Sunday, 27 August 2023 19:35

ከ4 ሚ. በላይ ኢትዮጵያውያን ከቀዬአቸው ተፈናቅለዋል

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(1 Vote)

በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ከ4 ሚሊዮን በላይ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች እንደሚገኙ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ድርጅት ባወጣው አዲስ ሪፖርት አስታወቀ። ድርጅቱ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ አደረኩት ባለው ጥናትና ግምገማ፣ ከ4.38 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን ከመኖሪያ ቀዬአቸው ተፈናቅለው በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች እንደሚገኙ አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡
ድርጅቱ ካለፈው ህዳር ወር እስከ ሰኔ ወር ድረስ ባሉት ጊዜያት ውስጥ በተደረገ ግምገማና ጥናት አረጋገጥኩት ባለው ሪፖርቱ፤ ለዜጎች መፈናቀል ከቀረቡት ምክንያቶች መካከል ዋንኛው ግጭት እንደሆነም አመልክቷል፡፡ በአገሪቱ በተለይም ከሁለት ዓመታት ወዲህ የተከሰቱ ግጭቶችና ጦርነቶች ለበርካታ ዜጎች ከመኖሪያቸው መፈናቀል ምክንያት እንደሆነ ያመለከተው የድርጅቱ ሪፖርት፣ በተጨማሪም ድርቅና ረሃብ፣ እንዲሁም የዝናብ እጥረትና በማህበረሰቦች መካከል የሚያጋጥም ውጥረት ለዜጎች መፈናቀል በምክንያትነት ተጠቅሷል፡፡
የመንግስታቱ ድርጅት ያወጣው ብሔራዊ የተፈናቃዮች ሪፖርት፣ በጦርነት ውስጥ የቆየውን የትግራይ ክልልን ያካተተ ሲሆን በአገሪቱ በግጭት ምክንያት ከተፈናቀሉ ሰዎች መካከል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዜጎች የሚገኙት በትግራይ ክልል መሆኑንም አመልክቷል። ከግጭቶች ውጭ በአገሪቱ ለተከታታይ አመታት ባጋጠመው ድርቅ ሳቢያ የተፈናቀሉ ወገኖች ቁጥርም ከፍተኛ መሆኑን የጠቆመው የድርጅቱ ሪፖርት፤ የሶማሌ ክልል በርካታ የድርቅ ተፈናቃዮች የሚገኙበት እንዲሆነም አመልክቷል፡፡ በአገሪቱ የተለያዩ ክልሎች ከመኖሪያ ቀዬአቸው ተፈናቅለው ከሚገኙ ዜጎች በተጨማሪ በተለያዩ ችግሮች ሳቢያ ለረሃብ ተጋላጭ የሆኑ 20 ሚሊዮን የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን የምግብ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ያለው የመንግስታቱ ድርጅት፤ ለዚህም 4 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልገኛል ብሏል፡፡

Read 1670 times