Saturday, 28 October 2023 20:22

ዳሽን ባንክ ባለፈው ዓመት 18 ቢ. ብር ገቢ ማስመዝገቡን አስታወቀ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

 - ከግብር በፊት 5ቢ.ብር ትርፍ ማግኘቱም ተተቁሟል
          - የባንኩ አጠቃላይ ሀብት ወደ 144 6 ቢ.ብር አድርጓል
                 
         ዳሽን ባንክ፤ ባለፈው የበጀት ዓመት 18 ቢ. ብር ገቢ ማስመዝገቡን አስታውቋል። ባንኩ ይህን የገለፀው ከትናንት በስቲያ ጥቅምት 15 ቀን 2016 ዓ.ም የባለ አክስዮኖች 30ኛ መደበኛ ጉባኤውን ባካሄደበት ወቅት ነው። ጉባኤውን በንግግር የከፈቱት የባንኩ የቦርድ ሊቀመንበር አቶ ዱላ መኮንን የበጀት ዓመቱ በብዙ ዓለም አቀፍና የሀገር ውስጥ አሉታዊ ተፅዕኖዎች ስር የወደቀ ነበር ካሉ በኋላ፣ ከዓለም አቀፍ ተጽዕኖዎች ውስጥ  በሩስያና በዩክሬን ጦርነት ምክንያት በዓለም የምርት አቅርቦት ላይ ያስከተለውን ጫና እና ቻይና በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ሳቢያ ያወጣችው ፖሊሲ በዓለም የምርት መጠን ላይ በአጠቃላይ ያደረሰውን አሉታዊ ተፅዕኖ አንስተዋል።


በሀገር ውስጥ ያለውን ሁኔታ በተመለከተም ባለፈው በጀት ዓመት የነበረው ማህበራዊና ፖለቲካዊ አለመረጋጋት፣ ሚዛናዊ  ያልሆነ የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታ በባንክ ኢንዱስትሪው ላይ ቀላል የማይባል አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን ያብራሩት የቦርድ ሊቀመንበሩ፤ በዚህም አገራዊ የኢኮኖሚ እድገቱ በውጪ ምንዛሬ እጥረት፣ ቀጣይነት ባለው የዋጋ ግሽበት፣ በበጀት ክፍተትና በውጭ ብድር ተፅዕኖ ውስጥ እንዲወድቅ ማስገደዱንም አብራርተዋል።


ምንም እንኳን ያለፈው በጀት ዓመት በበርካታ ተግዳሮቶች ተፅዕኖ ስር የወደቀ ቢሆንም ዳሽን ባንክ ተፅዕኖዎቹን ሁሉ ተቋቁሞ በውጤታማነት ዓመቱን ማጠናቀቁን የቦርድ ሊቀመንበሩ አቶ ዱላ አብራርተዋል።
ባንኩ በዚሁ ያለፈ የበጀት ዓመት ተጨማሪ 23 ነጥብ 6  ቢሊዮን ብር ተቀማጭ ገንዘብ መሰብሰቡንና አጠቃላይ ሀብቱን ወደ 144.6 ቢሊዮን ብር ማድረስ መቻሉም ተብራርቷል። ባንኩ በበጀት ዓመቱ 18 ቢሊዮን ብር ገቢ ያስመዘገበ ሲሆን፤ ከትርፍ አኳያም ከግብር በፊት 5 ቢሊዮን ብር ማትረፉንና ይህም ትርፍ ከቀድሞው ዓመት ትርፍ ጋር ሲነፃፀር የ31 ነጥብ 9 በመቶ ብልጫ ማሳየቱ ተገልጿል።
ባንኩ የቀደመውን አምስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ አጠናቅቆ በቀጣይ አምስት ዓመታት የሚተገብረውን አዲስ ስትራቴጂክ እቅድ ማዘጋጀቱን ገልፆ ይህ አዲስ ዕቅድ የደንበኞችን አገልግሎት በማሻሻል፣ አገልግሎቱን ይበልጥ በማዘመንና የባንኩን ቀጣይ ዕድገት በማረጋገጥ ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ የቦርድ ሊቀመንበሩ ተናግረዋል።


የደሽን ባንክ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አስፋው አለሙ በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር  ባንኩ ተደራሽነቱን ከማስፋት፣ ደንበኞች ከማምጣትና ሀብት ከመሰብሰብ አኳያ አዎንታዊ ውጤቶች የተመዘገበበት ዓመት ነበር-ብለዋል። ከውጤቶቹም መካከል በበጀት ዓመቱ 253 አዳዲስ ቅርንጫፎችን በተለያዩ የገሪቱ ክፍሎች መክፈቱን፣ በዚህም የቅርንጫፎቹን ብዛት ከ835 በላይ ማድረሱን በአርአያት የጠቀሱት አቶ አስፋው፤ ይህም ባንኩ ለደንበኞች ይበልጥ ተደራሽ ለመሆን የሚያደርገውን ጥረት ያግዛል ብለዋል።
በቅርቡ የባንክ ኢንዱስትሪው ለውጪ ባንኮች ክፍት እንደሚያደርግ መገለጹንና የካፒታል ገበያ ይቋቋማል መባሉን ተከትሎ ዳሽን ባንክ በዚህ ረገድ አስፈላጊውን ዝግጅት እንደሚያደርግም ዋና ስራ አስፈጻሚው ተናግረዋል።


5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ደንበኞች ያሉት ዳሽን ባንክ፤ በባንክ ኢንዱስትሪው የመጀመሪያ የሆነውን 40 ሚሊዮን ዶላር የውጪ ብድር ማግኘቱን ያስታወሱት አቶ አስፋው፣ ይህም በዘርፉ ያለውን የውጪ ምንዛሬ እጥረት ከመቅረፍና የግብርና ምርት ወደ ውጪ ከመላክ አንጻር ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖረው አብራርተዋል። ባንኩ ማህበራዊ ሃላፊነቱን ከመወጣት አንፃር ባለፈው የበጀት ዓመት በርካታ ተግባራትን ማከናወኑን ያብራሩት ዋና ስራ አስፃሚው ለዚሁ ተግባርም ከ285 ሚ. ብር በላይ ወጪ መደረጉን ጠቁመዋል።
ባንኩ ለደንበኞቹ ምቹና ቀልጣፋ አሰራርን ብሎም አዳዲስ ቴክሎጂዎችን በመተግበር ቀዳሚ ነው የተባለ ሲሆን ባለፈው ሳንት ቅዳሜ ከሸዋ ሱፐርማርኬት ጋር ለመወያየት የሚያስችል የስጦታ ካርድ መገናኛ በዘፍመሽ ሞል ስር በሚገኘው ሸዋ ሱፐር ማርኬት ውስጥ አስተዋውቋል።

Read 609 times