Tuesday, 03 October 2023 00:00

ዝምተኛ ልቦች

Written by 
Rate this item
(7 votes)
አርቲስት ጌትነት እንየው
አምነው የወደዱ፣
ወደው የተካዱ፣
ተክደው የራዱ፣
ፍርሃት አንሸራቶ ቁልቁል የጣላቸው፣
የብቸኛ ልቦች የትነው መውደቂያቸው?
የትነው መድረካቸው?
ማነው አጃቢያቸው?
እንዴት ነው ምታቸው?
የተካዱ ልቦች አጋር የራቃቸው፣
የሚያቀነቅኑት ምንድን ነው ዜማቸው?
የተመረኮዙት እምነት ታጥፎባቸው፣
ድንገት የወደቁ ፍቅር ያዳጣቸው፣
ሚስጥር የሚያጋሩት ሰው የበረዳቸው፣
ብቸኝነት ሰርጎ ብቻ ያስቀራቸው፣
ዝምተኛ ልቦች ምን ይሆን ቋንቋቸው?
ከየት ነው ጥሪያቸው?
በየት ነው ጉዟቸው?
የት ነው መድረሻቸው?
እንደ ሰብአሰገል ጠቅሶ የሚመራቸው፣
የቃተቱ ልቦች የታል ኮከባቸው?
መቼም ከአምላክ ትንፋሽ ከውሃ ከአፈሩ፣
ከእምንት እና እውነት ከፍቅር ሲሰሩ፣
ዝምተኛ ልቦች ጥንቱን ሲፈጥሩ፣
ተገፍትረው ወድቀው፣
ደቀው እንዳይቀሩ፣
በተስፋ ጸንተው ነው ዘላለም ሊኖሩ።
Read 1672 times