Friday, 22 September 2023 00:00

“እዚህ አገር ጋዜጠኝነት ድህነት ነው”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የኢትዮጵያ አርታኢያን ማህበር (Editors Guild of Ethiopia) “የጋዜጠኞች የአኗኗር ሁኔታ በኢትዮጵያ፡ በዋናነት የጋዜጠኞች የተሻለ ክፍያ ወደሚያስገኙ ስራዎች መፍሰስ” በሚል ርዕስ  ሳምንታዊ የቁርስ ላይ ውይይቱን ከትላንት በስቲያ ሐሙስ  ጠዋት በሂልተን ሆቴል አካሄደ።
በውይይቱ ላይ በእንግድነት የታደሙት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የቦርድ አባል የሆኑት አምባሳደር መሃመድ ድሪር ባስተላለፉት  መልዕክት፤ “ሚዲያ አንድ ትልቅ ራሱን የቻለ መንግሥት ነው…. ጥሩ መንግሥት ሲያገኝ ያብባል፤ ጥሩ መንግስት ሳያገኝ ሲቀር ደግሞ ይሸሻል፤ ይሰደዳል። የኢትዮጵያ ሚዲያ ባለመጎልበቱ ሣቢያ ያጣናቸው ብዙ ነገሮች አሉ፡፡” ብለዋል፡፡
ውይይቱ ለሙያው መጎልበት ትልቅ አቅም እንደሚሰጥ የጠቆሙት አምባሳደር  መሃመድ፤ መድረኩ በሙያተኞቹ  ብቻ ባይወሰንና  ከዩኒቨርሲቲ  ወይም ከሌሎች  ተቋማት  የሚመጡ ምሁራንም ሃሳባቸውን የሚያጋሩበት  መድረክ ቢሆን ጠቃሚ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ለዕለቱ  የማህበሩ ስብሰባ የውይይት መነሻ ሃሳብ ያቀረቡት  ጋዜጠኛ መሰለ ገ/ህይወት  ባቀረቡት ፅሁፍ፤ “ዛሬ በአገራችን አንጋፋ ጋዜጠኞች በብዛት አይታዩም፤ ብቃት ያለው ኤዲተር እጥረት ይስተዋላል፤ ጋዜጠኝነት የጀማሪና የወጣት ብቻ ሙያ እየሆነ መጥቷል፤ ወጣቶቹ ከአንጋፋዎቹ ልምድ እየወሰዱ አይደሉም፤” የሚሉ አንኳር ጉዳዮችን አንስተዋል፡፡
ኤዲተሮች የይዘት ኢንጂነሮች (Contents developers and builders) ናቸው ያሉት ጋዜጠኛ መሰለ፤ ይዘት የሚወሰነውና ተጣርቶ የሚያልፈው በእነሱ አማካኝነት ነው ሲሉ የአርታኢያንን ጠቀሜታ አመልክተዋል፡፡
አንጋፋ ኤዲተሮች በተቋማቸው ያሉባቸውን ችግሮችም  ሲጠቅሱ፤ በተለያየ ሙያ ሰልጥነው ለመጡ ሃላፊዎች ፈተና መሆናቸውን እንዲሁም ራሳቸው እንደፈለጉ ለመስራት እንቅፋት እንደሚሆኑባቸው አብራርተዋል፡፡
ጋዜጠኛ መሰለ ገ/ህይወት፣ “ኤዲተሮች በተቋማቸው ረዥም ዓመታት ለምን አይቆዩም?” የሚል ጥያቄም በማንሳት መልስ ለመስጠት ሞክረዋል፡፡ ከሰጧቸው መልሶች መካከልም፡- “ሃላፊዎች ልፋታቸውን ባለመረዳትና ጥቅማቸውን ባለመገንዘብ አይንከባከቧቸውም፤ በትምህርት ደረጃ በብቃትና በችሎታ የተመረኮዘ ምደባ አለመለመድ፤ የአገልግሎት ጊዜንና አቅምን ያገናዘበ ተገቢ ክፍያና ጥቅማጥቅም አለመኖር፤ በድህነት የሚኖሩና ሲታመሙ ገንዘብ የሚዋጣላቸው መሆናቸው፣” የሚሉ ይገኙባቸዋል፡፡
ጋዜጠኛ መሰለ “አንጋፋ ኤዲተሮች የት ነው ያሉት?” ሲሉም በፅሁፋቸው ወሳኝ ጥያቄ አንስተዋል፡፡ ጋዜጠኛው እንደሚሉት፤ አንጋፋ ኤዲተሮች በተለያዩ ተቋማት ውስጥ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊዎች ሆነው እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ አንዳንዶቹም በተለያየ ሙያ ላይ ተሰማርተዋል። ከፊሎቹ ደሞ በተቋማቸው ውስጥ ከይዘት ሥራ ውጭ ተመድበው እየሰሩ ናቸው፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ጡረታ ወጥተዋል ብለዋል።
 ፅሁፍ አቅራቢው  “አንጋፋ ኤዲተሮች ባለመኖራቸው ምን አጣን?” የሚል ርዕሰ ጉዳይም አንስተዋል -  ለዚህም በሰጡት ምላሽ፤ “ብቃት ያለው ኤዲተር እጥረት ተስተውሏል፤ የቅብብሎሽ ድልድዩ ተሰብሯል፤ ያልበሰለ ጋዜጠኝነት እየተስፋፋ ነው፤” ብለዋል፡፡
ጋዜጠኛ መሰለ ገ/ህይወት  ፅሁፋቸውን የቋጩት የመፍትሄ ሃሳቦች በማቅረብ ነው። “የጋዜጠኞች የስራ መደብ ዕድገት ቅደም ተከተሉን ይዞ መጓዝ አለበት፤ ሚዲያውን መምራት ያለባቸው ጋዜጠኞች ናቸው፤ ጋዜጠኞች የአመራር ሥልጠናም መውሰድ አለባቸው፤” ብለዋል- ባቀረቡት የመፍትሄ ሃሳብ፡፡
ሌላው በውይይቱ ላይ በእንግድነት የታደሙትና የኢትዮጵያ ሚዲያ ካውንስል አመራር አባል የሆኑት ጋዜጠኛ ታምራት ሃይሉ በሰጡት አስተያየት፤ “ሚዲያን ለማሻሻል መሰረቱ ያለው ኤዲተሮች ዘንድ  ነው፤ በእያንዳንዱ ይዘት ላይ የመወሰን ሥልጣን ያላቸው ኤዲተሮች ናቸው” ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል፣ የሚዲያ ተቋምን መምራት ያለባቸው ጋዜጠኞች ናቸው በሚለው ጉዳይ ላይ ግን በጋዜጠኛ መሰለ ሃሳብ እንደማይስማሙ ከራሳቸው ተሞክሮና መሬት ላይ ከሚታየው ተጨባጭ እውነታ በመነሳት አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡
በዕለቱ የኢትዮጵያ አርታኢያን ማህበር ሳምንታዊ ውይይት ላይ ጎልቶ የወጣው ስሜት፣ የኢትዮጵያ ኤዲተሮች ክፍያ ጅቡቲን ከመሳሰሉ ጎረቤት አገራት ጋር እንኳን ሲነፃፀር እጅግ ዝቅተኛ መሆኑና በአጠቃላይ “ጋዜጠኝነት እዚህ አገር ድህነት ነው” የሚለው ሃሳብ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ያለምንም ተጨማሪ ማስረጃና ማረጋገጫ በኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞችና ኤዲተሮች ህይወት ላይ በተጨባጭ የሚታይ እውነታ ነው።    



Read 1486 times