Saturday, 16 September 2023 00:00

መንግስት በአማራ ክልል የጣለውን የኢንተርኔትእገዳ በአስቸኳይ እንዲያነሳ ተጠየቀ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(2 votes)

 - በክልሉ ከነሐሴ ጀምሮ የተወሰደው ኢንተርኔትን የማቋረጥ እርምጃ ዓለም አቀፍ ህግን የጣሰ ነው ተብሏል
      - ባለፈው ዓመት ብቻ መንግስት በአገሪቱ ለ3 ጊዜያት ያህል ኢንተርኔት ማቋረጡም ተጠቁሟል፡፡
       
         ከ105 አገራት የተውጣጡ ከ300 በላይ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች፣ መንግስት በአማራ ክልል ላይ የጣለውን የኢንተርኔት እገዳ እንዲያነሳና በክልሉ የተቀሰቀሱ ግጭቶችና አለመረጋጋቶችን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ጥሪ አቀረቡ፡፡
በግጭት ወቅት የኢንተርኔት አገልግሎትን ማቋረጥ የዜጎችን ህይወት አደጋ ላይ የሚጥልና አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን እንዳያገኙ የሚያደርግ ተግባር እንደሆነም ገልፀዋል፡፡
አለማቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶቹ በጋራ ባወጡት መግለጫቸው ላይ እንደጠቆሙት፤ በክልሉ ካለፈው ነሐሴ ወር ጀምሮ በመንግስት የተወሰደው የኢንተርኔት አገልግሎትን የማቋረጥ እርምጃ የአለም አቀፍ ህግን የጣሰና የሰብአዊ መብት ጥሰትም ነው ብለዋል፡፡ በክልሉ የተቀሰቀሰው ግጭት እየተባባሰና የፀጥታው ሁኔታ እያሽቆለቆለ በሄደ ቁጥር በክልሉ የሚገኙ ዜጎች ከመላው አለም ጋር በመገናኘት የደረሰውን ሞትና የተፈፀመውን የመብት ጥሰት ለአለም ማሳወቅ ይኖርባቸዋል ያለው የድርጅቶቹ የጋራ መግለጫ ይህ እንዳይሆን በመንግስት በኩል የተወሰደው የኢንተርኔት መዝጋት እርምጃ ህገወጥ ነው ብሏል፡፡
በተለያዩ ጊዜያትና አጋጣሚዎች በኢትዮጵያ ግጭትና ቀውስ ሲያጋጥም የኢንተርኔት አገልግሎትን ማቋረጥ በመንግስት በኩል የተለመደ ጉዳይ ነው ያሉት ድርጅቶቹ፤ በትግራይ ክልል ተከስቶ በነበረው ግጭት ሳቢያ የኢንተርኔት አገልግሎት ለአመታት ተቋርጦ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡ ባለፈው ዓመት ብቻ በግጭትና ቀውሶች መቀስቀስ ሳቢያ በአገሪቱ ለሦስት ጊዜያት ያህል የኢንተርኔት አገርልግሎት ተቋርጦ መቆየቱንም ድርጅቶቹ በመግለጫቸው ጠቁመዋል፡፡ ግጭቶች በተነሱ ቁጥር ኢንተርኔት የማቋረጥ ልማድ መሻሻል ይገባዋል ያሉት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶቹ በአማራ ክልል ተዘግቶ የቆየው የኢንተርኔት አገልግሎትም በአስቸኳይ እንዲጀመር ጠይቀዋል፡፡ ግጭትንና አለመግባባቶች በሰላማዊ መንገድ የሚፈቱበት  መንገድ እንዲፈለግም ድርጅቶቹ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡ በአማራ ክልል በመንግስትና በፋኖ ታጣቂ ሃይሎች መካከል የተቀሰቀሰውን ግጭት ተከትሎ፣ በክልሉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከታወጀ በኋላ የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲቋረጥ መደረጉ የሚታወስ ነው፡፡


Read 1781 times