Saturday, 19 August 2023 21:10

መንግስት በአማራ ክልል ለተፈጠረው ችግር መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ በሃይል ለመፍታት ሞክሯል - ተቀዋሚ ፓርቲዎች

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

ከተበተኑት የአማራ ክልል ልዩ ሃይል አባላት መካከል አብዛኛዎቹ ታጣቂ ቡድኑን ተቀላቅለዋል
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሳቢያ የሚካሄዱ የጅምላ እስሮች ተበራክተዋል
በከተማዋ በተለያዩ ት/ቤቶች ውስጥ የታሰሩ ሰዎች መኖራቸውን የሰላም ሚኒስትሩ ተናግረዋል
በመዲናዋ የሚካሄዱ እስሮች በከተማዋ አስተዳደር የሚፈፀሙ ናቸው ተብሏል

መንግስት  በአማራ ክልል ለተከሰተው የፀጥታ ችግር ሰላማዊ መፍትሄ ከመፈለግ ይልቅ ችግሩን በሃይል ለመፍታት ሞክሯል ያሉት ተቃዋሚ ፓርቲዎች፤ በዚህም ሳቢያ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ተናገሩ። በአሁኑ ወቅት በክልሉ ለተከሰተው ችግር መፍትሄው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገግ ሳይሆን ሰላማዊ ድርድር ማካሄድ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡
በሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ ብናልፍ አንዱአለምና በእንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል በተመራውና ሰሞኑን በካፒታል ሆቴል ተካሂዶ በነበረው ስብሰባ ላይ 16 የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡
የሰላም ሚኒስትሩ አቶ ብናልፍ አንዱአለም በዚህ ወቅት ባደረጉት ንግግር፤ በአማራ ክልል የልዩ ሃይል አባላትን ወደ ሌሎች የፀጥታ መዋቅሮች የማስገባት ስራ ከተጀመረ በኋላ 50 በመቶ ያህሉ የልዩ ሃይል አባላት እንደተበተኑና ከእነዚህ ውስጥ አብዛኛዎቹ ታጣቂ ሃይሉን እንደተቀላቀሉ ገልፀዋል፡፡
አቶ ብናልፍ፤ አክለውም በአማራ ክልል የተከሰተው ግጭት በድንገት የተፈጠረ ነው የሚል እምነት እንደሌላቸውና በተለያዩ ጊዜያት የሚነሱና እየተደመሩ የመጡ ችግሮች መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡ ለችግሩ መባባስ ምክንያት  ናቸው ያሏቸውን ጉዳዮች ሲዘረዝሩም፤ የፍትሃዊ ተጠቃሚነትና የእኩልነት ጥያቄ፣ የወሰንና የማንነት ጉዳዮችና የፈለጉትን የፖለቲካ ሃሳብ ለማራመድ የሚያስችል ሁኔታ አለመኖር ዋንኞቹ ናቸው ብለዋል፡፡
ከወሰንና ማንነት ጋር የተያያዘው ጥያቄ ምላሽ እያገኘ አይደለም የሚል ቅሬታ መነሳቱን የገለፁት የሰላም ሚኒስትሩ፤ በክልሉ አመራር ላይ ክፍተት መኖሩም ለችግሩ መባባስ ምክንያት እንደሆነ አመልክተዋል፡፡
የክልል ልዩ ሃይል አባላትን ወደ ሌሎች የፀጥታ መዋቅሮች በማስገባቱ ስራ ከክልሉ ልዩ ሃይል አባላት 50 በመቶ ያህሉ መበተናቸውን የጠቆሙት የሰላም ሚኒስትሩ፤ ከተበተነው ሃይል አብዛኛው ታጣቂ ቡድኑን መቀላቀሉን ተናግረዋል።
በስብሰባው ላይ ከታደሙት የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች አብዛኞቹ በአማራ ክልል ለተከሰተው ችግር መንግስትን ጥፋተኛ በማድረግ ወቀሳ ሰንዝረዋል። መንግስት በክልሉ ለተፈጠረው ችግር አስቀድሞ መፍትሄ ከመፈለግ ይልቅ ችግሩን በሃይል ለመፍታት መሞከሩንም የተቃዋሚ ተወካዮቹ ተናግረዋል፡፡
በክልሉ ለተለፈጠረው ችግር መፍትሄው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገግ አይደለም ያሉት ፓርቲዎቹ፤ ለችግሩ መፍትሄ የሚሆነው ሰላማዊ ድርድር ማካሄድ ብቻ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
በሰላም ሚኒስትሩና በኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ የተሰጠውን የወቅታዊ ሁኔታ መግለጫ ከሰሙ በኋላ የተለያዩ ጥያቄዎችን ያቀረቡት የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካዮቹ፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁንና በአገሪቱ በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወኑ የሚገኙትን የጅምላ እስሮችን የተመለከቱ ጥያቄዎችን ሰንዝረዋል፡፡
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሳቢያ የጅምላ እስር እየተካሄ መሆኑን የገለፁት የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካዮቹ፣ የአዋጁ መውጣት በተለያዩ አካባቢዎች ለሚገኙ አመራሮች ትላንት የጠሉትን ሰው ለማሰር ምቹ ሁኔታን ፈጥሮላቸዋል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ተወካይና ዋና ፀሃፊው አቶ አበበ አካሉ በዚሁ ስብሰባ ላይ በሰጡት አስተያየት፤ በአማራ ክልል ለተከሰተው ችግር መፍትሄው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ ሳይሆን ሰላማዊ ድርድር ማድረግ ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዲሞክራቲክ ህብረት (ኢዲህ) ሊቀመንበሩ አቶ ገብሩ በርሄ በበኩላቸው፤  የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በአገሪቱ በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ለበርካቶች እስር መንስኤ እንደሆነ ጠቁመው፤ “በአዲስ አበባ ከፍተኛ አፈሳ አለ፤ በርካታ ህዝብ ታፍሶ እየታሰረ ነው፤ ት/ቤቶች በጅምላ የታፈሱና የታሰሩ ሰዎች ማጎሪያ ሆነው ሰንብተዋል” ብለዋል፡፡
 የፖርቲያቸው አባላትም ወንድራይድ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ውስጥ ታስረው መቆየታቸውን አክለዋል። በከተማዋ የተለያዩ ት/ቤቶች በርካታ ዜጎች ታስረው የሚገኙ ቢሆንም መንግስት ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በሰጠው መግለጫ፣ በኮማንድ ፖስቱ 23 ግለሰቦች ብቻ መታሰራቸውን መናገሩ ግራ እንዳጋባቸውና እነዚህን ሰዎች ያሰራቸው ማነው የሚል ጥያቄ እንዳጫረባቸው ገልፀዋል፡፡
ከተቃዋሚ ፓርቲ ተወካዮች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት ሁለቱ ሚኒስትሮች፤ በአገሪቱ በተለይም በከተማይቱ አዲስ አበባ ከፍተኛ የጅምላ እስር እየተካሄደ መሆኑን አምነዋል፡፡
የሰላም ሚኒስትሩ አቶ ብናልፍ አንዱአለም፤ በአገሪቱ በተለይም በከተማዋ አዲስ አበባ እየተካሄደ የሚገኙት እስሮች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስቱ የሚከናወኑ እንዳልሆነና እስሮች እየተፈፀሙ ያሉት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሆኑን ጠቁመው ይህንን ጉዳይ አስመልክቶም በመንግስት ደረጃ ንግግሮች እየተካሄዱ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
“የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስቱ በሚዲያ በግለጫ የሰጠባቸው በኮማንድ ፖስቱ የተያዙትን ብቻ ነው፤ ነገር ግን ከዚያ በላይ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በተለያዩ ት/ቤቶች ታስረው ይገኛሉ” ብለዋል- የሰላም ሚኒስትሩ፡፡
የእንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል በበኩላቸው በአዲስ አበባ ከተማ የሚታየው የጅምላ እስር በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ኮማንድ ፖስት ሳይሆን በከተማዋ አስተዳደር በኩል መሆኑን ሰምተናል፤ እዚያ አካባቢ ያሉ ችግሮች እንዲታረሙ እናደርጋለን ብለዋል፡፡
የህግ የበላይነት ለማረጋገጥ የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሰበብ በማድረግ፣ ሰው በማንነቱና በፖለቲካ አመለካከቱ የሚታሰርበት አገር ማየት አንፈልግም ብለዋል፡፡
የፌደራል ፖለስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ በሳምንቱ መጨረሻ በሰጡት መግለጫ፤ ከ23 ተጠርጣሪዎች ውጪ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስቱ የተያዘ ሰው አለመኖሩን የገለፁ ቢሆንም፤ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፣ በአዲስ አበባ ከተማ የአማራ ክልል ተወላጆችና ኤርትራውያን ስደተኞች በስፋት እየታፈሱና እየታሰሩ መሆኑን ከሰሞኑን መግለጹ ይታወሳል፡፡

Read 1363 times