Saturday, 23 September 2023 21:16

“ሁለት ባላ ትከል፤ አንዱ ቢሰበር በአንዱ ተንጠልጠል!”

Written by 
Rate this item
(4 votes)

አንድ የአርሜኒያ አፈ-ታሪክ እንዲህ ይላል፡፡
ከእለታት አንድ ቀን አንድ የአርሜኒያ ንጉስ፣ አፍ-ጠባቂዎቹን በመላ ሀገሪቱ ልኮ “ከድፍን አርሜኒያ በመዋሸት አንደኛ ለሆነ ሰው፣ ንጉሱ ከወርቅ የተሰራ ትልቅ ፍሬ ሊሸልሙ ይፈልጋሉ!” እያሉ እንዲነግሩና እችላለሁ የሚል ማንኛውም ሰው እንዲመጣ እንዲደረግ ትእዛዝ ይሰጣሉ። የሀገሩ ውሸታም ሁሉ ወደ ቤተ-መንግስት መጉረፍ ይጀምራል፡፡ ግቢውን መግቢያ መውጫ አሳጣው ሰዉ፡፡ እንደእየ ማእረጉ ከየኑሮ እርከኑ ያለ ሰው መጣ፡፡ መሳፍንትና ልኡላን፣ ታላቅ ነጋዴዎች፣ ገበሬዎች፣ ቀሳውስት፣ ባለፀጎችና ደሆች፣ ወፍራም ቀጭን፣ አጭር እረጅም፣ ቆንጆና አስቀያሚ፡፡ በአገሩ የቀረ የሰው አይነት ያለ አይመስልም፡፡
አርሜኒያ የውሸታም እጥረት ኖሮባት አያውቅም፡፡ ሁሉ እየመጣ ለንጉሱ ውሸቱን አወራ፡፡ ወሸከተ፡፡ ንጉሱ ግን ከዚህ ቀደም የውሸት አይነት በገፍ ሰምተው ስለነበር፣ አሁን እየሰሙአቸው ያሉት ውሸቶች እንደ ድሮ ውሸት አልጥምም አላቸው፡፡ ምርጥ የሚሉት ውሸት አጡ፡፡ ማዳመጡም ደከማቸው፡፡ በጣም ከመሰልቸታቸው የተነሳ ውድድሩን ያለአሸናፊ ሊዘጉት ፈለጉ-በጨረታው አልገደድም ብለው፡፡
ሆኖም በመጨረሻ አንድ ጭርንቁሳም ደሃ መጣ፡፡
“እህስ ምን ልርዳህ አንተ ዜጋ?” ሲሉ ጠየቁ ንጉሱ፡፡
“ንጉስ ሆይ” አለ ዜጋው ትንሽ እንደመደናገጥ ብሎ “እንደሚያስታውሱት ከዚህ ቀደም፤ አንድ እንስራ ወርቅ ሊሰጡኝ ቃል ገብተውልኝ ነበር” አላቸው፡፡
“ማ? እኔ? ለአንተ?”
“አዎን ንጉስ ሆይ፤ ለአያሌ ሰው ብዙ ቃል ስለሚገቡ እረስተውት ይሆናል እንጂ፤ በእርግጥ እሰጥሃለሁ ብለውኝ ነበር!”
“ይሄ ፍፁም ውሸት ነው! አንተ  ቀጣፊ ሰው ነህ! ምንም ገንዘብ ላንተ ልሰጥ ቃል አልገባሁም”
“እንግዲያው ይሄ ፍፁም ውሸት ነው ካሉ፤ ከወርቅ የተሰራ ትልቅ ፍሬ እሸልማለሁ ብለው አውጀው ነውና የመጣሁት፤ ሽልማቱ ለኔ ይገባኛል፡፡ የወርቁን ፍሬ ይስጡኝ” አላቸው፡፡
ንጉሱ ይሄ ዜጋ በዘዴ ሊያታልላቸው መሆኑን አሰቡና፤
“የለም የለም፤ አንተ ውሸታም አይደለህም” አሉት፡፡
“እንግዲያው ቃል የገቡልኝን አንድ እንስራ ሙሉ ወርቅ ይስጡኝ” አለ፤ ፍርጥም ብሎ፡፡
ንጉሱ አጣብቂኝ ውስጥ ገቡ፡፡ ከወርቅ የተሰራውን ትልቅ ፍሬ የግዳቸውን ለደሃው ሸለሙት፡፡
***
እውነተኛ ውሸት የሚዋጣለት ሰው እንኳ እንዳይጠፋ መመኘት ጥሩ ነው፡፡ ያ ሁሉ መኳንንት መሳፍንት፣ ነጋዴ ወዘተ ወሽክቶ ወሽክቶ የሚታመንና ማራኪ ውሸት መጥፋቱ ትልቅ ድክመት ነው፡፡ በአንፃሩ በገዛ አዋጁ፣ በገዛ መመሪያው፣ በገዛ ፕሮግራሙ፣ በገዛ እቅዱ አጣብቂኝ ውስጥ የሚገባ መሪ፣ አለቃ፣ ሃላፊ፣ የፖለቲካ ሰው፣ የፓርቲና የማህበር የበላይ ሃላፊ ሁሉ፤ ውሎ አድሮ የሚከፍለው እዳ እንዳለ ማስተዋል ደግ  ነው፡፡ የምንገባው ቃል እራሳችንን መልሶ የሚጠልፈን እናም የሚጥለን ሊሆን እንደሚችል አለመዘንጋት ነው፡፡
በታሪክ “አደገኛው ኢቫን” (Ivan the Terrible) በመባል ይታወቅ የነበረው የሩሲያ ንጉስ፤ አንዴ አስከፊ አጣብቂኝ ውስጥ ወድቆ ነበር ይባላል፡፡ ይሄውም፤ በአንድ በኩል፤ ሀገሪቱ  ለውጥና መሻሻል ትፈልጋለች፡፡ በሌላ በኩል፣ ወደፊት ገፍቶ ወደተሻለ አገር እንዳይለውጣት አቅም አጣ፡፡ በዙሪያው ያሉት ሁነኛ የሚላቸው ሰዎች ደግሞ ገበሬውን  ሡሪ-ባንገት-አውልቅ የሚሉት ልኡላን ናቸው፡፡ በዚህ መካከል ንጉሱ ታመመና ሊሞት ተቃረበ፡፡ ለልኡላኑ፤ “ልጄ አዲሱ ዛር ነጋሲ(ንጉስ) እንዲሆን አድርጉ” አለ፡፡  ልኡላኑ ተቃወሙት፡፡ ያኔ ስልጣኑና አቅሙን እንደወሰዱበት ገባው፡፡ ወዳጅ ጠላቱን አወቀ፡፡
በዚያን ጊዜ ሩሲያ ዙሪያዋን ጠብ ተጭሮባት ነበር፡፡ እንዳጋጣሚ ግን እሱ ከሞት ዳነ፡፡ አንድ ጠዋት ማንንም ሳያሳውቅ የዛሩን መንግስት ሃብት ንብረት ይዞ ከቤተ-መንግስት ወጣ፡፡ አገሪቱ በድንገት ስጋት ላይ ወደቀች፡፡ ጥቂት ሰንብቶ ንጉሱ ደብዳቤ ላከ፤ “የልኡላኑንና የመሳፍንቱን ተንኮል ስላልቻልኩት ስልጣኔን ለቅቄያለሁ” አለ፡፡ ዜጋው፣ ነጋዴው፣ ሃብታሙ ግን ከጭንቀት ብዛት ዝም ብሎ ሊቀመጥ አልቻለም፡፡ ስለዚህ ያለበት ድረስ ሄዶ ተማጠነው፡፡ ንጉሱም ከብዙ ልመና በኋላ በመጨረሻ ሁለት ምርጫ ሰጣቸው፡፡ “ወይ ሙሉና ፍፁም ስልጣን ስጡኝ፡፡ ማንም ጣልቃ አይግባብኝ አልያ አዲስ መሪ ፈልጉ” አለ፡፡ አጣብቂኝ ውስጥ ከተታቸው፡፡
“አንተው ሁንልን!” አሉት፡፡ የበለጠ ስልጣን፣ የበለጠ ጉልበት አገኘና ቁጭ አለ፡፡ አጣብቂኝ ውስጥ የገባ፣ ሌላውን አጣብቂኝ ውስጥ በመክተት እራሱን ከአጣብቂኝ ያወጣል፡፡
ሀገር የፖለቲካና የኢኮኖሚ አጣብቂኝ ውስጥ ስትገባ፣ የፖለቲካ መሪዎችና ሃላፊዎች አጣብቂኝ ውስጥ ሲገቡ፣ የአስተዳደርና የአመራር አካላት አጣብቂኝ ውስጥ ሲገቡ፣ ዜጎች የኑሮ አጣብቂኝ ውስጥ ሲገቡ፤ አማራጭ መውጫ ያስፈልጋቸዋል፡፡ የፖለቲካ አረንቋ ውስጥ ከገባን አማራጭ መውጫ ያሻናል፡፡ የኢኮኖሚ አዘቅት ውስጥ ከገባን አማራጭ ያሻናል፡፡ የጦርነት አዙሪት ውስጥ ከገባን (እንዲህ እንዳሁኑ) አማራጭ ያስፈልገናል፡፡ ሆኖም መብራት አጣን ለሚል ዜጋ፤ “ለምን ጄኔሬተር አይገጠምም” የሚል አማራጭ፤ ጥሩ አማራጭ አለመሆኑን መገንዘብ ያባት ነው፡፡ “መብራት ሳይኖር በፊት እንደኖረው ይኑር”፤ የሚል አማራጭም አማራጭ አይደለም፡፡ አማራጩ አማራጭ ብቻ ሳይሆን የመፍትሄ አማራጭ መሆን ይኖርበታል፡፡ ማህበረሰቡ “ዳቦ!” እያለ ይጮሃል ስትባል “ለምን ኬክ አይበሉም!” እንዳለችው እንደ ፈረንሳይዋ ንግስት እንደ ሜሪ አንቷሌት ያለ ታሪክ እንዳይደገም መጠንቀቅ ግድ ነው፡፡
ከአጣብቂኙ የሚወጡበት ሁነኛ መላም ያስፈልጋቸዋል፡፡ አማራጮችን ማየት ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ አማራጭ ሰዎች ያስፈልጋሉ፡፡ ብልህ አሳቢ ሽማግሌዎች ያስፈልጋሉ፡፡ ሆደ-ሰፊ ምሁራን ያስፈልጋሉ፡፡ ይህንንም እንደ አማራጭ መቀበል ያስፈልጋል፡፡ አገርን የሚያድናት አማራጭ የመፍትሄ ሃሳብና አማራጩን ሃሳብ የሚያስፈፅም አማራጭ ሰው ነው፡፡ “ሁለት ባላ ትከል፣ አንዱ ቢሰበር በአንዱ ተንጠልጠል” የሚባለው ይሄኔ ነው!

Read 1571 times