Friday, 13 October 2023 18:54

የአፍሪካ መንግሥታት በእስራኤልና ሃማስ ጦርነት የተለያዩ አቋሞችን አንፀባርቀዋል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  ግብፅና ደቡብ አፍሪካ የአሸማጋይነት  ሚናን መርጠዋል፤ኢትዮጵያስ?

ባለፈው ቅዳሜ መስከረም 26 ቀን 2016 ዓ.ም በአሜሪካና አጋሮቿ የሽብርተኛ ድርጅት ተብሎ የተበየነው እስላማዊው የሃማስ ቡድን፣ በእስራኤል ላይ የፈፀመውን ድንገተኛ ጥቃት ተከትሎ፣ በተቀሰቀሰው የእስራኤል-ሃማስ ጦርነት ዙሪያ የአፍሪካ መንግስታት የተለያዩ አቋሞችን አንፀባርቀዋል - አንዱን ደግፈው ሌላውን  በማውገዝ፡፡

በእርግጥ የትኛውንም ሳይወግኑና ሳይቃወሙ ገለልተኛነታቸውን ለማንፀባረቅ የሞከሩም አልጠፋም-ናይጀሪያ ትጠቀሳለች፡፡ እስካሁን በእስራኤል-ሃማስ ጦርነት ገዳይ ትንፍሽ ያላሉ የአፍሪካ መንግስታትም አሉ፡፡

በሌላ በኩል፤ አቋም ሳይዙ የአሸማጋይነት ወይም የአስታራቂነት ሚናን የመረጡም አገራት ታይተዋል - ግብፅና ደቡብ አፍሪካ፡፡

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን በበኩሉ፤ በሁለቱ ወገኖች መካከል ግጭት እንዲቆምና  ወደ ድርድር ጠረጴዛ እንዲመጡ  ጥሪ አስተላልፏል፡፡

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም፣ በእስራኤል- ፍልስጤም ጦርነት ጉዳይ የኢትዮጵያ አቋም ምን እንደሆነ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ፤ "ኢትዮጵያ በእስራኤል- ፍልስጤም ጉዳይ ዙሪያ ከዚህ በፊት ካላት አቋም የተለየ አቋም አልያዘችም፣ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት አቋም የሆነው የሁለት ሉዓላዊ ሀገር መሆን ችግሩን ይፈተዋል የሚለው አቋም ትናንትም ሆነ ዛሬም ትክክል እንደሆነ ታምናለች" ብለዋል።

የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ፌሊክስ ኬሲሽኬዲ፣ ከእስራኤል ጋር በአጋርነት እንደሚቆሙ ገልጸው፤አገራት ሽብርተኝነትን በሁሉም መልኩ ለመዋጋት አንድነትን መፍጠር እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ በተመሳሳይ፣ ከእስራኤል ጎን በአጋርነት እንደሚቆሙ በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

“ዓለማቀፉ ማህበረሰብ፤ የዚህን አስከፊ የሽብር ወንጀል ፈፃሚዎች፣ አደራጆች፣ የገንዘብ ድጋፍ አድራጊዎችና ደጋፊዎች  ተጠያቂ በማድረግ፣ በፍጥነት ለፍርድ ለማቅረብ መንቀሳቀስ አለበት፡፡” ብለዋል - ፕሬዚዳንት ሩቶ፡፡

 “ኬንያ ከቀረው ዓለም ጋር እስራኤልን በመደገፍ በአጋርነት ትቆማለች”፤ ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ “ሽብርተኝነትን እንዲሁም በአገሪቱ ውስጥ በንጹሃን ሲቪሎች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ሙሉ ለሙሉ  ታወግዛለች” ብለዋል፡፡

የኡጋንዳው ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ በበኩላቸው፤ “በእስራኤል - ፍልስጤም ዳግም አዲስ ግጭት መከሰቱ አሳዛኝ ነው፡፡ ለምንድን ነው ሁለቱ ወገኖች የሁለት ሉአላዊ አገራት መፍትሄን የማይተገብሩት? በተለይ ሊወገዝ የሚገባው፤ ተዋጊዎች ያልታጠቁ ሲቪሎችና ንጹሃንን ኢላማ ማድረጋቸው ነው፡፡” ብለዋል፡፡

የግጭት መባባስና የሰው ህይወት መጥፋት እንዳሳዘናቸው የገለፁት የጊኒ ቢሳው ፕሬዚዳንት ኡማሮ ሲሶኮ ኢምባሎ፤ በጋዛ ሰርጥ የተኩስ አቁም እንዲታወጅ  ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ኢምባሎ አክለውም፤ “ጊኒ ቢሳው ጦርነትን በቅጡ የምትረዳ ነገር ግን የሰላም አገር እንደመሆኗ፣ በጋዛ ሰርጥ ባለው ሁኔታ ከልብ ታዝናለች፡፡” ብለዋል፡፡

“በሚያሳዝን ሁኔታ በሃማስ የአየር ድብደባ ተፈፅሟል፤ እንዲያም ሆኖ ሁለቱም ወገኖች ግጭት እንዲያቆሙ እንጠይቃለን፤ ምክንያቱም የብዙዎች ህይወት እየጠፋ ነው” ሲሉ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል- ኢምባሎ፡፡

የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሳይሪል ራማፎሳ፣ ከትላንት በስቲያ ሃሙስ፣ ከደቡብ አፍሪካ የግጭት አፈታት ልምድ በመውሰድ፣ የእስራኤል - ፍልስጤም ግጭን ለመሸምገል ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ራማፎሳ በተጨማሪም፣ እርዳታ በአስቸኳይ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች መድረስ ይችል ዘንድ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በፍጥነት “የሰብአዊ ኮሪደር” በመካከለኛው ምስራቅ እንዲከፈት ጠይቀዋል፡፡

የተለመደውን የአሸማጋይነት ሚናዋን የቀጠለችው ግብፅ፤ ሁለቱም ወገኖች ከግጭት “ራሳቸውን እንዲያቅቡ” ጥሪ ያቀረበች ሲሆን፤ “የግጭት መባባስ ስለሚያስከትለው ከፍተኛ አደጋ” አስጠንቅቃለች፡፡ የግብፅ ፕሬዚዳት አብደል ፋታህ አልሲሲና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው፣ ከአውሮፓ ህብረት የዲፕሎማሲ ሃላፊ ጆሴፕ ቦሬል እንዲሁም ከኢሜሬትስ፣ ዮርዳኖስ፣ ቱርክ፣ ፈረንሳይና ጀርመን ባለስልጣናት ጋር በጉዳዩ ዙሪያ መወያየታቸውን ተናግረዋል፡፡


የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሞሳፋኪ ማሃማት በበኩላቸው፤ ሁለቱም ወገኖች በአፋጣኝ ወታደራዊ ግጭትን አቁመው ወደ ድርድ እንዲመጡ ጥሪ አቅርበዋል - በመግለጫቸው፡፡

“የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ሁለቱም ወገኖች በአስቸኳይ ወታደራዊ ግጭትን አቁመው፣ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ፣ ወደ ድርድር ጠረጴዛ በመመለስ፣ የሁለት ጎን ለጎን የሚኖሩ ሉአላዊ አገራት መርህን እንዲተገብሩና የፍልስጤም ህዝብንና የእስራኤል ህዝብን ፍላጎቶች እንዲያስጠብቁ ጥሪ አቅርበዋል፡፡” ይላል - መግለጫው፡፡

“ሊቀመንበሩ በተጨማሪም፣ ዓለማቀፍ ማህበረሰቡ በተለይም ተፅዕኖ ፈጣሪ ሃያላን አገራት፤ ሰላም የማስፈንና የሁለቱን ህዝቦች መብቶች የማረጋገጥ ሃላፊነታቸውን ይወጡ ዘንድ ጠይቀዋል፡፡” በመግለጫው፡፡

 በእስራኤል-ሃማስ ጦርነት ላይ ገለልተኛ አቋም ያንፀባረቀችው ናይጀሪያ፤ “የግጭትና የአፀፋ ምላሽ አዙሪት”፤ ለሁለቱም ወገን ሰላማዊ ህዝቦች፣ “ማብቂያ የሌለው የስቃይ አዙሪት” ይፈጥራል ስትል አስጠንቅቃለች፡፡

በሌላ በኩል፣ የአልጀሪያ፣ ቱኒዝያ፣ ጅቡቲና ሞሮኮ መንግስታት ለፍልስጤም ሙሉ ድጋፋቸውንና አጋርነታቸውን ገልፀዋል -  እስራልን በመቃወምና በማውገዝ፡፡

በኡጋንዳ ካምፓላ የሰብአዊ መብት አንቂ የሆነው ኢብራሂም ሴንዳውላ፤ በእስራኤል - ሃማስ ጦርነት ለአንዱ ወይም ለሌላው መወገን ግጭትን ያባብሰዋል ሲል ለደቸቨሌ ተናግሯል፡፡

“የአውሮፓ መሪዎች የሰላም ጥሪ ከማቅረብ ይልቅ የእስራኤልን ጥቃት መደገፋቸው አስገራሚ ነው፤ በተመሳሳይ ሃማስ እስራኤል ላይ የፈፀመውን ጥቃት አንዳንድ ሰዎች ሲደግፉና ሲያደንቁ ማየት ያስገርማል፡፡ ይሄ አሳዛኝ ነው” ብሏል - ሴንዳውላ፡፡

Read 1558 times