Tuesday, 12 September 2023 18:06

የአውዳመት ምሣ - በሙዳይ በጎ አድራጎት

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

•  ድርጅቱ ለቤት ኪራይ ብቻ በወር 250ሺ ብር እያወጣ ነው ተባለ

•  ከአስተዳደሩ ቦታ ቢሰጠውም በፋይናንስ እጥረት ግንባታ አልጀመረም  

ሙዳይ በጎ አድራጎት ድርጅት እንደወትሮው ቢሆን ኖሮ፣ ለሚደግፋቸው ከ1ሺ100 በላይ ችግረኛ ወገኖች ለዓመት በዓል ዱቄትና ዘይት እንዲሁም የበሬ ቅርጫ የመሳሰሉ የአውዳመት ፍጆታዎችን በያሉበት ያከፋፍላቸው ነበር፡፡ ዘንድሮ ግን በኑሮ ውድነቱ ሳቢያ የተለመደውን ችሮታ ማድረግ አለመቻላቸውን የበጎ አድራጎት ድርጅቱ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ሙዳይ ምትኩ ይናገራሉ፡፡

ይህን ችግራቸውን ያማከሩት ጋዜጠኛ ተሻለ ጣሰው፣ በመጨረሻ ሰዓት፣ በሬ ገዝቶና ሙሉ ወጪውን ችሎ፣ አዲስ ዓመትን ከ100 በላይ ከሚሆኑ ተረጂ ወገኖች ጋር ምሳ እየበላን በደስታ እንድናሳልፍ አድርጎናል ሲሉ  ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

የድርጅቱ መሥራች ይህን የተናገሩት፣ በዛሬው ዕለት፣ ኮተቤ በሚገኘው የሙዳይ በጎ አድራጎት ድርጅት ግቢ ውስጥ ተረጂ ወገኖችን ምሣ የማብላት ሥነስርዓት ከተከናወነ በኋላ ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቆይታ ነው፡፡

የበጎ አድራጎት ሥራ ከጀመረ 23 ዓመታትን ያስቆጠረው ሙዳይ በጎ አድራጎት ድርጅት፤ በአሁኑ ወቅት ከ1ሺ100 በላይ ለሚሆኑ ችግረኛ ወገኖች የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ የሚገኝ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 650 ያህሉ ህጻናት መሆናቸው ታውቋል፡፡

ድርጅቱ የራሱ የሆነ ማዕከል ስለሌለው ለሚደግፋቸው ወገኖች የቤት ኪራይ ብቻ  በወር 250ሺ ብር እንደሚያወጣ መሥራቿ ይናገራሉ፡፡ ይህን ችግራቸውን የተረዳው የአዲስ አበባ አስተዳደር ታዲያ ዝም አላላቸውም፡፡ በአቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማና በሃያት አካባቢ በአጠቃላይ  4ሺ ካሬ ቦታ እንደሰጣቸው ገልጸዋል፡፡

የከተማው አስተዳደር ቦታውን መስጠት ብቻ ሳይሆን ግንባታውንም ለማከናወን በወቅቱ ቃል መግባቱን ነው ወ/ሮ ሙዳይ የሚናገሩት፡፡ ሆኖም አስካሁን ግንባታው ባለመጀመሩ ለከፍተኛ ችግር ተዳርገናል ብለዋል፡፡

የራሳችንን ማዕከል በፍጥነት መገንባት ብንችል ቢያንስ የቤት ኪራይ ወጪያችንን በመቀነስ ለተጨማሪ ችግረኛ ወገኖች መድረስ እንችል ነበር ያሉት ወ/ሮ ሙዳይ፤ ኢትዮጵያውያን ከአንድ ምስማር ጀምሮ የአቅማቸውን በማዋጣት ግንባታውን እውን ያደርጉላቸው ዘንድ ተማጽነዋል፡፡

“ሙዳይ በጎ አድራጎት ከ1ሺ100 በላይ ተረጂ ወገኖችን ቤት ተከራይቶና ቀለብ ቆርጦ እንዴት ነው የሚያኖረው?” በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ወ/ሮ ሙዳይ ሲመልሱ፤ የተለያዩ የባልትና ውጤቶችን ለአገር ውስጥና ለውጭ  በማቅረብ እንዲሁም በከብት እርባታ ላይ በመሰማራት  ከሚያገኙት ገቢ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ በተለይ “ሙዳይ እንጀራ” በከተማዋ እንደሚታወቅ የጠቆሙት ወ/ሮ ሙዳይ፤ ይሄ ሥራ ከ1ሺ በላይ ለሚሆኑ እናቶችም የሥራ ዕድል መፍጠሩን አክለው ገልጸዋል፡፡    

አቅሙ ያላቸው ኢትዮጵያውያን በወር 500 ብር ስፖንሰር በማድረግ አንድ ልጅ ማሳደግ እንደሚችሉ የጠቆሙት የበጎ አድራጎት መሥራቿ፤ በ9923 አጭር መልዕክት ሙዳይን እንዲደግፉም ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም ያለምንም ተጨማሪ ክፍያ በ9923 አጭር መልዕክት ድርጅቱ ድጋፍ እንዲያገኝ በማድረጉም ምስጋቸውን ያቀረቡት ወ/ሮ ሙዳይ ምትኩ፤አዲሱ ዓመት ለመላው ኢትዮጵያውያን የሰላም፣ የፍቅር፣ የመተሳሰብና የመደጋገፍ እንዲሆን ተመኝተዋል፡፡

Read 1452 times