም፡፡ የተለዩ መሆናቸውን፣ የተሻሉ መሆናቸውን፣ ከሁሉ በላይ መሆናቸውን የሚነግራቸውን አማካሪ ነው የሚወዱት፡፡ በጊዜና በታሪክ አጋጣሚ እንጂ እነሱም እንደማናቸውም ባለሟል እንደነበሩ፤ ይዘነጋል፡፡ አንገረ ፈላስፋ፤ “ሸክላ ሲሰበር ገል ይሆናል፤ መኳንንትም ሲሻሩ ያው እንደማንኛውም ሰው ይሆናሉ” የሚለውን ይረሱታል፡፡ እንደ ዕውነቱ ከሆነ ሲሾሙና ሥልጣን ሲይዙ ራሳቸውን ከጥንት ወዳጆቻቸው የተለየ ፍጡር አድርገው ባያዩ፤ ከሥልጣን ሲወርዱ የተዋረዱ አድርገው ራሳቸውን ከህዝብ እንዳይሸሽ በጠቀማቸው ነበር። በእርግጥም፤ ራሳቸውን የተለየ ፍጡር አድርገው ማየት፤ የተለየ እንክብካቤ፤ የተለየ ጥቅም፣ የተለየ ከበሬታ ወደመፈለግ እንዲያመሩ ያደርጋቸዋል፡፡ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን፣ በአንደኛው ቴያትሩ ውስጥ “የዘመኑ ተራማጅ፤ ሥልጣን በሸተተው ማግሥት አካሄዱ፣ አረማመዱ ሁሉ እንደ ድመት ኮርማ ይሆናል” ይላል፡፡ በመሰረቱ ማናቸውም ሥልጣን ላይ የሚቀመጥ ሰው የዚያ ወንበር ተሸካሚ፣ የዚያ ኃላፊነት አገልጋይ እንጂ በዚህ ሥልጣን ተገልጋይና የግል ጥቅሙን አሳዳጅ፣ የግል ወገናዊነቱን ተግባሪ ሊሆን አይደለም፡፡ ራስን ልዩ አድርጎ ማስቀመጥ ተነጥሎ መታየትን ብቻ ሳይሆን ዒላማ መሆንን ያስከትላል ይሏልና፤ በዚህም ረገድ ቢሆን አደገኛ ነው፡፡ ዛሬ ያልነውን ነገ መሻር ተዓማኒነትን ያሳጣል፡፡ በምንም ረገድ፤ በምንም ዘዴ ተጠቅመን እናስተባብለው ታዳሚው በልቡ ፅላት እንደሚፅፈው አለመርሳት ነው፡፡ ታዳሚ ጆሮ የገባ ነገር በዋዛ አይፋቅም፡፡ ይህን ምንጊዜም ማስተዋል ይበጃል፡፡ አንዴ ተዓማኒነትን ካልጣን መልሰን ማግኘት ዘበት ነው፡፡ አንድ ሁለት  ግለሰቦችን ቡድኖችን ማታለል ይቻል ይሆናል፤ ህብረተሰብን ግን ማታለል አይቻልም። ይህን እንደዋና መመሪያ ከመያዝ ዋና ነገር ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ግን የምንመራውን ህዝብ ምንም ያህል መልካም ፖሊሲ ብንቀርፅለት፤ ጊዜና ቦታ ለይተን፤ መጠንና ልክ አውቀን፤ ባህል ልምዱን አጣጥመን፤ ካላቀረብንለት ከየትም ከየትም ከምእራብም ከምስራቅም ያሰባሰብነው መመሪያና ደንብ እንዲሁም መተዳደሪያ፤ ባንድ ጊዜ እናስውጥ ብለውን ተርፎ የሚፈሰው፣ ሳይጨበጥ የሚሰበረው፣ ለአደጋ የሚያጋልጠው ይበዛና ካሰብነው ቦታ እንዳንደርስ እንሆናለን። ይኼ በየዘመኑ ደጋግመን አይተናል፡፡ በአንፃሩ ስለተጠነሰሰ ብቻ የማይጠመቅ ብዙ ጠላ አለ፡፡ ስለተወራ ብቻ የልብ የማያደርስ ብዙ ደጋግ እቅድ አለ፡፡ ከወረቀት የማያልፍ አያሌ ህግና ደንብ አይተናል፡፡ የማስፈራሪያ ያክል የሚጮህበት አያሌ መሬት ያላረፈ መፈክር ታዝበናል፡፡ (የቀድሞ መሪ አብዮቱ በፈነዳው በስምንተኛ አመቱ “የምንለውን ብለናል፤ የምናደርገውን እንጀምር” ማለታቸውን ልብ ይለዋል፡፡) ለፖለቲካዊ ልዩነቶች ሁሉ ወታደራዊ እርምጃዎችን እንደብቸኛ መፍትሄ መውሰድ ለአገርም ለመንግስትም ለህዝብም አይበጅም፡፡ ጦርነት ከአንዱ ክልል ወደ ሌላው ክልል ማሻገር አይመከርም ዘላቂ መፍትሄም አያመጣም፡፡
“ሁሉንም እንቁላልህን አንድ ቅርጫት ውስጥ አስቀምጥ” የተባለውን ያህል፤  “ገና ሳይፈለፈሉ ጫጩቶችህን መቁጠር አትጀምር” እንደሚባል አለመርሳት ታላቅ ነገር ነው፡፡ ሁሉንም አባልህን በአንድ አሸንዳ እንዲፈሱ አታድርግ፡፡ የሃሳብ ልዩነትህን ውደድ፤ አስተናግድ፡፡ ሁሉንም ወዳጆችህን ለአንድ ጉዳይ አታውል፡፡ ሁሉንም ተከታይህን የአንድ ሀሳብ ቁራኛ አታድርግ ማለትም ያስኬዳል፡፡

Read 1615 times