Saturday, 21 October 2023 20:06

የእናት ጡት ወተት

Written by  ሀይማኖት ግርማይ ከኢሶግ
Rate this item
(1 Vote)

 እኤአ በ2022 በወጣው የዩኒሴፍ እና የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ መሰረት በዓለም አቀፍ ደረጃ ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆነ ህፃናት በተቆራረጠ ሁኔታም ቢሆን የእናት ጡት ማግኘት ችለዋል። በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደተወለዱ በ1 ሰአት ጊዜ ውስጥ የእናት ጡት ወተት ማግኘት የቻሉት 43 በመቶ ሲሆኑ ለ6 ወራት የእናት ጡት ብቻ ያገኙት ደግሞ 44 መቶ ናቸው።
በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚኒሊየም ሜዲካል ኮሌጅ የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ሳሮን ተካ እንደተናገሩት የእናት ጡት ወተት ለተወለደ ልጅ አስፈላጊ የሚባሉ ንጥረነገሮችን የያዘ ፈሳሽ ነው። በውስጡ ከያዘው ንጥረነገሮች መካከል ሀይል ሰጪ (ካርቦሀይድሬት)፣ ፕሮቲን፣ ቅባት፣ ቫይታሚን እና ሚነራል ይጠቀሳል። በሽታ የመከላከል አቅም የሚጨምር ለሰውነት አስፈላጊ የሆነ ንጥረነገር በበቂ መጠን እና ይዘት በውስጡ ይዟል።  
የእናት ጡት ወተት የሚመረትበት ሁለት ደረጃዎች አሉ። በመጀመሪያ ደረጃ የሚመረተው በእርግዝና 4 ወይም 5ኛ ወር ላይ ነው። በዚህ ወቅት ነፍሰ ጡር ሴቶች በጡት ጫፍ ላይ ወተት (ፈሳሽ) ሊያዩ ይችላሉ። የጡት ወተት በብዛት የሚመረተው ልጅ ከተወለደ በኋላ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ነው። ልጅ ከተወለደ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚፈሰው ወተት(እንገር) በሽታ የመከላከል አቅም የሚሰጥ ንጥረነገሮችን ያያዘ መሆኑን የህክምና ባለሙያዋ ተናግረዋል። ስለሆነም በተለምዶ እንገር አላስፈላጊ ነው በሚል ለልጆች እንዳይሰጥ የማድረግ ሁኔታ(እሳቤ) የተሳሳተ መሆኑን አክለው ተናግረዋል።
ልጅ በተወለደ በአማካይ በ1 ሰአት ጊዜ ውስጥ የእናት ጡት ወተት እንዲያገኝ ይመከራል። እንዲሁም በአንድ ቀን ውስጥ ከ8 እስከ 12 ጊዜ ጡት መጥባት አለበት። ይህም ማለት አንድ ልጅ በ2 ወይም በ3 ሰአት ልዩነት ውስጥ የእናት ጡት ያገኛል። ልጅ ከተወለደ በኋላ ለ6 ወራት የእናት ጡት ወተት ብቻ ነው ማግኘት ያለበት። እንዲሁም እስከ 2 ዓመት ከሚወስደው ምግብ በተጨማሪ የእናት ጡት ወተት እንዲያገኝ ይመከራል። ነገር ግን እናቶች በበሽታዎች እና በተለያዩ ምክንያቶች ጡት እንዳያጠቡ የሚደረግበት ወይም የሚገደብበት ሁኔታ ይኖራል። ይህንን ማወቅ የሚቻለው የህክምና ባለሙያ በማማከር ነው። እናቶች ማንኛውንም አይነት መድሀኒት ሲወስዱ የህክምና ባለሙያ ሊያማክሩ ይገባል።
የእናት ጡት ወተት ለልጅ ያለው ጥቅም
ምግብ ወደ ሰውነት ሲሰራጭ የሚተላለፍበት ትቦ እንዲያድግ(እንዲዳብር)
በሽታ የመከላከል አቅምን ማዳበር
ያለ ጊዜ የተወለደ ልጅ ከሚያጋጥሙት በሽታዎች ለመከላከል
በልጅነት ሊከሰት ከሚችል ስኳር፣ ካንሰር እና ከመጠን ካለፈ ውፍረት ለመከላከላል
ለአእምሮአዊ እድገት
ጡት ማጥባት ለእናት የሚሰጠው ጥቅም
ልጅ(ፅንስ) የተቀመጠበት የማህፀን ክፍል ወደነበረበት እንዲመለስ (እንዲኮማተር) ያደርጋል
ከደም መፍሰስ ይከላከላል
እንደ ወሊድ መቆጣጠሪያ ያገለግላል
የሰውነት ክብደት መጨመርን ይከላከላል
ከወሊድ በኋላ የሚኖር የድብርት ስሜት እንዲቀንስ ያደርጋል
በጡት እና ማህፀን ካንሰር የመያዝ እድልን ይቀንሳል
ለእናት ጡት ወተት ምትክ ለሚወል ግብአት መግዣ[አላስፈላጊ ወጪ] የሚውል ገንዘብ ይቀንሳል የዩኒሴፍ መረጃ እንደሚያሳየው በዓለምአቀፍ ደረጃ እናቶች በሥራ ቦታዎች ላይ ድጋፍ አለማግኘታቸው ለ6 ወራት የእናት ጡት ወተት ብቻ እንዳይሰጡ እንቅፋት ሆኗል። 15 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች ጡት ማጥባት እንዲቀጥሉ ከሚሰሩበት አከባቢ ምንም አይነት ድጋፍ አያገኙም። ከወሊድ በኋላ እናቶች ተገቢውን የስራ ክፍያ እንዲያገኙ የሚያደርጉት 12 በመቶ የሚሆኑ ሀገራት ናቸው። እናቶች ከወሊድ በኋላ የሚኖራቸው እረፍት በጨመረ ቁጥር ጡት የማጥባት ሁኔታቸውም እየጨመረ ይሄዳል።
አንዲት እናት ጡት እንድታጠባ የተመቻቸ አከባቢ፣ በቂ እረፍት፣ የተስተካከለ(የተመጣጠነ) አመጋገብ፣ ቢያንስ ለ6 ወራት ከልጇ ጋር አካላዊ ቁርኝት እና በጤና ባለሙያዎች የሚመከሩ ልጅ ለማጥባት የሚያስፈልጉ ሁኔታዎችን(አቀማመጥ፣ ልጅ አያያዝ እና መሰል ጉዳዮች) ማግኘት አለባት። የሚያጠቡ እናቶች ብዙ ፈሳሽ እንዲያገኙ በማሰብ በተለምዶ የአልኮል መጠጦችን እንዲወስዱ ሲበረታታ ይስተዋላል። ነገር ግን የአልኮል መጠጥ መውሰድ የተከለከለ መሆኑን ዶ/ር ሳሮን ተካ ተናግረዋል። እናት በስራ እና በተለያየ ምክንያት ከልጇ አጠገብ ሆና ማጥባት በማትችልበት ወቅት የጡት ወተት በማለብ ለልጇ መስጠት ትችላለች። ወተቱ የሚታለብበት እና የሚቀመጥበት እቃ ንፅህናው የተጠበቀ እንዲሆን ማድረግ እንዲሁም እንዳይበላሽ ቀዝቃዛ ቦታ ማስቀመጥ ያስፈልጋል።  
 በዩኒሴፍ እኤአ በ2018 የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው ከአደጉ ሀገራት ይልቅ በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራት ጡት በማጥባት ዙሪያ የተሻለ አፈፃፀም አላቸው። ሩዋንዳ 86.9 በመቶ፣ ብሩንዲ 82.3 በመቶ፣ በስሪላንካ 82 በመቶ፣ የሰለሞን ደሴቶች 76.2 በመቶ እና በቫኑዋቱ 72.6 በመቶ ህፃናትን ለ6 ወራት የእናት ጡት ብቻ በመስጠት በቅደም ተከተል ተቀምጠዋል። ጥናቱ እንደሚያሳየው በገጠር የሚኖሩ ጨቅላ ህጻናት ከከተማ ህጻናት የበለጠ የእናት ጡት ያገኛሉ።
የእናት ጡት በአግባቡ ያላገኙ ልጆች በሽታ የመከላከል አቅማቸው ዝቅተኛ መሆን፣ በልጅነት የሚያጋጥም የስኳር፣ ካንሰር እና ከመጠን ያለፈ ውፍረት እንዲሁም በተለይ የላም ወተት በሚጠቀሙ ልጆች ላይ ቀይ የደም ሴል ማነስ ሊያጋጥም ይችላል። በዓለምአቀፍ ደረጃ በአንድ ዓመት ውስጥ እድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች የሆኑ ከ820ሺ በላይ ህፃናት ጡት ካለመጥባት ጋር በተያያዘ ህይወታቸው ያልፋል። ልጆች የእናት ጡት ወተት በአግባቡ እንዲያገኙ በማድረግ የህፃናትን ሞት መቀነስ ይቻላል። እንዲሁም ጡት ማጥባት ለልጆች ብቻ ሳይሆን በጡት ካንሰር የሚሞቱ 20ሺ እናቶችን ለመታደግ ይረዳል።
እናቶች ጡት በሚያጠቡበት ወቅት የተለያዩ ችግሮች ሊያጋጥሟቸው ይችላሉ። ከዚህም ውስጥ የወተት ምርት ማነስ እና የጡት ጫፍ ላይ ኢንፌክሽን መኖር ይጠቀሳል። የጡት ጫፍ ላይ የማበጥ፣ የማሳከክ፣ የመሰነጣጠቅ፣ የቁስለት፣ መቅላት እና የመድረቅ ሁኔታ እንዲሁም የትኩሳት ወይም የቅዝቃዜ(ብርድ) ስሜት ሲኖር የጡት ጫፍ ኢንፌክሽን ሊሆን ስለሚችል የህክምና ባለሙያ ማማከር ያስፈልጋል። ከእናት በተጨማሪ በልጁ ላይ ምቾት ያለመኖር፣ የማልቀስ፣ በአግባቡ እንቅልፍ ያለመተኛት፣ እጅ ወይም ሌላ ቁስ ወደ አፍ መክተት፣ የሽንት ማነስ፣ የክብደት ማነስ እና በአጠቃላይ የፀባይ ወይም የሁኔታዎች መለዋወጥ ሲኖር ወደ ህክምና ተቋም በመሄድ ችግሩን ማወቅ እንደሚያስፈልግ ዶ/ር ሳሮን ተካ ተናግረዋል።
የህክምና ባለሙያዋ ጡት ከማጥባት ጋር ተያይዞ ለሚነሱ ችግሮች እንደ መፍትሄ ያስቀመጡት የህክምና ባለሙያዎች በሚሰጡት ምክር መሰረት ጡት ማጥባትን በአግባቡ መተግበርን ነው። እንዲሁም ከበሽታ እና ከሌሎች ችግሮች ጋር በተያያዘ ጡት ማጥባትን የሚያስተጓጉሉ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ የህክምና ባለሙያ ማማከር ያስፈልጋል። በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚኒሊየም ሜዲካል ኮሌጅ የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ሳሮን ተካ ልጆች ለ6 ወራት የእናት ጡት ወተት ብቻ ማግኘት እንዳለባቸው፣ እስከ 2 ዓመት ከምግብ በተጨማሪ የእናት ጡት ማግኘታቸው መቀጠል እንዳለበት እና ማንኛውም አይነት ችግር ሲኖር የህክምና ባለሙያ ማማከር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

Read 576 times Last modified on Saturday, 21 October 2023 20:21