Saturday, 14 October 2023 00:00

አጭር ልብወለድ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

ሴት እና ወንድ

ድንግል ነው፡፡ በግል ሀሳቦቹም ሆነ በወሲብ ህይወቱ ድንግል ነው፡፡ ከምንም አይነት ሴት ጋር ቀርቦ ምንም አይነት ፍቅር ሰርቶ አያውቅም፡፡ ጠዋት ተነስቶ ወደ ስራው…ምሽት ላይ ተመልሶ አልጋው ውስጥ መሰተር ነው፤ ለጊዜው ህይወት ለምድር ላይ ትዕይንት የመረጠችለት ገጸባህሪ፡፡ ዛሬ ላይ ሰላሳ አምስት አመቱን እያከበረ ነው፡፡ ሰላሳ አምስት የድንግልና ህይወቱን መልሶ መላልሶ በመርገም ላይ ነው ያለው፡፡ የደወለችለት እናቱ ብቻ ናት፡፡ ከቦረና ሆና ስትደውልልለት ግን ለመልካም ምኞት ሳይሆን፣ ምን ያህል እድሜውን ያለ ሴት አንድዶ እንዳወደመው ልታስታውሰው ነው፡፡ ልደቱ መሆኑን የነገራት ከወቀሳው  በኋላ ነው፡፡
በዚህም ምክንያት ድፍን ምድር ስለሱ የረሳ እንዲመስለው አድርጎታል፡፡ ማንም ሰው የእሱን መፈጠር እንደረሳና ከሱ ጋርም አብሮ መዋልን እንደማይፈልግ ነው የተረዳው፡፡ መልኩ እንደማያምር አምኗል፡፡ አይኖቹ ስሜትን መናገር እንደማይችሉ ጥንቅቅ አድርጎ ከሌሎች ሰዎች በላይ ማስረዳት የሚችለው እሱ ራሱ ነው፡፡ አጠገቡ የሚቆም ሰው እንደ ሰው ቆጥሮት ሲያከብረው አንድም ቀን ሊመለከት አልቻለም፡፡ የፈለገውን ያክል ጮክ ብሎ ቢናገር የሚያደምጠውና አይኑን የሚያሳርፍበት ሰው ቢያስስ ሊያገኝ አልቻለም፡፡ ተመስገን ማለት እንግዲህ ይህ ነው፡፡ በምድር ላይ ሰው መስሎ ተፈጥሮ ሰው የማይቀርበው…የሰው ነፍስ ተሸክሞ ለነፍሱ ሀዘንም ደስታም የሚመጥን ክብርና ትኩረት ያላገኘ፡፡ ራሱን መልከ ጥፉ አድርጎ የሚያስብና ከዚህም በኋላ ማሰብ ቢያቆም ደስተኛ የሚሆን የሚመስለው ባለ ተብከንካኝ ነፍስ ተሸካሚ ፍጥረት ነው፡፡
አንዳንዴም ሰው የሆነ አይመስለውም፡፡ አንዳንዴ ለምን ብሎ ፈጣሪው እንደፈጠረው አይገባውም፡፡ ለማንምና ለምንም ነገር እንዳይረባ ሆኖ መፈጠሩ በራሱ ሳይሆን በፈጣሪው እንዲገረም አድርጎታል፡፡ አንዳንዴ በሰፈሩ ውስጥ የሚያልፉት ውሾች ጋር ቆም ብሎ ሰዎች እንዳያዩት ግራና ቀኙን እያየ ሊያዋራቸው ይሞክራል፡፡ ውሾቹም በማይገባቸው ቃላት ፈገግ ብሎ የሚያወጋቸውን ተመስገንን በመገረም እያዩት መልስ ሳይሰጡት ያልፋሉ፡፡ አንዳንዴ ደግመው ሲያገኙት ከርቀት የሚሸሹትም አይጠፉም፡፡ ሰላሳ አምስት አመት ምድር ላይ ቆይቷል፡፡ ለህይወት ባዶ…ለሀሳብ ባዶ…ለማህበራዊ ህይወት ባዶ…ለፍቅር ባዶ….ለወሲብ ባዶ…ለስሜት ባዶ…ለደስታ ባዶ…ለሀዘን ባዶ የሆኑ ሰላሳ አምስት አመታት ተሸክሞ ምድርን ረጋግጧል፡፡ ከዚህ በኋላ ግን ሌላ አንድ አመት ቢጨምር የሚያብድ እየመሰለው ነው፡፡ ስለዚህ ምርጫ መምረጥ እንዳለበት ማሰብ ጀምሯል፡፡ ወይ አግብቶ መውለድና ህይወቱን አንድ ብሎ መጀመር ….ወይ ደግሞ መሞት፡፡ ዘላለማዊ ፀጥታ ውስጥ መግባት፡፡ ማንም እንዳያየው ማድረግ፡፡ ከዛ…ዝምታ ብቻ፡፡….
ነፃነት ከመኝታ ቤቷ ውስጥ ሆና የከፈተችውን የላፕቶፗን መስኮት በፍፁም ጥበቃ እየተከታተለች ነው፡፡ ከነጋ ማንም የፃፈላት የለም፡፡ ከነጋ ነው ያልኩት…እንደዛ አይደለም ፌስ ቡኳን ከከፈተች ጀምሮ ማንም በመልዕክት ሳጥኗ ውስጥ የሰላምታ ቃላት የሚሆን እንኳን የላከላት የለም፡፡ ለምን እንደሆነ እስካሁን ድረስ ምንም የምታውቀው ነገር የላትም፡፡ እጅግ የምታምር ሴት እንደሆነች ታውቃለች፡፡ ይሄን ለማወቅ ማንም የሚቸገር አልመሰላትም፡፡ የፌስ ቡክ ወዳጆቿ ግን ይሄን ለማየት አልታደሉም፡፡ ዝም ብላ የአንዲት ሎተስ የተባለች አበባ ምስል ነው ፕሮፋይሏ ላይ የለጠፈችው፡፡
ዛሬ ላይ ግን አዲስ ሀሳብ መጥቶላታል፡፡ የምትፈልገውን ወንድ ለማጥመድ እሷ ራሷን የምትረዳባቸውን መንገዶች በጥንቃቄ መቀየስ እንዳለባት አምናለች፡፡ ስለዚህም ምን አይነት ወንድ ነው ይህ ሚድያ እንዲያመጣልኝ የምፈልገው ብላ ማሰብ ጀመረች፡፡
በመጀመሪያ ችግሮቿን የሚረዳላት፡፡ መልኩ ማንኛውንም አይነት ቀለም ተሸክሞ መምጣት ይችላል፡፡ የተማረ፣ ስራውን የሚያከብር፡፡ እንደ ህፃን ልጁ አይቷት የሚንከባከባት፣ ህይወትና ደስታ የራቀው ህይወቷ ውስጥ የድል ችቦውን ይዞ መጥቶ ጨለማዋ ላይ የሚለኩስላት፡፡ ወንድ ትፈልጋለች፡፡ ወንድ የሆነ ወንድ፡፡ ከቃላቱ በላይ የሚያስብ፡፡ ጉልበቱን በቃላት ሳይሆን በተግባር መዝብሮ ማሳየት የሚችል፡፡ ወንድ የሆነ፡፡ ሴትነቷን ብቻ እያየ ክብሯን የሚያፀናላት …ከዛ ደግሞ ነፃነቷን ተቀብሎ በህይወቷ ውስጥ የምትገዛለትና የሚገዛላት ወንድ ነፃነት ፈልጋለች፡፡ የሴትነት ፍላጎቷም ከዚህ አጥር በላይ አይዘልም፡፡
ሆኖም ከወንድ ፊት ቆማ ማውራት አትችልም፡፡ የመንደሩም ሰው የገዛ ቤተሰቧን ጨምሮ የአይነጥላ ድግምት እንደተደረገባት ያወራሉ፡፡ ከውበቷ ብዛት ብዛት ያለው ወንድ በተለያየ መልኩ የትዳር ጥያቄ ለቤተሰቦቿ ቢልኩም ነፃነት ግን ነፃነቷን እንደ መንገድ ላይ  የሽንኩርት ችርቻሮ አስመርጣ የምትሸጥ አይደለችምና የማናቸውንም ጥያቄ ሳትቀበል ቆየች…አሁን ሀያ ስድስት አመቷ ነው፡፡ እወልዳለሁ እከብዳለሁ ካለችው እድሜ ጣራ አለፍ ብላለች፡፡ አሁን ሰዓቷ እንደደረሰ ይገባታል፡፡
ለዛም ነው ከከፈተችው ሶስት ሳምንት የሆናት የፌስ ቡክ አካውንቷን ከፍታ የመጀመሪያውን ተንደርድሮ የመጣውን ወንድ ለማውጋት ያሰፈሰፈችው፡፡ ፍርሀት ከሌለባት እንደልብ ማውራት እንደምትችል አውቃለች፡፡  መወደድ ሳይሆን መውደድ ትፈልጋለች …መታየት ሳይሆን እሷ በፈቀደችው ሰዓትና ቦታ ማየትና ማዳመጥ ትፈልጋለች፡፡ ውበቷ ያመጣባትን የነፃነት እዳ ተደብቃ በዛች የላፕቶፕ መስኮት ውስጥ ማስመለስ ትፈልጋለች፡፡
እየጠበቀች ነው….አንድ ሰው እያየሁሽ ነው እንዲላት …ከዛ ምርጫዎቿ ላይ ልትሰለጥን ዝግጅት ላይ ናት….……
ተመስገን የሆነ ሰው ማናገር ፈልጓል፡፡ ብቻ የሆነ ሰው ብቻ የሆነ ፍጥረት ይሁን….ብቻ ብቸኝነቱን የሚያላቅቅለት ቃላት የተሸከመ ፍጥረት እንዲያናግረው ጉጉት ላይ ነው፡፡ በእርግጥም አሁን ላይ ተቀምጦበት ካለው ካፌ ውስጥ ከሚርመሰመሰው የሰው ዝርያ መካከል አንዱም ቢሆን ወደ እሱ ቀርቦ ምነው ብቻህን ሆንክ የሚለው አካል እንደማያገኝ አውቆታል፡፡ ድንገት ግን አንድ ነገር ትዝ አለው፡፡ ፌስቡክ የተባለ የተባረከ ነገር እንዳለ ትዝ አለው፡፡ በዚህ አለም ውስጥ መተያየት የለም፡፡ ቃላት አሸናፊዎች ናቸው፡፡ አማራጮች ማብቂያ የላቸውም፡፡ ከብዙ ጊዜያት በፊት ከፍቶት የነበረውን አካውንት አስታውሶ ፌስ ቡኩን ከፈተ፡፡ ከዛም በውስጡ መልኮችን ማማረጥ ውስጥ ገባ፡፡ አንድ አገኘ፡፡ ያገኘው አካውንት ግን በፕሮፋይሉ ላይ ምንም አይነት ፎቶ አላስቀመጠም፡፡ ጨለማ ብቻ ነው የሚታየው፡፡ ጨለማ ብቻ ከሆነ ደግሞ ይህ ሰው ሀዘን ላይ ሊሆን ይችላል ብሎ ገመተ፡፡ ወደ ውስጥ ዘልቆ ስለዛ ሰው ማጥናት አልፈለገም …እንደው ብቻ እድሉ ሳያመልጠው….ያ የፎቶ ሳጥን ውስጥ ያለው ጨለማ ከሱ ቀድሞ የመጣ ብርሀን ሳያገኘው በፍጥነት ወጉን መጀመር እንዳለበት ደረሰበትና የመጀመሪያውን ሰላምታ ማቅረብ ጀመረ፡፡
“ሰላም….”
ምላሽ በፍጥነት አላገኘም፡፡ መልዕክቱ ግን እንደታየ ይናገራል፡፡  ጠበቀ ….
“ሰላም…” የሚል ምላሽ ተላከለት፡፡
ምን ብሎ እንደሚመልስ ግራ ገባው፡፡ ብዙ አሰበ፡፡
“መተዋወቅ ይቻላል?” …. ስርዓቱን ጠብቆ እየሄደ እንደሆነ አመነ፡፡ …ጠበቀ….
“ ይቻላል፡፡”  የሚል ምላሽ ቀጠለ፡፡
ማነኝ ብሎ ይተዋወቅ፡፡ ስራ ሲቀጠር ብቻ ነው ስለ ማንነቱ ተጠይቆ የሚያውቀው፡፡ ማንም ስለሱ የህይወት ታሪክ ማወቅ የሚፈልግ የለም፡፡ አልነበረምም፡፡ ስለዚህ እንዴት አድርጎ ስለራሱ ማስረዳት እንደሚችል የሚያውቀው ነገር የለም፡፡ ሆኖም አሁን ግዴታ ራሱ ባመጣው ጥያቄ ውስጥ እስረኛ ሆኖ ከመክረሙ በፊት መልስ መስጠት አለበት፡፡
ቀጠለ…
“ተመስገን እባላለሁ፡፡ ከዚህ በላይ ስለራሴ ማስረዳት የምችል አይመስለኝም፡፡ እንዴት እንደማወራሽም ምናልባት የማውቅ ሰው አይደለሁም፡፡ ምናልባት ይሄን ስልሽ አንቺን ማስጨነቅና እንድትርቂኝ የሚያደርግ ነገር እየፈጸምኩ እንደሆነ አላውቅም፡፡ እንዲሁ ፕሮፋይልሽን ሳየው ሀዘን ውስጥ ያለሽ እንደሆነ ለመጠየቅና ሀዘንሽን ለመጋራት በማሰብ ነው ላወራሽ የመጣሁት፡፡ “
ብዙ ዝምታ፡፡ ድሮም አውቄው ነበር ብሎ አሰበ፡፡ ቃላቱ ለሰው ልጅ እንደማይሆን እንዲሁ ማመን ከጀመረ የቆየ ነፍስ ይዞ እነዚህን ሁሉ ቃላት በመልዕክት ሳጥኑ መላኩ ምን ያህል ደንባራ ፍጥረት እንደሆነ የሚነግረው መሰለው፡፡ ተስፋ ግን መቁረጥ አልፈለገም፡፡ ደግሞ ላከ፡፡
“የምር ሀዘን ላይ ነሽ ያለሽው?”  
አሁንም ምላሽ የለም፡፡ ምላሹም ቢመጣ ፍጥነት የለውም፡፡ ሴቶች ለምን በፍጥነት ማሰብና ማውራት እንደማይችሉ ሲያስብ ግራ ይገባዋል፡፡ እንደገና ደግሞ መለስ ይልና ይሄኔ እንደኔ አይነቱ ስንት አይነት ጣፋጭ ቃላት እየደረደረ ልቧን ማቅለጥ ላይ ነው ይላል፡፡
ድንገት…
“ነፃነት እባላለሁ፡፡”  የሚል መልዕክት ብቅ አለ፡፡ ይሄን ሁላ የተተራመሰ ቃላት ተጠቅሞ መልስ ማግኘቱ ገረመው፡፡ ከሰው ጋር ሳይሆን ከሮቦት ጋር የሚያወራ መሰለው፡፡ የምር ከሰው ጋር ሀሳብ ሊለዋወጥ መሆኑን ተገንዝቦ ራሱን አመቻችቶ ተቀመጠ፡፡ ምንም ያድርግ ምን ያስብ የማያገባው የካፌው ተጠቃሚ ላይ አይኖቹን በኩራት እያጉረጠረጠ ፈገግ ይል ጀመር፡፡
“ነፃነት ስላወኩሽ ደስ ብሎኛል፡፡” አለ…የምሩን ነው፡፡
“እኔም…” ወዲያው ነው መልሱ የመጣው፡፡ መልሱን ተመልክቶ አይኖቹ እንባ አቀረሩ፡፡  ……..
ነፃነት ከተመስገን ጋር በፌስ ቡክ ማውራት ከጀመረች ሁለት ወራት አለፉ፡፡ እንዳየችው ከሆነ ምስኪን ሰው ነው፡፡ የቻለው ድረስ ሳይሰስት እውነተኛ የሚባሉት ሀሳቦቹን ለማስተላለፍ በመሞከር ላይ ነው፡፡ ይህም እንድትንቀው ሳይሆን የባሰ እንድታከብረው አድርጓታል፡፡ ሆኖም ሁለቱም መልካቸው ምን አይነት እንደሆነ የሚያወቁት ነገር የለም፡፡ እንደው በቃላት ብቻ ነፍሶቻቸውን መጓተት ውስጥ ናቸው፡፡
ዛሬ ላይ ግን ከወትሮው ለየት ያለ ስሜት እየተሰማት ነው፤ ከእንቅልፏ የነቃችው፡፡ አለ አይደል…እየናፈቀች ነው የነቃችው፡፡ አይተውት የማያውቁትን ሰው መናፈቅ ምን የሚሉት ነው ብላ አሰበች፡፡  ሆኖም አሁን ከማንም ጋር ማውራት አትፈልግም…የተመስገን ቃላት ከምታውቃቸው ሰዎች በላይ እውነተኛ ናቸው…ቅን ናቸው፡፡ በውስጣቸው ለህይወት የቀረበ ተስፋን ይዘው ነው ወደ ነፍሷ እንደጎርፍ እየፈሰሱ ያሉት፡፡
ፌስ ቡክ ከፈተች፡፡ እንደ ሁልጊዜው አሁንም ተመስገን ኦንላይን ነው፡፡ ፃፈች…
“ተሜ….” አለች፡፡ እንደዚህ ማለት ከጀመረች ቆየች፡፡
“ወዬ…” አለ፡፡ ሁልጊዜ መልዕክቱን እንዳነበበ ነው በፍጥነት የሚፅፈው፡፡ ሁልጊዜ፡፡
“አንድ ነገር ልጠይቅህ? “….ቃላቶቿ ውስጥ አይኖቿን ማየት እንዲችል እያደረገች ነው የምትፅፍለት፡፡ እሱም እያንዳንዱ ነገር ይገባዋል፡፡
“የፈለግሽውን ጠይቂኝ….”
“አሁን ልክ እኔን እንደምታወራኝ የምታዋራቸው ሴቶች አሉ? ካሉስ ስንት ናቸው?”  የእውነትም እስከዛሬ እንደዚህ አይነት ወሬ አውርተው አያውቁም፡፡ ተመስገን የሚያየውን ማመን አቅቶት የሚይዘው የሚጨብጠው ጠፋው፡፡ ጥያቄው ከብዶት አይደለም፡፡ የነፃነት ነፍስ ነው የከበደው፡፡
“አንቺን ብቻ ነው የማናግረው ነፂዬ፡፡ እውነት ነው የምልሽ፡፡ አንቺን ለማውራት ሳስብ ብቻ ነው ፌስ ቡኩን ራሱ የምከፍተው፡፡….እንዴት ዛሬ ይሄን ጠየቅሺኝ?”  
ነፃነት የሚቀጥለውን መልዕክት ከመፃፏ በፊት እጇ ላይ የያዘችው ስልክ አልጋ ላይ አስቀምጣ ትንሽ ተንጎራደደች፡፡ ብዙ አሰበች፡፡ ለማንኛውም በጭንቅላቷ ለሚመጣ ጥያቄ መልስ ሰጠች፡፡ ወደ ስልኳ ተመለሰች፡፡
“እንድንገናኝ አስቤ ነው፡፡ ማለቴ….በአካል፡፡”
ያለወትሮው በመልዕክት ሳጥኑ ውስጥ ፀጥታ ሰፈነ፡፡  
“የምርሽን ነው?” ከብዙ ቆይታ በኋላ፡፡
“የምሬን ነው፡፡”  በፍጥነት መለሰችለት፡፡ ለምን ቆይቶ እንደመለሰላት መጠየቅ አልፈለገችም፡፡ ብቻ እሺ እንዲላት ብቻ ነው የምትፈልገው፡፡ መልስ ሳታገኝ መሸ፡፡ ብዙ ፀጥታ፡፡ ብዙ ትካዜ፡፡ ብዙ ተስፋ መቁረጥ፡፡ ብዙ ፍርሀት፡፡ ብዙ ጥያቄዎች፡፡ ለነዚህ ነገሮች ሁሉ አሳልፎ ሰጣት፡፡ እሱ አይታወቀውም፡፡ እሱ ስለሚሆነው ነገር ምንም እውቀት የለውም፡፡ ነፃነት ግን ተደብቃበት ከነበረው ራስን የመሸሽና ራስን የመጥላት ስሜት አሳዶ ያወጣት  ይህ ሰው፣ ለሷ ሳታስበው የፈጣሪ ስጦታ ከሆነ ቆየ፡፡ አሁን ህይወቷ ውስጥ ማንንም ሳይሆን የምትፈልገው ተመስገንን ብቻ ነው፡፡ ሌላው ነገር በሙሉ እርግማኗ እንደሆነ ነው እየተረዳች ያለችው፡፡ ተመስገንን አግኝታ ፈጣሪዋን ተመስገን ማለት ነው የምትፈልገው፡፡ አለበለዚያ ግን የብቸኝነቷ ጨለማ ውጦ ሊሰለቅጣት እንደሚችል አምናለች፡፡
መሽቶ ነጋ …መልሶ መሸ፡፡ ተመስገን መልስ አልሰጠም፡፡
…..
ተመስገን ካለበት አልጋ ላይ ሆኖ በትካዜ ከፊት ለፊቱ ያስቀመጠው መስታወት ላይ አይኖቹን አትሞ በሀሳብ ገመድ የማያውቀው የስሜቱ ማማ ላይ ለመድረስ ምጥ ላይ ነው፡፡ ነፃነት ፍቅር ውስጥ እንደገባች መጠርጠር አልፈለገም፡፡ ነገር ግን ፍቅር ውስጥ የገባችው ከእሱ ሳይሆን ከቃላቶቹ እንደሆነም ይረዳል፡፡ የትኛውን ተመስገን አሳምኖት ነፃነትን በአካል ማግኘት እንዳለበት ግን ሊያውቅ አልቻለም፡፡ ከራሱ ጋር ሳይታረቅ የነፃነትን አይኖች መመልከት እንደማይችል ጠንቅቆ ይረዳል፡፡ ምን ማድረግ እንዳለበት የሚያዋየው ከራሷ ከነፃነት ውጭ ማንም የለም፡፡
ነፃነት የህይወት ዘመን ጥያቄ መልሱ ናት…ለሱ የገባው ይሄ ነው፡፡
ሆኖም ጊዜያቶች በነጎዱ ቁጥር የተመስገንም ስሜት በነፃነት ላይ መቀዝቀዝ ጀመረ፡፡ ሌሎች ወንዶች ሲያወሩ ሲሰማ ይገረም ነበር፤ አሁን ግን ገባው፡፡ ወንድ ልጅ በልፋት ያገኛትን ሴት ልጅ ነው የሚፈልገው እንጂ በልመና የምትፈልገውን ሴት ሊቀርብ አይፈቅድም የሚለው ሀሳብ ራሱ ላይ ሲከሰት መደንገጥ ጀመረ፡፡ ነፃነት ምንም አይነት ሴት ልትሆን ትችላለች ነገር ግን እሱ ቀድሞ የመገናኘት ፍላጎት ሳይኖረው እሷ ቀድማ ጠየቀችው፡፡ ቀድማው ፈለገችው፡፡ ቀድማው በርቀት ደብቆ ያስቀመጠውን ስሜቱን በራሷ ቃላት ተረከችበት፡፡ ምናልባት ተበሳጭቶባት ሊሆን ይችላል፡፡ ምናልባት የማይለቅ የሚመስለው የወንድ ልጅ ኩራት ከነፍሱ ተጣብቶ አልላቀቅ ብሎትም ሊሆን ይችላል…የትኛው እንደሆነ ሳያውቀው ነፃነትን ናቃት፡፡
……
ነፃነት ለተጨማሪ ሁለት ተከታታይ ወራት ተመስገን ጋ እየፃፈች ፈለገችው፡፡ የምር ፈለገችው፡፡ ሆኖም ተመስገን የለም፡፡ ድንገት ከሌሎቹ ምናንምቴ የወንድ አይነቶች ጋር ተቀላቅሎ ተሰውሮ እንደሆነ ጠርጥራለች፡፡ ሆኖም ይህ የሀሳብ ግኝት ተመስገንን እንድትጠላው ሳይሆን ይባሱኑ እንድትፈልገውና እንድትወደው አደረጋት፡፡ ለምን እንደሆነ የሴትነት እውቀቷ ሊያስረዳት አልቻለም፡፡ የሚሰማትን ስሜት የምታጋራው ሰው የላትም፡፡ ነፃነት ለጊዜው መውደድ ብቻ ነው የምትችለው …መጠበቅ ብቻ፡፡ እንዲህ አድርጎ የሀሳብ ቅርፊቱ ውስጥ የከተታት ደግሞ ተመስገን ነው፡፡
……
ተመስገን የፌስ ቡኩ አለም ተመችቶት ቁጭ አለ፡፡ ከነፃነት ጋር ያደረገው ንግግር ከሌሎች ሴቶች ጋር በነፃነት ማውራት እንዲችል አድርጎታል፡፡ ከመልኩ ይልቅ ቃላቶቹ የውበቱ መገለጫዎች እንደሆኑ አምኖ ያገኛቸውን ሴቶች በሙሉ በሆሄያት ጥበብ ማንዘሩን ተያያዘው፡፡ አምኗል…የትኛዋም አይነት ሴት አይታው ልትወደው እንደማትችል፡፡ ሆኖም ባልገባው መንገድ እነዚህን ሴቶች መበቀል ላይ እንደሆነ አንድ ቀን ተገለፀለት፡፡
ፍቅር የማይገባቸው፣ በቁስ ሱስ ምክንያት ቁሳዊ እብደት ውስጥ ተሰትረው የተከረቸሙ፣ ህይወት የማይገባቸው፣ ሀሳብን ማድመጥ የማይችሉ፣ ቂጣቸውን ማስፋት ውበታቸውንና እድላቸውን እንደማስፋት አድርገው የሚያስቡ፣ ገንዘብ ሲያዩ ነፍስ የሚዘሩ፣ ውሸትን መምጠጥ የሚችል ስፖንጅ ጭንቅላት የተሸከሙ፣ ሀሜት የማይሰለቻቸው፣ እርስ በራሳቸው የማይዋደዱ፣ የሚቀናኑ፣ ተፈጥሮ ቁጥሩ በማይታወቅ ብዛት የረገመቻቸው ፍጥረቶች እንደሆኑ ማመን ከጀመረ ቆየ…ሴት የተባለች ፍጥረት ሁላ፡፡ ስለዚህ እንዲህ ካለች ፍጥረት ጋር ኖርኩኝ አልኖርኩኝ ጉዳዬ አይደለም ብሎ ደመደመ፡፡ ውበቱንም የዚያው ውሳኔው ውስጥ አገኘው…ወንድነቱን፡፡ እስከዛሬ ሴቶችን የፈራቸው ስለማያውቃቸው እንደሆነ ተገነዘበ፡፡ ስለዚህ ተዋቸው፡፡ ልክ ይሄን ያሰበ ቀንና መወሰኑን የተረዳ ደቂቃ ላይ የተነፈሳት ትንፋሽ…እፎይታው… ለኔ ለፀሀፊው እንኳን ያልተረዳሁት የነፍስ መቅለል ስሜት እንዲሰማው አድርጎታል፡፡
……
ነፃነት ከወንድ ጋር ካወራችም ሆነ ሰላምታ ከተለዋወጠች ዘመናት አለፉ፡፡ ስታስባቸው ራሱ ያንገሸግሻታል…ወንዶችን፡፡ ከአሁን በኋላ ወንዶች ማለት ለነፃነት…
ውሸታሞች፣ ክብር የማይወድላቸው፣ መፈቀር እርግማናቸው የሆነ፣ በፍቅር ህይወት ውስጥ ሀላፊነት መውሰድ የማይፈልጉ ፈሪዎች፣ የመለመን ሱስ የዳጣቸው የሴት ገላ ባሪያዎች፣ ወሲብ አምላካቸው…ዝሙት ድላቸው የሆነባቸው፣ የሴት ልጅን ነፍስ እንደ ካልሲያቸው በፈለጉት ሰዓት የሚለብሱትና የሚጥሉት አድርገው ሁልጊዜ የሚያስቡ፣ ከራሳቸው በላይ ሴትን ልጅ የሚያውቁ የሚመስላቸው፣ ጨካኞች፣ ሀሳባቸው ብቻውን የሚያሳምም፣ ውሸታሞች፣ ውሸታሞች፣ ውሸታሞች፣ ውሸታሞች፣ ውሸታሞች፣ ውሸታሞች፣ ውሸታሞች…..ወንዶች ማለት ለነፃነት አሁን ላይ እንዲህ ይገለፃሉ፡፡
ስለዚህ ወንድ ልጅን ለማፍቀር የሚበቃ የህሊና ክፍተት በጭንቅላቷ ልታገኝ ስላልቻለች፣ አይኖቿን አይኖቿ ሊያዩት ወደማይችሉት ፈጣሪዋ መለሰቻቸው፡፡ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ሆና በድንግልና ወደ ገዳም የሚሰዳትን የመለኮታዊ እውቀት እስክትጠግብ በጭንቅላቷ ተመገበች፡፡ ወንድ ዝር የማይልበት ገዳም ውስጥ ገብታ ራሷን በምታመልከው ፈጣሪዋ እውቀት ውስጥ ማንም እንዳይደርስባት አድርጋ አጠፋችው፡፡
እንግዲህ ይሄው ነው፡፡ አንድ የህይወት ቅፅበት ዘላለምን ሲተውን ማለት ይሄው ነው፡፡ በነፃነትና በተመስገን ውስጥ ያሉት የሴትና የወንድ ትርጓሜዎችና እውቀቶች አሁን ላይ እኛ ጋር አሉ፡፡ ወንድ ማለት…ሴት ማለት…እያልን የምንገልፃቸው ፍጥረቶች ራሳችንን እንደሆነ እስክንረዳ ድረስ ሴት የወንድ ልጅ ፈተናው፣ ወንድ ደግሞ የሴት ልጅ ድክመቷ እየሆኑ ዘላለም ይነጥባል፡፡ ትርጓሜያችን ምንም ያህል እውነቱን እንደሚስት ብንረዳም እርስ በራሳችን ዘወትር እንግዳ ፍጥረቶች ሆነን ምድርን ትተን እንሄዳለን፡፡ እዚህ ድረስ ነው እውቀታችን የመራን…..ወንድ ሴትን ለመረዳት ሴትም ወንድን ለመርዳት የተፈጠርን ፍጥረቶች አድርገን ራሳችንን እየሰራን፡፡

Read 919 times