Tuesday, 17 October 2023 00:00

ሀበሻ ቪው 4ኛ ዙር የፊልም ፌስቲቫሉን በለንደን ከተማ ሊያካሂድ ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ሀበሻ ቪው 4ኛ ዙር የፊልም ፌስቲቫሉን በለንደን ከተማ ሊያካሂድ ነው

ሀበሻ ቪው 4ኛ ዙር የፊልም ፌስቲቫሉን በእንግሊዝ አገር ለንደን ከተማ በቅርቡ ሊያካሂድ ሲሆን፤ የቅድመ መክፈቻ ሥነሥርዓቱን ባለፈው ቅዳሜ ጥቅምት 3 ቀን 2016 ዓ.ም ምሽት በሃያት ሪጀንሲ ሆቴል አካሂዷል፡፡

በዘንድሮው የለንደኑ የኢትዮጵያ ፊልም ፌስቲቫል ለዕይታ የተመረጡት  “ጸጸት” እና “ዝምታዬ” የተሰኙት ሁለት የኢትዮጵያ  ፊልሞች ሲሆኑ፤ የፊታችን ጥቅምት 17 እና 18 ቀን 2016 ዓ.ም በለንደኑ ሪትዚይ ሲኒማ ለዕይታ እንደሚቀርቡ  ታውቋል፡፡

በምሽቱ መርሃግብር ታዋቂ የፊልም ፕሮዱዩሰሮች፣ አዘጋጆችና ተዋናዮች እንዲሁም የፊልም ጥበብ ቤተሰቦች ታድመዋል፡፡

የፊልም ፌስቲቫሉ ዓላማ፤ ኦሪጂናል የኢትዮጵያ ፊልሞችንና ተሰጥኦ ያላቸው ፊልም ሰሪዎችን በመላው ዓለም ለማስተዋወቅና ትኩረት እንዲያገኙ ለማድረግ  ነው ተብሏል፡፡

በመርሃግብሩ ላይ  ንግግር ያደረጉት የሀበሻ ቪው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ትዕግስት ከበደ፣ በፌስቲቫሉ የሚሳተፉ ፊልሞች ከሚመረጡባቸው መስፈርቶች መካከል በአገራችን ቋንቋ መሰራታቸውና ኦሪጂናል መሆናቸው ነው ብለዋል፡፡ ድርጅቱ ፊልሞቹን የሚመርጡና የሚገመግሙ ከ20 በላይ ባለሙያዎች እንዳሉትም ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ጠቁመዋል፡፡

በምሽቱ ለኢትዮጵያ ፊልም ዕድገትና አሁን ያለበት ደረጃ ላይ መድረስ አስተዋጽኦ ያደረጉ ግለሰቦችና ተቋማት ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡ በዚህም መሠረት፤ የዛሬ 60 ዓመት ለተሰራው “ሂሩት አባቷ ማነው“ የተሰኘው የመጀመሪያ ኢትዮጵያዊ  ፊልም መሥሪያ የገንዘብ ብድር የሰጠው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ እንዲሁም የዛሬ 30 ዓመት የተሰራውን “ጸጸት” ፊልም ፕሮዱዩስ ያደረጉት የመጀመሪያዋ ፕሮዱዩሰር ወ/ሮ ሩቅያ መሃመድ ምስጋናና ዕውቅና ከመድረኩ ተችሯቸዋል፡፡

ሀበሻ ቪው ለመጀመሪያ ጊዜ በምሽቱ ባከናወነው የሽልማት (Award) መርሃግብር ላይ ለአንድ ጎምቱ የኪነጥበብ ባለሙያና ለሁለት ተቋማት ሽልማቶችን አበርክቷል፡፡

በግለሰብ ደረጃ ከሀበሻ ቪው የመጀመሪያው ሽልማት የተበረከተላቸው ለ60 ዓመት ከኪነጥበብ ያልተለዩትና አያሌ የጥበብ ባለሙያዎችን ያፈሩት ጋሽ ተስፋዬ አበበ (ፋዘር) ሲሆኑ፤ በተቋም ደረጃ ባለቤትነቱ የአትሌት ሃይሌ ገ/ሥላሴ የሆነው ዓለም ሲኒማና የአዲስ አበባ ከተማ ሲኒማ ቤቶች አስተዳደር ናቸው፡፡

ሀበሻ ቪው ያዘጋጀውን  ሽልማት  ለተሸላሚዎች ያበረከቱት የምሽቱ የክብር እንግዳና ጎምቱው የኪነጥበብ ባለሙያ እንዲሁም የመጀመሪያው የግል ቴአትር ቤት (ቀንዲል) ባለቤት የሆኑት ጸሃፌ ተውኔት አያልነህ ሙላት ናቸው፡፡

ሀበሻ ቪው ቴክኖሎጂና መልቲ-ሚዲያ እ.ኤ.አ ከ2015 ጀምሮ በሥራ ላይ የሚገኝ ድርጅት ሲሆን፤ በአፍሪካዊነትና ተያያዥ ርዕሰጉዳዮች ላይ ይዘቶችን በማበልጸግ ይታወቃል፡፡ ድርጅቱ በአሜሪካ ቨርጂኒያ የተመዘገበ የንግድ ምልክት ሆኖ ሲሰራ የቆየ ሲሆን፤ እ.ኤ.አ ከ2020 ጀምሮ ደግሞ በኢትዮጵያም ተመዝግቦ እየሰራ ይገኛል፡፡

Read 990 times