Wednesday, 23 August 2023 19:42

ጤና፣ ልማትና ጸረ ወባ ማህበር፤ የተመሠረበትን 25ኛ ዓመት የኢዮቤልዩ በዓል ማክበር ጀመረ

Written by  -ሪፖርታዥ-
Rate this item
(1 Vote)

•  ባለፉት 25 ዓመታት የብዙ መቶ ሺዎችን ህይወት ታድጓል

•  በቀጣይ ወራት የወባ ወረርሽኝ ሊከሰት እንደሚችል ተገለጸ

ጤና፣ ልማትና ጸረ-ወባ ማህበር (ጤልጸወማ)፤የተመሰረተበትን  የ25ኛ ዓመት የኢዮቤልዩ በዓል፤ አባላት፣ በጎ ፈቃደኞችና የመገናኛ ብዙኃን በተገኙበት፣ በዛሬው ዕለት ከረፋዱ 4 ሰዓት ጀምሮ በኢንተር ሌግዠሪ ሆቴል ማክበር ጀምሯል፡፡

የዛሬው የ25ኛ ዓመት በዓሉን ለማክበር የማስጀመርያ መርሃግብር መሆኑ የገለጹት ሃላፊዎቹ፤ የፊታችን መስከረም መጨረሻ ላይ በተለያዩ ዝግቶች የኢዮቤልዩ በዓሉ በድምቀት እንደሚከበር አስታውቀዋል፡፡   

የዛሬ 25 ዓመት በምዕራብ ጎጃም የተከሰተውን የወባ ወረርሽኝ ለመቀልበስ በማለም በ8 በጎ ፈቃደኞች ወደ ሥራ መግባቱን ያስታወሱት  የማህበሩ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አበረ፤ ማህበሩ በአሁኑ ወቅት  ከ260ሺ በላይ አባላትና በጎ ፈቃደኞችን እንዳፈረ አስታውቀዋል፡፡

ወባ ቁጥር 1 ገዳይ በሽታ እንደነበር የጠቆሙት ዶ/ር አበረ፤በወቅቱ  በምዕራብ ጎጃም በአንድ ቤተ ክርስትያን ውስጥ  በቀን እስከ 13 ሰው ድረስ ይቀበር እንደነበር  አስታውሰዋል፡፡

 በአማራ ክልል የተከሰተውን የወባ ወረርሽኝ ተከትሎ፣ ማህበሩ ተመስርቶ ወደ ሥራ ይግባ እንጂ ባለፉት 25 ዓመታት በመላው ኢትዮጵያ ችግሮች በተከሱበት ሁሉ እየተዘዋወረ ድጋፍና አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፤ማህበሩ ለአንድ ክልል ወይም ብሔረሰብ የተቋቋመ ሳይሆን ህብረ ብሄራዊ ነው ብለዋል፤አጽዕኖት በመስጠት፡፡

ባለፉት 25 ዓመታት ማህበሩ ያከናወናቸውን አንኳር አንኳር ተግባራት ያስቃኙት የጤልጸወማ ዋና ዳይሬክተር፤ ማህበሩ የተመሰረተበት ዋና ዓላማ ከሆነው ወባን የመከላከልና የማጥፋት እንቅስቃሴዎቹ  በተጨማሪ በንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትና 10 ሺ ለሚሆኑ ወላጆቻቸውን ያጡ ህጸናት ልዩ  ድጋፍ በመስጠት ብቁ  ዜጎችን በማፍራት እንዲሁም  ለሴተኛ አዳሪዎች  የተለያዩ የክህሎት ሥልጠናዎችን በመስጠት ህይወታቸውን በመለወጥ በኩል ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱን  አስረድተዋል፡፡   

የዛሬ 25 ዓመት ማህበሩን ከመሰረቱት አባላት ጥቂቶቹ እንዲሁም  በቅርበት የሚያውቁ ባለድርሻ አካላት ከምስረታ እስካሁን ያለውን የማህበሩን ጉዞ የተመለከተ ግሩም ምስክርነት ለታዳሚው ሰጥተዋል፡፡

“የዚህ ማህበር አነሳስና ጉዞ በመጽሐፍ መልክ ቢዘጋጅ፣ ለቀጣዩ ትውልድ አስተማሪና አነቃቂ ሊሆን ይችላል፡፡” ብለዋል፤ከማህበሩ መሥራቾች አንዱ፡፡

ባለፉት በርካታ ዓመታት ከማህበሩ ጋር  በቅርበት ሲሰራ የቆየው  የ“ማላሪያ ኮንሶርቲየም ኢትዮጵያ“  ተወካይ  ዶ/ር አጎናፍር ተካልኝ በበኩላቸው፣ በቀጣዩ የማህበሩ ጉዞ መከናወን አሉባቸው ያሏቸውን ተግባራት ዘርዝረዋል፡፡

ወባ የፖለቲካ አጀንዳ (ትኩረት) እንዲሆን እየተሰራ እንደሚገኝ የጠቆሙት ዶ/ር አጎናፍር፤ማህበሩ የህብረሰቡ ልሳን ሆኖ መቀጠል እንዳለበት እንዲሁም ድርጅቶችን ወክሎ ስለወባ የሚናገረውንም  መቀጠል እንደሚገባውም ተናግረዋል፡፡ ሃብት ማሰባሰብን በተመለከተም፣ ሁልጊዜ ከውጭ ለምነን አንችለውም ያሉት የኮንሰርቲየሙ ተወካይ፤ ከሃገር ውስጥ ሃብት ማሰባሰብ የምንችልበትን ስልት መዘየድ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡

 በተቆራረጠ የዝናብ ወቅት የወባ ወረርሽኝ  እንደሚጨምር  የገለጹት  ዶ/ር አጎናፍር ተካልኝ፤ማህበረሰቡ ራሱን በወባ በሽታ ምክንያት ሊከሰት ከሚችለው ህመምና ሞት እንዲጠብቅ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡

በመጪው ወራት የወባ ወረርሽኝ  ለምን እንደሚጨምር  ያብራሩት ዶ/ር አጎናፍር፤ ከግጭቱ ጋር ተያይዞ የተፈጠረውን መፈናቀል እንዲሁም  በዓለም ላይ የታየውን የአየር ንብረት ለውጥ በምክንያትነት ጠቅሰው፤ የወባ ትንኝና ተህዋሲያት መላመድም ሌላው ችግር ነው ብለዋል፡፡

“ህብረተሰቡ በእጅጉ ተዘናግቷል፤እናቶችና ህጻናት ትኩሳት ሲሰማቸው ኮቪድ ነው እያሉ ወደ ሆስፒታል መሄድ ትተዋል” ያሉት ዶ/ር አጎናፍር፤ ህብረተሰቡን በማንቃት ረገድ ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

ጤና፣ ልማትና ጸረ-ወባ ማህበር ፤የወባ ወረርሽኝ በወገን ላይ እያስከተለ የነበረውን ጉዳት ለመከላከልና ምላሽ ለመስጠት፣ በ1990 ዓ.ም የተቋቋመ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ነው፡፡

መንግሥት ከዓለማቀፍ አጋሮች ጋር እጅ ለእጅ በመሥራት፣ብሔራዊ የወባ ማጥፊያ ስትራቴጂክ ዕቅድ የቀረጸ  ሲሆን፤ ግቡም እ.ኤ.አ በ2030 በሽታውን ሙሉ በሙሉ ከአገሪቱ ሁሉም አካባቢዎች ማጥፋት ነው ተብሏል፡፡

ማህበሩ፤ በተጨማሪም፣ በፋብሪካ የተቀነባበሩና የታሸጉ፣ ጤናማ ያልሆኑ ምግቦች ወደ ሃገራችን በብዛት እየገቡ መሆኑንና  እነዚህን ምግቦችና መጠጦች አዘውትሮ በመውሰድ የሚከሰቱ ተላላፊ ያልሆኑ ህመሞች እየጨመሩ መምጣታቸውን በተደጋጋሚ በማስታወቅ፣ ህብረተሰቡ ከመሰል ምግቦች እንዲታቀብ ግንዛቤ እየሰጠ እንደሚገኝም ይታወቃል፡፡

Read 1374 times