Saturday, 04 November 2023 00:00

የቴአትር እና የቴሌቪዥን ፌስቲቫል እየተካሄደ ነዉ

Written by 
Rate this item
(0 votes)
የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ከሚሰራቸዉ ዋና ዋና ተግባራት መካከል ከኪነ-ጥበብ ባለሙያዎችና በዘርፉ ውስጥ ካሉ አካላት ጋር ኪነ-ጥበብን በተለያዩ መንገዶች ማሳደግና በኪነ-ጥበብ የተገነባ ትውልድን ማፍራት ነዉ።
በዚሁ መሰረት የኢትዮጵያ ቴአትር ባለሞያዎች ማህበር ከቢሯችን፣ ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽንና ከቢ ኘላስ ጋር በመተባበር የተዘጋጀ የቴአትር እና ቴሌቪዥን ፌስቲቫል የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎችና የቴአትር ተማሪዎች በተገኙበት ለአራተኛ ጊዜ እየተካሄደ ነዉ።
ፌስቲቫሉ ቦሌ በሚገኘው ፍሬንድሺፕ ሆቴል እና ሸጎሌ ባለው አዲሱ የኢቢሲ ሚዲያ ኮምፕሌክስ ውስጥ ይካሄዳል።
በአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ (የኪነ-ጥበብ ሐብቶች ልማት፣ መድረኮችና ኩነቶች ዝግጅት ዳይሬክተር ) አቶ ሰለሞን ደኑ ቢሮው ከኢትዮጵያ ቴአትር ማህበርና ከሌሎች የኪነ-ጥበብ ባለድርሻዎች ጋር በትስስር በመስራት ኪነ-ጥበባዊ ጥናትና ዉይይቶች እየቀረቡ ለህዝብ መድረሳቸው ለዘርፉ የመረጃ ፍሰትን ያዳብራል ብለዋል።
በተጨማሪም ቢሮዉ ቀጣይ ይህን መሰል ፕሮግራም በማስተባበር እንደሚሰራ አሳዉቀዋል።
ዛሬ ጥቅምት 24 /2016 ዓ.ም የቴአትርና ቴሌቪዥን ፌስቲቫል ላይ "የአዛውንቶች ክበብ" የተሰኘዉ ተዉኔት ታሪክ አወቃቀርና አጠቃላይ ገለፃ ተደርጎል።
ከዛሬ አርባ ዓመታት በፊት በፀኃፊ ተውኔት ነጋሽ ገ/ማርያም የተደረሰዉ "የአዛውንቶች ክበብ" ቴአትር በሀገራችን አንጋፋ በሆኑት በአውላቸዉ ደጀኔ፣ ወጋየሁ ንጋቱ እና በሌሎች ዕውቅ ተዋኒያን ተተዉኗል።
"የአዛዉንቶች ክበብ" ቴአትር በኢትዮጵያ የቴአትር ታሪክ ዉስጥ ትልቅ ሚና የጣለ እንደሆነ የቴአትር ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዚደንት ቢኒያም ወርቁ አንስተዋል።
ድርሰት እና አጠቃላይ ታሪኩን የሚመለከት ጥናት በባለሙያ ቀርቦ ዉይይት ተደርጎበታል።
ቀጣይ በሚካሄደው የቴአትር ፌስቲቫል በገጣሚ ታረቀኝ በዳሳ የተደረሰዉ "የሁለት ክፍል ግብዣ" የተሰኘዉ ተውኔት ጥናትና ውይይት ሸጎሌ በሚገኘዉ በኢቲቪ አዲሱ የሚዲያ ኮምፕሌክስ ይቀርባል ነዉ የተባለዉ።
ሌሎች የቀደምት ተውኔቶች በመድረክ ድጋሜ እየቀረቡ ለህዝብ ቢቀርቡ የሚሉ ሀሳቦች ተነስተዋል።
የኢትዮጵያ ቴአትር ባለሞያዎች ማህበር ጥያቄዉን በመዉሰድ እንደሚሰራ አሳዉቋል።
የአርካይቪንግ እና ዶክመንቴሽን ስራዎች ላይ ጥንቃቄ ሊደረግባቸዉ እንደሚገባ ተነስቷል።
በተለይም ዲጂታል በሆነ መንገድ ቢቀመጡ በተፈለጉ ሰዓት መገኘት የሚችሉበት ሁኔታ ቀላል አማራጭ እንደሚሆን ኤርሚያስ ፍቅሬ/ጥናት አቅራቢ/ አንስተዋል።
የሁለቱ ተውኔቶች ጥናትና ውይይት በዋናነት የአርባኛ ዓመት መታሰቢያ ዘመናቸውን ምክንያት በማድረግ በትብብር የተዘጋጀ ሲሆን ሌሎች የተውኔት ስራዎችን ለመዘከር ያግዛል ተብሏል።
(ባ/ኪ/ቱ ቢሮ)
Read 945 times