Saturday, 23 September 2023 21:12

በኢትዮጵያ የጦር ወንጀልና በሰብአዊነት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ተባብሰዋል ተባለ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወዲህ በርካታ ግፎች
በንፁሀን ላይ ተፈፅመዋል ተብሏል

በኢትዮጵያ የጦር ወንጀሎችና በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ተባብሰው መቀጠላቸው ተገለፀ፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሀይል የተሞሉ ግጭቶች መበራከታቸውንና በተለይም በአማራና በትግራይ ክልሎች በንፁሃን ላይ የሚፈፀሙ ከፍተኛ በደሎች መኖራቸውም ተመልክቷል፡፡
አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ኤክስፐርቶች በኢትዮጵያ (ICHREE) ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ባቀረበው ሪፖርት ላይ እንደተገለፀው በትግራይና አማራ ክልሎች የተደራጁ የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎችንና ሌሎች ዘግናኝ ግፎች ተፈፅመዋል፡፡ በኦሮሚያ የመንግስት የፀጥታ ሃይሎች በክልሉ በንፁሃን ላይ የእስራትና የማሰቃየት ወንጀሎች መፈፀማቸውን ያመለከተው ባለ 21 ገፁ ሪፖርት፤ በአማራ ክልል በተለይም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀ ወዲህ በርካታ ግፎች በንፁሃን ላይ ተፈፅሟል ብሏል፡፡ አያይዞም ቢያንስ አንድ የድሮን ጥቃት በፌደራል መንግስቱ መፈፀሙን አመልክቷል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት የጥቃቱ አድራሾች በአግባቡ እንዲመረመሩ ወይንም ተጠያቂ እንዲሆኑ ከማድረግ ይልቅ አለም አቀፍ ምርመራ እንዳይካሄድ ሆነ ብሎ እንቅፋት እየፈጠረ ነው ብሏል፡፡
በቅርቡ የስራ ጊዜው የሚጠናቀቀው የመንግስታቱ ድርጅት በኢትዮጵያ የሚያካሂደውን የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዲመረምር ያቋቋመው ይኸው ቡድን፣ ተልእኮውን ለተጨማሪ አንድ አመት እንዲያራዝም ተጠይቋል፡፡
ስድስት የአሜሪካ ኮንግረስ አባላት ለአሜሪካ የውጪ ጉዳይ መ/ቤትና በመንግስታቱ ድርጅት የአሜሪካ ተወካይ በፃፉት ደብዳቤ፤ የአጣሪ ኮሚሽኑ የምርመራ ጊዜ እንዲራዘም ጠይቀዋል። የመርማሪ ቡድኑ በመላ ሀገሪቱ የተፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በመመርመር ፍትህና ተጠያቂነትን በማስፈን ተጎጂዎች እንዲካሱ ማድረግ ያስፈልጋል ያሉት የኮንግረስ አባላቱ፤ ለዚህም ገለልተኛና ብቸኛ የሆነው የምርመራ ቡድኑ የስራ ጊዜ በአንድ አመት እንዲራዘም ማድረጉ ወሳኝ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡
ያለ አሜሪካና አጋሮቿ ጥረት የመርማሪ ቡድኑ የስራ ጊዜን የማራዘም እድል የለም ያሉት የኮንግረስ አባላቱ፤ የባይደን አስተዳደር በኢትዮጵያ የሚከተለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ፍትህንና ተጠያቂነትን ማዕከል ያደረገ ሊሆን እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡




Read 2064 times