Saturday, 19 August 2023 21:08

የአፍሪካ ህብረት በአማራ ክልል የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጥሪ አቀረበ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

ተፋላሚ  ወገኖች ግጭቱን አቁመው ወደ ንግግር እንዲገቡም ጠይቋል
- በክልሉ የተከሰተው ግጭት በሰላማዊ መንገድ እንዲቋጭ ኢሰመኮ የተለያዩ የእምነት ተቋማት አሳሰቡ።

  በአማራ ክልል በመከላከያ ሰራዊትና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የተፈጠረውና የብዙዎችን ህይወት የቀጠፈው ግጭት በእጅጉ እንዳሳሰበውና ተፋላሚ ወገኖች ግጭቱን በአስቸኳይ አቁመው የሰላማዊ ዜጎችን ደህንነት እንዲያስጠብቁ የአፍሪካ ህብረት ጥሪ አቀረበ፡፡
የህብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳፋኪ ማጣማት ባወጡት መግለጫ እንዳመለከቱት፤ በክልሉ ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች ውጊያውን አቁመው፣ ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ እንዲወያዩም ጠይቀዋል፡፡
የኢትዮጵያን ሁኔታ በቅርበትና በከፍተኛ ስጋት እየተከታተሉ እንደሆነ ያመለከቱት ሊቀመንበሩ ሁለቱም ወገኖች ጦርነቱን በአስቸኳይ አቁመው የሰላማዊ ዜጎችን ከለላ እንዲያረጋግጡ አሳስብዋል፡፡
የአፍሪካ ህብረት ለኢትዮጵያ ህገመንግስታዊ ስርዓት፣ ለግዛት አንድነትና ሉአላዊነት ቀናዒነት እንዳለው የገለፁት ሊቀመንበሩ፤ ህብረቱ በአገሪቱ እንዲሁም በቀጠናው ውስጥ መረጋጋት እንዲሰፍንና ለዚህም በኢትዮጵያ ተነሳሽነት ለሚደረግ የሰላም መፍትሄ ድጋፍ እንደሚሰጥ አመልክተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ሳምንቱ መጀመሪያ ላይ ባወጣው ሪፖርት የምስራቅ አፍሪካ የጋራ ልማት ባለስልጣን (ኢጋድ)፣ የአፍሪካ ህብረት የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና አለማቀፍ ማህበረሰብ ሲል  የጠራቸው አካላት በአማራ ክልል ታጣቂዎችና በመንግስት መካከል የውይይት መድረክ እንዲያመቻቹ ጥሪ አስተላልፏል፡፡

Read 1202 times