Tuesday, 07 November 2023 00:00

የአምራች ኢንተርፕራይዞች አገር አቀፍ ኤግዚቢሽንና ባዛር ለ5 ቀናት ይካሄዳል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

የአምራች ኢንተርፕራይዞች አገር አቀፍ ኤግዚቢሽንና ባዛር ለ5 ቀናት ይካሄዳል


•  ኤግዚቢሽንና ባዛሩ ታህሳስ 3 በስካይ ላይት ሆቴል ይከፈታል


”ኢትዮጵያ ታምርት፤ እኛም እንሸምት” በሚል መሪ ቃል፣ ”የኛ ምርት” የተሰኘ የአምራች ኢንተርፕራይዞች አገር አቀፍ ኤግዚቢሽንና ባዛር፣ ከታሕሳስ 3 እስከ ታሕሳስ 7 ቀን 2016 ዓ.ም በስካይ ላይት ሆቴል እንደሚካሄድ ተገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት አመራሮችና የፕራና ኢቨንትስ ዳይሬክቲንግ ማናጀር፣ ኤግዚቢሽንና ባዛሩን አስመልክቶ ዛሬ ጠዋት ረፋዱ ላይ በስካይ ላይት ሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

”የኛ ምርት” የተሰኘው ኤግዚቢሽንና ባዛር ዋና ዓላማ፣ አምራች ኢንተርፕራይዞች በምርት ትውውቅ፣ በምርት ሽያጭ፣ በገበያ ትስስር፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በልምድና የመረጃ ልውውጥ የተሻለ አቅም መፍጠርና የዘርፉን ፋይዳ  ማሳየት የሚያስችላቸውን መድረክ መፍጠር ነው ተብሏል፡፡

በዚህ ኤግዚቢሽንና ባዛር፣ ከመላ አገሪቱ የተውጣጡ ከ100 በላይ የጨርቃጨርቅና አልባሳት ውጤት አምራቾች፣ የፕላስቲክ ውጤት አምራቾች፣ የቆዳና የቆዳ ውጤት አምራቾች፣ የአግሮ ፕሮሰሲንግ አምራቾች፣ የኬሚካል ውጤት አምራቾች፣ የማዕድንና ጌጣጌጥ ውጤት አምራቾች፣ የእንጨትና ብረታ ብረት ውጤት አምራቾችና ሌሎች ዋና ድጋፍ ሰጪ ተቋማት የሚሳተፉበት ሲሆን፤ ከ50ሺ በላይ ገዢና ጎብኚዎች ይስተናገዱበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ኤግዚቢሽንና ባዛሩ፣ ከመላው ኢትዮጵያ የተውጣጡ ውጤታማ  የአገር ውስጥ አምራች ኢንተርፕራይዞች በአንድ ጣሪያ ሥር ተሰባስበው ከመላ አገራችን ከሚመጡ የህብረተሰብ ክፍሎችና ከአጋር ተቋማት ጋር የገበያ ትስስር ለመፍጠር የሚያስችል፣ ልምድና ተሞክሮ ለመጋራት ምቹ ዕድል የሚፈጥር እንዲሆን ለማስቻል ጥረት መደረጉ የተገለጸ ሲሆን፤ በተጨማሪም፣ አምራቾች የደረሱበትን የቴክኖሎጂና የምርት የእድገት ስኬት ደረጃ፣ ልምድና ተሞክሮ የሚያካፍሉበት እንዲሁም በዘርፉ ጥናት ያደረጉ ምሁራን ጥናታዊ ጽሁፍ የሚያቀርቡበትና የፓናል ውይይት የሚካሄድበት መድረክ እንደሚሆንም ለማወቅ ተችሏል፡፡


”የኛ ምርት” ኤግዚቢሽንና ባዛር፣ ዘላቂ የንግድ ትስስርን ለመፍጠርና የምርት ዕድገትን ለማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ በጥንቃቄ የታቀደ ነው የተባለ ሲሆን፤ ለተሳታፊዎች የንግድና የምርት ስኬት የሚተጋ ከመሆኑም በላይ የአምራች ኢንተርፕራይዞች ምርቶችን ማህበረሰቡ በአገር ምርት እንዲኮራና ትኩረት ሰጥቶ እንዲሸምት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ልዩ ኹነት መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

”የኛ ምርት” የተሰኘውን አገር አቀፍ  ኤግዚቢሽንና ባዛር፣ የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት እና ፕራና ኤቨንትስ በትብብር እንደሚያዘጋጁት ታውቋል፡፡

Read 699 times