Saturday, 14 October 2023 00:00

በ35ኛው የዓለም ኮከብ አትሌት ሽልማት

Written by  ግሩም ሰይፉ
Rate this item
(0 votes)

ጉዳፍና ትግስት ታጭተዋል፤ 7ኛውን ሽልማት ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት?
 ኃይሌ ገብረስላሴ (በ1998 እኤአ) ፤ ቀነኒሳ በቀለ (በ2004ና በ2005 እኤአ)
መሰረት ደፋር (በ2007 እኤአ) ፤ ገንዘቤ ዲባባ (በ2015 እኤአ) ፤ አልማዝ አያና (በ2016 እኤአ)


የዓለም አትሌቲክስ ማህበር በ2023  የውድድር ዘመን ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ  አትሌቶችን በሚያወዳድርበት የዓለም ኮከብ አትሌቶች World Athletics Award ምርጫ የድጋፍ ድምፅ ማሠባሠብ ጀምሯል።   በዓመቱ ኮከብ አትሌት ምርጫው ላይ በሁለቱም ፆታዎች ለውድድር የቀረቡ እጩ አትሌቶችም ሰሞኑን ታውቀዋል። በሴቶች ምድብ በእጩነት ከቀረቡት 11  ምርጥ    አትሌቶች ሁለቱ ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ በወንዶች ምድብ ግን ኢትዮጵያውያን በእጩነት ሳይካተቱ ቀርተዋል።
ከ2023 በፊት በተካሄዱት ያለፉት 34 የዓለም  ኮከብ አትሌት የሽልማት ስነስርዓቶች የኢትዮጵያ አትሌቶች በሁለቱም ፆታዎች 6 ጊዜ ለመሸለም በቅተዋል።በወንዶች ምድብ 3 ጊዜ እንዲሁም በሴቶች ምድብ 3 ጊዜ በማሸነፍ ነው፡፡ በወንዶች ምድብ ያሸነፉት በ1998 ኃይሌ ገብረስላሴ እንዲሁም በ2004ና በ2005 እኤአ ቀነኒሳ በቀለ ናቸው። በሴቶች ምድብ ደግሞ በ2007  መሰረት ደፋር ፤ በ2015 እኤአ ገንዘቤ ዲባባና በ2016 እኤአ አልማዝ አያና ተሸልመዋል። በዓለም አትሌቲክስ የኮከቦች ምርጫ በልዮ ዘርፍ ያሸነፉም አሉ። በ2006 እኤአ አሰልጣኝ ዶክተር ወልደመስቀል ኮስትሬ ብቸኛውን የአይኤኤኤፍ የህይወት ዘመን ስኬት ሽልማት አግኝተዋል። በ2005ና በ2008 ጥሩነሽ ዲባባ እንዲሁም በ2006 እኤአ  መሰረት ደፋር በሴቶች ምድብ እንዲሁም በ2019 ሰለሞን ባረጋ በወንዶች ምድብ የዓመቱ ምርጥ ብቃት ሽልማትን አሸንፈዋል።
በዓለም ኮከብ አትሌቶች ምርጫ የ2023 እጩዎች
በዓለም ኮከብ አትሌት ምርጫው ላይ በሴቶች ምድብ ዕጩ ለመሆን የበቁት ሁለቱ የኢትዮጵያ አትሌቶች ጉዳፍ ፀጋይና ትግስት አሰፋ በውድድር ዘመኑ ሁለት አስደናቂ የዓለም ሪከርዶች በማስመዝገባቸው ሽልማቱን ለመውሰድ ከፍተኛ ግምት አግኝተዋል።  አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ በ19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ቡዳፔስት ላይ በ10,000 ሜትር ሻምፒዮንነት የወርቅ ሜዳሊያ ከተጎናፀፈች በኋላ በአሜሪካ ዩጂን በተጠናቀቀው የ2023 ዳይመንድ ሊግ ማሸነፏና በ5,000 ሜትር የዓለም ሪከርድ ማስመዝገቧ ይታወቃል። አትሌት ትግስት አሰፋ ደግሞ በጀርመኑ የበርሊን ማራቶንን በማሸነፏና የዓለም የማራቶን ሪከርድን ከ 2 ደቂቃዎች በላይ በማሻሻሏ ነው።   
በሴቶች ምድብ የቀረቡት ሌሎቹ እጩዎች በ1500 ሜ እና በ5000 ሜ የዓለም ሻምፒዮንና የዓለም ሪከርዶች ባለቤት ፌዝ ኪፕየገን ከኬንያ፤ በ200 ሜትር የዓለም ሻምፒዮንና ቀ100 እና 200 ሜ ዳይመንድ ሊግን ያሸነፈችው ሼሪካ ጃክሰን ከጃማይካ፤ በ400 ሜትር መሰናክል  የዓለም ሻምፒዮንና የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሪከርድ የያዘችው ራምኬ ቦል ከሆላንድ፤ በጦር ውርወራ የዓለም ሻምፒዮንና የዳይመንድ ሊግ አሸናፊ ሃሩካ ካቲጉቺ ከጃፓን፤ በከፍታ ዝላይ የዓለም ሻምፒዮንና የዳይመንድ ሊግ አሸናፊ ያሮስላቫ ማቹቲካህ ከዮክሬን፤ በ20ኪ ሜ እና በ35 ኪ ሜ የርምጃ ውድድሮች የዓለም ሻምፒዮን የሆነችውና በ35 ኪሜ ርምጃ ውድድር የዓለም ክብረወሰን ያላት ማርያ ፔሬስ ከስፔን፤ በ100 ሜ የዓለም ሻምፒዮን ለመሆን የበቃችው ሻካሪ ሪቻርድሰን፤ በስሉስ ዝላይ የዓለም ሻምፒዮንና የዳይመንድ ሊግ አሸናፊ ዮሊማር ሮጃስ ከቬንዝዋላና በ4ሺ ሜትር መሠናክል በዓለም ሻምፒዮና በዳይመንድ ሊግ ያሸነፈችው ዊንፍሬድ ያቪ ከብራዚል ናቸው። በወንዶች ምድብ ከቀረቡት እጩዎች የማራቶንን ርቀት በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከ2 ሰዓት 2 ደቂቃ እና ከ2 ሰዓት 1 ደቂቃ በታች በመግባት አስደናቂ የዓለም ማራቶን ሪከርድ ያስመዘገበው የኬንያው ኬቨን ኪፕቱሚ ከፍተኛ የአሸናፊነት ግምት ወስዷል። በ5000 ሜ  የዓለም ሻምፒዮን ለመሆን የበቃው የአውሮፓ ምርጥ እትሌት ጃኮብ ኢንግሪብስተን ከኖርዌይ፤ በ100 ሜትርና በ200 ሜትር የዓለም ሻምፒዮን ለመሆን የበቃው ኖህ ላየልስ ከአሜሪካ በ400 ሜትር መሠናክል የዓለም ሻምፒዮን ካርተን ዎርል ከኖርዌይ እንዲሁም በ3ሺ መሰናክል የዓለም ሻምፒዮን የሆነው ሱፍያን ኤልባካሊ ከሞሮኮ ይጠቀሳሉ።ጦር ወርዋሪው ኔራጅ ቾፕራ ከህንድ ፤ አሎሎ ወርዋሪው ራያን ከርሰር ከአሜሪካ፤ የምርኩዝ ዘላዩ ሞንዶ ዱፕላንቲስ ከስዊድን፤ የዴካትሎን ስፖርተኛው ፒርስ ሌፔጅ ከካናዳ፤ የርምጃ ተወዳዳሪው አልቫሮ ማርቲን ከስፔንና የርዝመት ዝላይ ስፖርተኛ ሚታልዲ ቴንቴጎሎ ሌሎቹ እጩዎች ናቸው።
የዓለም አትሌቲክስ ማህበር የምርጫ ሂደት
በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር የሚካሄደው   የዓለም ኮከብ አትሌቶች ምርጫ አጠቃላይ ሂደት ከሁለት ወራት በላይ የሚፈጅ ነው።  የሽልማት ስነስርዓቱ በየዓመቱ  በፈረንሳይ ሞናኮ ከተማ ውስጥ ሲካሄድ ቆይቷል።  ከመላው ዓለም ከአንድ ሺ በላይ የአትሌቲክስ ባለድርሻ አካላት በክብር እንግድነት ይታደሙታል።  ከሽልማቱ ስነስርዓት በፊት በሚከናወነው የዓለም ኮከብ አትሌቶች የምርጫ ሂደት የመጀመሪያው ተግባር እጩዎችን ማሳወቅ ነው፡፡ በሁለቱም ፆታዎች ለመጨረሻ ፉክክር በእጩነት የሚቀረቡ አትሌቶችን  በየውድድር ዘርፉ በመመልመል 11 የመጀመርያ እጩዎችን  በዓለም አትሌቲክስ ኦፊሴላዊ ድረገፅ ይገለፃሉ። በመጀመሪያው ምዕራፍ  ከዓለም አትሌቲክስ አፍቃሪዎች በዓለም አትሌቲክስ ኦፊሴላዊ የፌስቡክ ፤ የትዊተርና የኢንስታግራም ማህበራዊ ገፆች የድጋፍ ድምፅ መሰባሰብ ጀምሯል። ከዚያ በኋላ ድምፆችን የሚሰጡት  ደግሞ የዓለም አትሌቲክስ ማህበረሰብ የሚባሉት የአባል አገራት ፌደሬሽኖች፤ አሰልጣኞችና ሌሎች ባለሙያዎች  ናቸው፡፡  
በምርጫው ሁለተኛ ምዕራፍ በዓለም አትሌቲክስ የሚሰሩ የስፖርቱ ኤክስፐርቶች ከፍተኛ ድምፅ ያገኙትን የመጨረሻ ተፎካካሪዎች በመለየት ግምገማ ያደርጋሉ ። በሁለቱም ፆታዎች ለመጨረሻ ፉክክር የቀረቡትን ሶስት እጩዎች ያሳውቃሉ፡፡  በሁለቱም ፆታዎች የመጨረሻ እጩ አድርገው ከቀረቡት አትሌቶች መካከል ደግሞ የዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ተቋም ምክር ቤት አባላት  አሸናፊዎቹን ይመርጣሉ፡፡ በነገራችን ላይ በሁለቱም ፆታዎች የዓለም ኮከብ አትሌት ሆነው የሚመረጡ አትሌቶች ልዩ የዋንጫ ሽልማት እና 100ሺ ዶላር ቦነስ ይበረከትላቸዋል፡፡የዓለም ኮከብ አትሌቶች ምርጫ የተጀመረው በ1988 እኤአ ላይ ሲሆን በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፋውንዴሽን ምክር ቤት እና በዓለም አትሌቲክስ ማህበር  ትብብር የሚዘጋጅ ነው።  ባለፉት 34 የዓለም ኮከብ አትሌት የሽልማት ስነስርዓቶች በወንዶች ምድብ የ13 አገራት አትሌቶች ተሸላሚዎች ሲሆኑ  አሜሪካ 8 ጊዜ በማሸነፍ ግንባር ቀደም ስትሆን ጃማይካ 7 ጊዜ በማሸነፍ ትከተላለች። እያንዳንዳቸው 3 ጊዜ ማሸነፍ የቻሉት እንግሊዝ ፤ ሞሮኮ፤ ኬንያና ኢትዮጵያ ናቸው።  አልጄርያ፤ ዴንማርክ፤ቼክ፤ ፈረንሳይ፤ ስዊድን፤ ኳታርና ኖርዌይ በወንዶች ምድብ አንድ አንድ አሸናፊዎች አስመዝግበዋል፡፡
 በወንዶች ምድብ ለ5 ጊዜያት በ2008፣ በ2009፣ በ2011፣ በ2012 እና በ2013 እኤአ ላይ በማሸነፍ ጃማይካዊው ዩሴያን ቦልት ከፍተኛውን ስኬት ያስመዘገበ ነው። የሞሮኮው ሂካም አልገሩዥ በ2001፣ በ2002 እና በ2003 እኤአ ለ3 ጊዜያት እንዲሁም ኢትዮጵያዊው ቀነኒሳ በቀለ በ2004 እና በ2005 እኤአ ለሁለት ተከታታይ ጊዜ በመሸለም ተከታታይ ደረጃ ያገኛሉ፡፡ በሴቶች ምድብ ደግሞ ያለፉትን 35 የዓለም ኮከብ አትሌት ሽልማቶች ለማሸነፍ የበቁት 12 አገራት ናቸው፡፡ 11 ጊዜ በማሸነፍ አሜሪካ አንደኛ ደረጃ ስትወስድ፤ 4 ጊዜ ራሽያ፤ 3 ጊዜ ጃማይካና ኢትዮጵያ ፤  2 ጊዜ ጀርመንና እንግሊዝ አሸንፈዋል።    ኒውዝላንድ፣ አውስትራሊያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ክሮሽያ፣ ሮማንያ ፣ ኩባ ፣ ቤልጅየም ፤ ኮሎምቢያና ቬንዝዋል አንድ አሸናፊ ያስመዘገቡ ናቸው።

Read 552 times