Friday, 06 October 2023 00:00

“የመገናኛ ብዙኃን ዋልታ-ረገጥነት የፖለቲካችን ነጸብራቅ ነው”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

* መገናኛ ብዙኃን ከችግር ፈጣሪነት ወጥተው ፖለቲካውን መምራት አለባቸው ተብሏል  

የኢትዮጵያ አርታኢያን ማህበር፤ "Media Polarization; How Editorial Policy Counteracts Polarization in the News Media" በሚል ርዕስ፣ በመገናኛ ብዙኃን ዋልታ-ረገጥነት ዙሪያ ከትላንት በስቲያ ሐሙስ  ሳምንታዊ የቁርስ ላይ ውይይቱን አካሄደ።

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የዲጂታል ሚዲያ ዋና አዘጋጅ አቶ ነብዩ ወንደሰን፣ በርዕሰ-ጉዳዩ ላይ ለውይይት መነሻ ሃሳብ የሚሆን ፅሁፍ አቅርበዋል።

አቶ ነብዩ በፅሁፋቸው፣ ቀደም ሲል የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን በሁለት ይከፈል እንደነበር (የመንግስትና የግል) አውስተው፤ አሁን ግን በአራት ነው የሚከፈለው ብለዋል። ሲዘረዝሩም፤ የመንግሥት፣ የግል፣ የኢትዮጵያን አንድነት የሚያቀነቅኑና ብሔርን መሰረት ያደረጉ መገናኛ ብዙኃን ናቸው ብለዋል፡፡  

የመገናኛ ብዙኃን ዋልታ-ረገጥነት፣ የተበላሸው ፖለቲካችን ነጸብራቅ መሆኑንም አስረግጠው ተናግረዋል፡፡

በአገሪቱ ለዘመናት የተከማቸ የፖለቲካ ችግር እንዳለ፣ አለመተማመንና ጥርጣሬ መስፈኑን  እንዲሁም በፖለቲካዊ ክርክራችን ከምክንያታዊነት ይልቅ ስሜታዊነት እንደሚንፀባረቅ ያነሱት ፅሁፍ አቅራቢው፤ መገናኛ ብዙኃኑም  ከዚህ  ውጭ መሆን ስለማይችሉ ዋልታ-ረገጥ ሆነዋል ብለዋል።

ዋልታ-ረገጥነት በሁሉም መገናኛ ብዙኃን ላይ የሚስተዋል ክስተት ቢሆንም፣ እንደ አሸን በፈሉት ብሔርን መሰረት ያደረጉ መገናኛ ብዙኃን ላይ የበለጠ  ጎልቶ እንደሚስተዋል የጠቀሱት አቶ ነብዩ፤ ጋዜጠኞች ገለልተኛ ሆነው እውነቱን በሚዛናዊነት ከመዘገብ ይልቅ ለመጡበት ብሔርና ሃይማኖት የሚወግኑ  እየሆኑ መጥተዋል ሲሉ ተችተዋል፡፡

የመገናኛ ብዙኃን ዋልታ-ረገጥነት በቅርቡ በቤተክህነት ውስጥ በተከሰተው ችግር በግልጽ ተንፀባርቋል ያሉት ፅሁፍ አቅራቢው፤ ከፊሎቹ ቤተክህነትን ወግነው ሲዘግቡ፣ የተቀሩት ደግሞ ተለይተው የወጡትን ቡድኖች በመወገን  መዘገባቸውን በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡

መገናኛ ብዙኃን ገለልተኛ ሆነው እውነቱን ከመዘገብ ይልቅ ዋልታ-ረገጥ መሆናቸው ለጋዜጠኝነት ሙያ አደጋ ከመሆኑም ባሻገር  አገርን  ለግጭትና ብጥብጥ እየዳረገ እንደሚገኝም አቶ ነብዩ ተናግረዋል፡፡
 
 መገናኛ ብዙኃኑ የሚስተካከሉት የፖለቲካው ዋልታ-ረገጥነት ሲስተካከል ነው የሚል አቋም ያንጸባረቁት  አቶ ነብዩ፤ መገናኛ ብዙኃኑ የኤዲቶሪያል ነፃነታቸውን ጠብቀው እንዲሰሩ ጥረት ማድረግን፣ እንዲሁም ሃላፊነት የተመላበት ጋዜጠኝነትን ማጎልበትን እንደ መፍትሄ ሃሳብ ጠቁመዋል፡፡

የማህበሩ አባላትና ተጋባዥ እንግዶች በርዕሰ ጉዳዩ ላይ የተለያዩ  ሃሳቦችን ያንሸራሸሩ ሲሆን፤ የሚበዙት አስተያየት ሰጪዎች የሚዲያውን መልክአ-ምድር በመቀየር ረገድ አርታኢያን የጎላ ሚናና አስተዋፅኦ እንደሚኖራቸው አስምረውበታል፡፡

መገናኛ ብዙኃኑ የተበላሸው የፖለቲካችን ሁኔታ ነፀብራቅ መሆኑን የተቀበሉ አንድ አስተያየት ሰጪ፤ እንዲያም ሆኖ መገናኛ ብዙኃን የፖለቲካውን መልክአ-ምድር መቀየር የሚያስችል አጀንዳ መቅረፅ አለባቸው ብለዋል፤ ከችግር ፈጣሪነት ወጥተው  ፖለቲካውን መምራት እንዳለባቸውም  በማከል፡፡

አብዛኛው ሰው ለመገናኛ ብዙኃን ያለው ግምትና አመለካከት የተዛባ ነው ያሉት ሌላው የማህበሩ አባል፤ የመገናኛ ብዙኃንን ዋልታ-ረገጥነት ማስተካከል የምንችለው በመጀመሪያ በህብረተሰቡ ዘንድ ስለ መገናኛ ብዙኃን ትክክለኛ ግንዛቤ መፍጠር ስንችል  ነው ብለዋል፡፡

ፅሁፍ አቅራቢው፣ የመገናኛ ብዙኃን ዋልታ-ረገጥነት፣ የፖለቲካው ዋልታ-ረገጥነት ነጸብራቅ ነው በሚል ያቀረቡትን ሃሳብ ያልተቀበሉ አንድ አስተያየት ሰጪ፤ የመገናኛ ብዙኃን ዋልታ-ረገጥነት ዛሬ የተፈጠረ አይደለም ብለዋል፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፣ የመገናኛ ብዙኃን ዋልታ-ረገጥነት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የፖለቲካውን ዋልታ-ረገጥነት ተከትሎ የተፈጠረ ሳይሆን፤ ከደርግም ጀምሮ በኢህአዴግም ጭምር የተስተዋለ ክስተት ነው፡፡

ለመገናኛ ብዙኃን ዋልታ ረገጥ መሆን ተጠያቂ የሚያደርጉትም በተለያዩ ጊዜያት ሥልጣን ላይ የወጡ መንግሥታትን ነው፤ መንግሥታት የሥልጣን ዕድሜያቸውን ለማራዘም ሲሉ መገናኛ ብዙኃኑን የአንድ ወገን ፕሮፓጋንዳ ብቻ እንዲያስተጋቡ  ያደርጓቸዋል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

የመገናኛ ብዙኃንን ዋልታ-ረገጥነት ለማስተካከልም መፍትሄው ያለው በመንግሥት እጅ መሆኑን የጠቆሙት አስተያየት ሰጪው፤ ጉዳዩ የመንግሥትን የፖለቲካ ቁርጠኝነት የሚጠይቅ ነው ብለዋል፡፡  

መንግሥትስ ምን እያለ  ይሆን??

Read 1624 times