Friday, 18 August 2023 00:00

ጋዴፓ፤ “የህዝባችን ጥያቄ ራስን በራስ የማስተዳደር ነው” አለ አዲሱ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የምስረታ በዓል ፣ዛሬ በአርባ ምንጭ ይካሄዳል

Written by  ሪፖርታዥ
Rate this item
(1 Vote)

የጋሞ  ህዝብ ጥያቄ በክላስተር የመደራጀት አይደለም ያለው የጋሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ጋዴፓ)፤ህዝቡ ለረዥም ጊዜ ሲጠይቅ የቆየው ራሱን በራሱ የማስተዳደርና በክልል የመደራጀት ህገመንግስታዊ መብቱ እንዲከበርለት ነው ብሏል፡፡
የጋሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አመራሮች፣ ዛሬ ከሰዓት በኋላ 8 ሰዓት ላይ፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት ጽ/ቤት አዳራሽ ውስጥ፣ በአዲሱ የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች አደረጃጀት ዙሪያ መንግሥት እያደረገ ካለው እንቅስቃሴ ጋር በተገናኙ ጉዳዮች ላይ  ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
አዲሱን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመሰረቱት የጌዲኦ፣ የወላይታ፣ የጋሞ፣ ጎፋ፣ የኮንሶ፣ የደቡብ ኦሞ ዞኖች እንዲሁም የቡርጂ፣ የአማሮ፣ የደራሼ፣ የባስኬቶ እና የአሌ ልዩ ወረዳዎች መሆናቸው ይታወቃል፡፡
ይሁን እንጂ የጋሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የጋሞ ዞን በክላስተር የክልል አደረጃጀት ውስጥ መካተቱን እንደማይቀበለው ይገልጻል፡፡ የጋሞ ህዝብ ጥያቄ በክላስተር ልደራጅ የሚል አይደለም  ያለው ፓርቲው፤ ህዝቡ ራስን በራስ የማስተዳደር ህገ-መንግሥታዊ መብቱ እንዲከበርለት ነው የጠየቀው ብሏል፡፡
”የጋሞ ዞን ህዝብ ጥያቄ  ከማዕከልነት ጋር የተያያዘ ወይም የከተማ አመዳደብ ኢ-ፍትሃዊነት ጉዳይ አይደለም“ ያሉት የጋሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ቡንካሾ ሀንጌ፤የህዝቡ ጥያቄ የክልልነትና ራስን በራስ የማስተዳደር ህገ-መንግስታዊ ጥያቄ ነው ብለዋል፤ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ በሰጡት ማብራሪያ፡፡
“የጋሞን ህዝብ በክላስተር መደራጀት ይጎዳዋል የምንለው ያለምክንያት አይደለም” የሚሉት የህዝብ ግንኙነት ሃላፊው፤ “የጋሞ ህዝብ በፊት አዋሳ መጥቶ ነበር አገልግሎቶችን የሚያገኘው፤ በአዲሱ አደረጃጀት ግን አገልግሎት ለማግኘት ዲላ ድረስ መምጣት አለበት፤በዚያ ላይ ከአንድ ማዕከል አገልግሎቶችን ማግኘት የማይቻልበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡“ ሲሉ አስረድተዋል፡፡  
“በክላስተር መደራጀትን የተቃወምነው አርባምንጭ በአዲሱ የክልል አደረጃጀት ዋና  መቀመጫ ሳትሆን በመቅረቷ  ነው  ብለው የሚያወሩ አንዳንድ ወገኖች አሉ፤ ይሄ ግን ሃሰት ነው፡፡” ያሉት የፓርቲው የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ኤልያስ ዛለ በበኩላቸው፤ ህዝቡ ያቀረበው የማዕከልነት ጥያቄ ሳይሆን፣ “ክልላችን ጋሞ፣ ማዕከላችን አርባምንጭ” የሚል ነው ብለዋል፡፡  
ቲያቸውም ሆነ የጋሞ ህዝብ የማዕከልነትን ጥያቄ  እንዳላነሱ የገለጹት  የፓርቲው ም/ፕሬዚዳንት አቶ ዳሮት ጉምአ ጉጌ፤ “በክላስተር አደረጃጀት ማዕከል የሚባል ነገር ያለ አይመስልም፤ እኛ የጠየቅነው  የጋሞ ክልላዊ መንግሥትን የመመሥረት ህገ-መንግስታዊ መብታችንን ነው፤ ማዕከሉንም አርባምንጭ ማድረግ፡፡” ሲሉ በመግለጫው ላይ ተናግረዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ፤ “የጋሞ ሕዝብ በክልል የመደራጀትና ራስን በራስ የማስተዳደር ህገ-መንግሥታዊ መብቱ ይከበር፤ሕዝቡ ያቀረበው ህጋዊ ጥያቄም ሕገ-መንግሥታዊ መልስ ይሰጠው!” በሚል መሪ ቃል፣ ጋዴፖ  ባለ 7 ገጽ የአቋም መግለጫ በዛሬው ዕለት አውጥቷል፡፡
”የጋሞ ሕዝብ ከላይ እስከ ታች ባሉት መንግሥታዊ መዋቅሮቹና ምክር ቤቶቹ አጽድቆ ያቀረበው የጋሞ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የክልልነት ጥያቄ ሕገ-መንግሥታዊ ምላሽ ባላገኘበት ሁኔታ፣ በብልጽግና ካድሬዎች የሸፍጥ አሠራር የመጣን ክላስተር የክልል አደረጃጀት” እንደማይቀበለው በመግለጫው የጠቆመው  ጋዴፓ፤“መንግሥት ይህን ከግንዛቤ ውስጥ ያስገባ የማሻሻያ እርምጃ እንዲወስድ” በአጽንኦት ጠይቋል፡፡
“መንግሥት የጋሞን ሕዝብ ክልላዊና ሀገራዊ መብት፣ ጥቅምና ክብር በሕገ-መንግሥታዊ መንገድ ያላከበረውን የአዲሱን የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምሥረታ ሒደት ከማጣደፍ እንዲቆጠብ” ያሳሰበው ፓርቲው፤ “ይልቁንም የጋሞ ሕዝብን በጉዳዩ ዙሪያ ከላይ እስከ ታች የሚያወያይበትን አካታችና አሳታፊ መድረኮች በአስቸኳይ እንዲፈጥር“ በዚሁ መግለጫው ጠይቋል፡፡
አዲሱን አደረጃጀት  በመቃወም  ለነሐሴ  4 ቀን 2015 ዓ.ም በዞኑ  ሰላማዊ ሰልፍ ጠርቶ እንደነበር ያስታወሰው ጋዴፓ፤ ነገር ግን የዞኑ አስተዳደር ወታደራዊ ሃይል በማሰማራት፣ ለሰልፍ ከወጡት  400 ያህሉን ማሰሩን ጠቁሞ፣  የጋሞ ሕዝብ ኃሳቡን በነፃነት የመግለጽ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቱን የረገጡት የጋሞ ዞን አስተዳደርና የጋሞ ዞን ሰላምና ጸጥታ መምሪያ፣ በሕግ እንዲጠየቁና፣ ይህም መተግበሩን መንግስት ለሕዝብ እንዲገልጽ አሳስቧል፡፡


በሌላበኩል፤አዲሱ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ይ

ፋዊ የምስረታ በዓሉን በዛሬው ዕለት በአርባ ምንጭ ከተማ ሊያካሂድ  መሆኑ ተገለጸ። የነባሩ የደቡብ ክልል ምክር ቤትም በተመሳሳይ ቀናት አስቸኳይ ጉባኤ መጥራቱ ተዘግቧል፡፡
በአርባ ምንጭ ከተማ የሚካሄደው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምስረታ፣ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ነው ተብሏል፡፡ትላንት  በነበረው   መርሃ ግብርም፤ የአዲሱ ክልል ምክር ቤት መስራች ጉባኤውን  አድርጓል፡፡   
በዛራ ዕለት አዲሱ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በይፋ የምስረታ ፕሮግራሙን እንደሚያካሄድ ተጠቁሟል፡፡ የአዲሱ ክልል ርዕሰ መስተዳድርና የካቤኔ አባላትም  እንደሚሾሙ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡  
አዲሱን ክልል የመሰረቱት የወላይታ፣ የጋሞ፣ የጎፋ፣ የደቡብ ኦሞ፣ የጌዴኦ፣ የኮንሶ ዞኖች እንዲሁም የደራሼ፣ የአማሮ፣ የቡርጂ፣ የአሌ እና የባስኬቶ ልዩ ወረዳዎች ሲሆኑ፤ በአስራ አንዱ መዋቅሮች የተመሰረተው 12ኛው ክልል፤ ከነባሩ የደቡብ ክልል ምክር ቤት ስልጣን በይፋ የተረከበው ባለፈው ሐምሌ መጨረሻ  ላይ ነበር፡፡


Read 518 times