Saturday, 19 August 2023 21:07

ዳሽን ባንክ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው አለም አቀፍ ቨርቹዋል ካርድ አስተዋወቀ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

አዳዲስ ቴክሎጂዎችን ቀድሞ በማስተዋወቅና “ምንጊዜም አንድ እርምጃ ቀዳሚ” በሚለው መሪ ቃሉ የሚታወቀው ዳሽን ባንክ፣ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን ለውጪ ተጓዦች የሚያገለግል ዓለም አቀፍ ቨርቹዋል የመገበያያ ካርድ ከማስተር ካርድ ጋር በመተባበር አስተዋወቀ።
ካርዱ እስከዛሬ ከተለመደውና በስም ከሚታተመው የፕላስቲክ ካርድ የተለየና በሰማያዊ መደብ የተዘጋጀ ሲሆን፤ በተለይ ወደ ውጪ ሀገር የሚጓዙ ደንበኞች እንደ ልባቸው የሚገበያዩበት ሲሆን፤ በአገር ውስጥም ሆነው ዶላር ወደ ኢትዮጵያ ብር መመንዘር፣ መገበያየት፣ ያላቸውን ትራንዛክሽን ማወቅና ሁሉን ማድረግ ያስቻላቸው ተብሏል። ካርዱ አንዴ ለደንበኞች ከተሰጠ በኋላ የምስጢር ቁጥሮቹን ለመቀየር ወይም ቢሰረቅ ወዲያው አገልግሎት እንዲያቆም ለማድረግና ሌሎችም የደህንነት መጠበቂያዎች የተሰሩለት ስለመሆኑ በካርዱ ማስተዋወቂያ  ሥነ-ስርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት የዳሽን ባንክ ዋና ሥራ አስፈፀሚ አቶ አስፋው አለሙ ተናግረዋል።
ደንበኞች ካርዱን አንዴ ካገኙ በኋላ የሞሉት ገንዘብ ቢያልቅ ካርዱን መቀየር ሳያስፈልጋቸው እንደገና መሙላት እንደሚችሉ የገለፁት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፤ በአጠቃላይ ይህ ካርድ ከባቢያዊ ሁኔታን ያገናዘበና ሁኔታዎችን ቀላልና ምቹ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
ይህንን ካርድ ለማግኘት ወደ ውጪ ተጓዥ መሆን፣ የዳሽን ባንክ አካውንት ያለው መሆን፣ የጉዞ ቪዛ ፓስፖርትና አውሮፕላን ትኬት ይዞ መቅረብ የሚያስፈልግ ሲሆን፤ በዚህ ካርድ በኢ-ኮሜርስ  (በበይነ መረብ) ከአማዞንና ከሌሎችም የኦንላይ የመገበያያ መድረኮች ግብይት መፈፀም  የሚያስችል መሆኑ ተነግሯል።
የማስተር ካርድ ፔይመንት ጌትዌይ ካርድን ነጋዴዎች መጠቀም ካስፈለጋቸው፣ ህጋዊ ዌብሳይት (ድረ-ገጽ)፣ ሞባይል መተግበሪያ፣ የነጋዴው ድርጅት በህጋዊ መንገድ የሚሰራ ስለመሆኑ የሚያረጋግጥ የኢንሳ  ሰርትፍኬትና ዳሽን ባንክና ነጋዴው የሚግባቡበት የመብት ግዴታ የውል ስምምነት ማድረግ እንደሚያስፈልግም ተገልጿል።
በማስተዋወቂያ ሥነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የማስተር ካርድ የምስራቅ አፍሪካ የኢትዮጵያ ተጠሪ ሽህርያር አሊ ባደረጉት ንግግር እንዳብራሩት፤ ማስተር ካርድ ከዳሽን ባንክ ጋር ያደረገው ጥምረት በኢትዮጵያ እንደ አለም አቀፍ ካርድ ያሉ አገልግሎቶችን በማስተዋወቅ ማህበረሰቡ ይበልጥ የዲጅታል አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከፍተኛ ሚና እንደሚያበረክት ተናግረዋል።
በዳሽን ባንክ የቅድመ ክፍያ ማስተር ካርድ ደንበኞች ከኤቲኤምና ከፖስት ማሽን በተጨማሪ በኢ-ኮሜርስ ክፍያ መክፈል ይችላሉ ተብሏል።
ዳሽን ባንክና ማስተር ካርድ ከካርዱ በተጨማሪ የንግድ ተቋማት ክፍያቸውን በበይነ መረብ ከየትኛውም የዓለም ክፍል መቀበል የሚያስችል የማስተር ካርድ ክፍያ መቀበያ ማስተር ካርድ ጌትዌይ ሲስተም ያለው ሲሆን በአጠቃላይ ካርዱ ሶስት አይነት አገልግሎቶችን በአንድ ላይ የያዘ ዘመናዊና የተለያየ አማራጭ ያለው ስለመሆኑ ተብራርቷል።
ዳሽን ባንክ በዚህ የማስተር ካርድ ፕሮጀክትና በቴክኒክ ስራ ላይ ለተሳተፉ ሰራተኞቹ እውቅናና ሽልማት አበርክቷል። ማስተር ካርድ በዓለም አቀፍ ደረጃ በ210 አገራት ውስጥ ክፍያ የሚፈጸምና ከ1.9 ቢሊዮን በላይ ደንበኞችን ያፈራ መሆኑ ተገልጿል።

Read 1232 times