Friday, 10 November 2023 11:27

መንግስቱ ‹‹ኮበለሉ›› ወይስ ‹‹የተሳካ መፈንቅለ መንግስት›› ተካሄደባቸው?

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(1 Vote)

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ‹‹የክህደት ቁልቁለት›› በሚል ርዕስ በ1992 ዓ.ም ባሳተሙት መጽሐፍ ላይ ‹‹የማይጠራጠር ሰው እውነት ላይ አይደርስም›› የሚል ኃይለ ቃል አስፍረዋል፡፡ የሚጠራጠር ሰው በቶማስ ይገለጻል፡፡ ቶማስ የኢየሱስ ክርስቶስን ከሞት መነሳት ‹‹ሚስማር የተቸነከረበት የእጅህን መዳፍና በጦር የተወጋው ጎንህን ካላየሁ አላምንም›› የሚል ጥያቄ አቅርቦ ማረጋገጫውን ካየ በኋላ በማመኑ ይታወቃል፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ታላቁ መጽሐፍ ‹‹ሳያዩ የሚያምኑ ብጹኃን ናቸው››ም ይላል፡፡ የነገሮችን እውነታ ለመረዳት አንጻራዊ እይታ ጠቃሚና አስፈላጊም ነው፡፡ በሳይንስም አንጻራዊነት (Relative) አንዱ እውነትን መፈለጊያ ዘዴ ነው፡፡
ለ‹‹እውነት ምንድነው?›› ጥያቄም በፍልስፍና የዕውቀት ዘርፍ በአንጻራዊ ዕይታ ብዙ ትርጓሜና ምላሽ ይሰጥበታል፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ፤ አንድን ጉዳይ ‹‹አንድም እንዲህ አንድም እንዲያ›› በሚል የሚሰጠው ‹‹የአንድምታ ትርጓሜ››ም ለዚህ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ የታሪክ ፀሐፊያን ያገኙትን መረጃ እንደወረደ ከመክተብ ታቅበው እውነቱን ማጥሪያ ጊዜ እንደሚገዙ ይታወቃል፡፡ ጊዜ ተወስዶ ከስክነት በኋለ የተዘጋጁ ናቸው በሚባሉ መጻሕፍ ላይ ለሚታዩ ልዩነቶች፣ ምክንያታቸው ከአንጻራዊነት ጋር ነው የሚያያዘው፡፡ በቀይ እና ነጭ ሽብር አጀማመርና እልቂት ላይ እየቀረቡ ያሉ የተለያዩ መረጃዎች ለዚህ አንዱ ማሳያ ይሆናሉ፡፡
በተለየ ሊባል በሚችል መልኩ ከ1960ዎቹ ወዲህ ያለው የሀገራችንን የፖለቲካ ታሪክ በተመለከተ በተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተደጋጋፊና ተቃራኒ ሀሳቦች የተላለፈባቸው ጥቂት የማይባሉ መጻሕፍት ታትመው ለአንባቢያን ቀርበዋል፤ በቅርቡ ከታተሙት መሐል በኮሎኔል ዱሬሳ ዋማ ተዘጋጅቶ ‹‹እንዴት ሊሆን ቻለ? - መልሱን ከዓይን ምስክሩ›› በሚል ርዕስ በ2015 ዓ.ም የታተመው ግለ-ሕይወት ታሪክ መጽሐፍ አንዱ ነው፡፡ መጽሐፉ ብዙ አዳዲስና ሊያወያዩ የሚችሉ መረጃዎችን ያካተተ ነው፡፡
ደራሲው ምዕራብ ወለጋ ቃቄ የምትባል የገጠር መንደር በ1933 ዓ.ም ነው የተወለዱት፡፡ በልጅነታቸው የቤተ ክህነት ትምህርት ቀስመዋል፡፡ እንደብዙዎቹ የገጠር ልጆች በብዙ ችግሮች ውስጥ አልፈው፣ ወደ አዲስ አበባ ካመጧቸው ሰዎች ጋር ከአንዱ ወደሌላው ስፍራ ለ34 ቀናት ያህል 800 የሚደርስ ኪሎ ሜትር በእግር ተጉዘው ነበር አዲስ አበባ የደረሱት፡፡
 
በልጅነት ባይዋቸው የወለጋ ገጠርና ከተሞች ንግድ፣ እርሻ፣ ባህላዊና ኃማኖታዊ ስርዓቶች ምን ይመስሉ እንደነበር፤ በአካባቢው በተለይ ከንግድ ጋር በተያዘ የውጭ ሀገር ዜጎች ሚና፤ የውሃ ወፍጮው አቋቋሙት ለሕዝቡ አገልግሎት በመስጠት ታዋቂ የነበሩት ጣሊያናዊ፣ ኢትዮጵያዊ በማግባታቸው ምክንያት ‹‹አባ ክንፉ›› የተባሉት ባለወፍጮ፣ በመኖሪያ ቤታቸ ዙሪያ ሙዝ፣ ብርቱካን፣ ፖፖዬ የመሳሰሉ አትክልትና ፍራፍሬዎችን ስለማልማታቸቨው ተነስቷል፡፡
ባለታሪኩ አዲስ አበባ ከተማ በመጡበት ወቅት በተለይ ለገሀር አካባቢ ምን ገጽታና እንቅስቃሴ እንደነበረው በልጅነት አእምሮ ያዩትን ታሪክ የመጽሐፋቸው አካል አድርገውታል፡፡ በሽመልስ ሀብቴ ትምህርት ቤት ዘመናዊ ትምህርት የመቀጠል ዕድል ባገኙበት አጋጣሚ አብረዋቸው ከተማሩት እንዱ ሰመረ ርዕስም የሚባል ከኤርትራ ማንደፈራ የመጣው የቅርብ ጓደኛቸው ሆኖ ከ1 እስከ 7 ክፍል በአንድ ክፍል ተምረዋል፡፡ ሁለቱም ጎበዝ ተማሪዎች ስለነበሩ ‹‹በደብል ፕሮሞሽን›› 7ኛ ክፍል ለመድረስ 3 ዓመታት ብቻ ነበር የወሰደባቸው፡፡
የ8ኛ ክፍል ሚኒስትሪ ፈተናን ሁለቱም መቶ ፐርሰንት በማምጣት ነበር ያለፉት፡፡ ከሚኒስትሪ በኋላ ሰመረ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ግቢ ይገኝ ወደነበረው በዕደ ማርያም ትምህርት ቤት ገቡ፤ በመቀጠል ከዩኒርስቲው የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አገኙ፡፡ የደራሲው የልጅነት ጓደኛ አምባሳደር ሰመረ ርዕሶም፣ በቅርቡ በኢትዮጵያ የኤርትራ አምባሳደር ሆነው ተሹመው እንደነበር ይገልጻሉ - ደራሲው፡፡
ወጣቱ ዱሬሳ ዋማ 9ኛ ክፍል በሽመልስ ሀብቴ እየተማሩ እያለ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ጥይት ፋብሪካ ጥሩ ውጤት ያላቸው ልጆችን መልምሎ መቅጠር እንደሚፈልግ ሲያዩ ተወዳድረው ስላለፉ በዚያ ፋብሪካ ስራ ጀመሩ፡፡ በመቀጠል በቀ.ኃ.ሥ ጦር ትምህርት ቤት እጩ መኮንን ሆኖ መሰልጠን የሚያስችል ዕድል አግኘተው በ20ኛ ዕጩ መኮንንነት ጋር ስልጠና ወስደው ተመረቁ፡፡ ከዚያ ዘመን ገጠመኛቸው አንዱ የ1953 ዓ.ም የታህሳስ ግርግር ሲነሳ የሆለታ ጦር ትምህርት ቤት እጩ መኮንኖች መፈንቅለ መንግሥቱን ለማክሸፍ የራሳችንን አስተዋጽኦ ስለማድረጋቸው አንስተዋል፡፡
በም/ጦር መሐንዲስ መምሪያ ብዙ ጊዜ አገልግለዋል፡፡ አሜሪካዊያን የኢትዮጵያን ሚሊተሪ ለመደገፍ የሚያስችል MAAG /Military Assistance Advisory Group/ ፕሮግራም ሲነደፍ ስልጠና ካገኙት አንዱ ነበሩ፡፡ በ1955 ዓ.ም ወደ ኮንጎ የዘመተው የ4ኛው የጠቅል ብርጌድ ዐባል ሆነው አገልግለዋል፡፡ የ1969 ሶማሊያ ወረራን በቅርብ ሆነው አይተዋል፡፡ ለተጨማሪ ትምህርት ወደ አሜሪካ የሄዱበት ታሪክ አለ፡፡ በአሰልጣኝነት ወደ የመን ሄደው ያገለገሉበት ጊዜ ነበር፡፡ በመሐንዲስ መምሪያ እያሉ በሀገሪቱ የተለያዩ ቦታዎች በሙያቸው (ፈንጂ በማጥመድና ማምከን) በስፋት አገልግለዋል፡፡ በኢትዮጵያ አየር መንገድ በሚገኝ በረራ ደህንነት መስሪያ ቤት (Anti Hijack) ተመድበው ሰርተዋል፡፡ ከትምህርትና ስራ ጋር በተያያዘ ወደ 24 የሚደርሱ አገራት የመጓዝ ዕድል አግኝተዋል፡፡

በሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ከ1973 እስከ 1983 ዓ.ም ድረስ አስቸኳይ ጉዳዮች ማጣሪያና የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገራት ባለስልጣኖች ጥበቃ ዋና መምሪያ ውስጥ ባገለገሉበት አጋጣሚ በርካታ ታሪኮች ውስጥ አልፈዋል፡፡ ግንቦት 13 ቀን 1983 ዓ.ም ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም ሀገር ጥለው የወጡበት ክስተት ‹‹የተሳካ መፈንቅለ መንግስት›› ነው የሚልና መሰል አስደማሚ መረጃዎችን በመጽሐፋቸው ያስነብባሉ፡፡
 
ከፕሬዚዳንት መንግስቱ ኃይለማርያም ‹‹ኩብለላ›› ጋር በተያያዘ ስሙ በተደጋጋሚ የሚነሳው የብለቴን አካባቢ 1970ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ የኮሎኔል መንግስቱን ትኩረት የሳበ ስፍራ እንደ ነበር ሲናገሩ ‹‹ብላቴን እርሻ ልማት ለመጎብኘት ርዕስ ብሔሩ ኮ/ል መንግሥቱ ኃ/ማርያም ወደዚያ አዝወትረው ይጓዙ ነበር … አሁን ዶ/ር ዐብይ ተግባራዊ እያደረገው ያለው ‹የበጋ ሰንዴ ልማት›፤ የፕሬዚዳንት መንግስቱ ኃይለማርያም ዕቅድ ነበር፡፡ ሶማሌ ክልል ኦጋዴን ጎዴ በዋቢ ሸበሌ ወንዝ ላይ ግድብ ተሰርቶ ሀገር ከመመገብ በተጨማሪ ወደ ውጭ ለመላክ የሚያስችል የመስኖ እርሻ ስራ ተግባራዊ ማድረግ ጀምሮ ነበር፡፡ በአካባቢው በዘላንነት የሚታወቁ የማህበረሰብ ክፍሎችን በአንድ ስፍራ እንዲሰፍሩ በማድረግ አርሶ መኖርን እንዲለማመድ ሁሉ አድርጐ ነበር፡፡

‹‹ዋቢ ሸበሌ ወንዝ ላይ ከጎዴ በስተሰሜን ምዕራብ ከፍ ብሎ በሚገኝ ቦታ ላይ ለግድብ ሥራ አመቺ የሆነ ቦታ ድረስ ሄዶ በባለሙያ ገለጻ ተደርጎለት መላ ኢትዮጵያን ለመመገብ የሚችል ስንዴ ሊመረትበት እንደሚችል ትልቅ ተስፋ ተጥሎ ነበር፡፡››
በቅርቡ ከ‹‹ብሪክስ›› የሀገራት ጥምረት ጋር በተያያዘ የተነገረውን ጨምሮ፣ ከዶላርን ተጽእኖ አሳዳሪነት ለመላቀቅ የተለያዩ ሀገራት በተለያዩ ጊዜ የተለያየ ጥረት አድርገዋል፡፡ የኮሎኔል ዱሬሳ ዋማ መጽሐፍ በዚህ ዙሪያ የሊቢያው መሪ መሐመድ ጋዳፊ ስላደገሩት ጥረትና ምኞታቸው አልሳካ ሲላቸው ስለፈጠሩት ስህተት አስገራሚ ታሪክ አቅርቧል፡፡ በ19ኛው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መድረክ ላይ፣ አፍሪካውያን የራሳቸውን መገበያያ ገንዘብ በጋራ አሳትመው መንቀሳቀስ ከቻሉ ‹‹አፍሪካ ከእጅ ጥምዘዛ ነፃ ትወጣለች›› የሚለው ሀሳባቸው ለጊዜው ተቀባይነት ባለማግኘቱ የተናደዱት መሐመድ ጋዳፊ፣ በደርግ ዘመን በአዲስ አበባ ከተማ የግብፁን መሪ በመኪና ላይ በተጠመደ ፈንጅ ለመግደል ያደረጉት ጥረትና ውጡቱ ምን ይመስል እንደነበር በዝርዝር ያቀረበ መጽሐፍ ነው፡፡
 
የሊቢያው መሪ ፕሬዚዳንት ሙሐመድ ጋዳፊ፤ አሁን የአድዋ ዜሮ ዜሮ ሙዚየም እየተሠራበት ያለው ሰፊ ሜዳ ላይ፣ በአፍሪካ ትልቅና አንደኛ ሊባል የሚችል መስጊድ የመገንባት ምኞት አለኝ ብለው፤ ለመሬቱ 3 ቢሊዮን ዶላር ለመክፈልም ፈቃደኛ መሆናቸውን ገልፀው፤ ይህንንም ምኞታቸውን ለኮ/ል መንግሥቱ ኃይለማርያም ሲያቀርቡላቸው፣ መንግሥቱ ኃይለማርያም ማንንም ሳያማክሩ ‹‹የማይሆን ሀሳብ መሆኑን›› አሳውቀው እምቢ እንዳሏቸውም ተነስቷል፡፡
ግንቦት 8 ቀን 1981 ዓ.ም በኮሎኔል መንግስቱ ኃያለማርያም ላይ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ የተደረገ ዕለት፤ እቅዱ መክሸፍ በጀመረበት ቅጽበት ጀኔራል አበራ አበበ የመከላከያ ሚኒስትሩን በያዘው ማካሮቭ ሽጉጥ ደረታቸው ላይ ሦስት ጊዜ አከታትሎ ተኩሶ ከጣላቸው በኋላ በፓፓሲኖስ ሕንፃ መሐል ያለውን የግንብ አጥር ዘሎ ከግቢው ስለመውጣቱ፣ ሚኒስትሩም ሆስፒታል ከደረሱ በኋላ ሕይወታቸው ስለማለፉ የመጀመሪያ ደረጃ ምስክርነት የቀረበበት መጽሐፍ ነው፡፡

ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም በተለያዩ ስፍራዎች የጥይት፣ የሽጉጥ፣ የክላሽ፣ የመትረየስና የከባድ ጦር መሣሪያ ጥይቶች ማምረቻ ማቋቋም ጀምረው ነበር የሚሉት ኮሎኔል ዱሬሳ ዋማ፤ በተለይ በአምቦ መስመር የሚገኘው የከባድ መሣሪያ ጥይት ማምረቻ ፋብሪካ በተመረቀ በሳምንቱ፤ በኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም ላይ የግንቦት 8 ቀን 1981 ዓ.ም መፈንቅለ መንግስት እንደተካሄደ ያነሳሉ፡፡ የግንቦት 13 ክስተትም ‹‹ኩብለላ›› ሳይሆን የውጭ ኃይሎች ደባ ጋር በተያያዘ የተፈጸመ ‹‹የተሳካ መፈንቅለ መንግሥት›› ነው የሚሉት ከዚህ በመነሳት ነው፡፡
የደርግ መንግስትን ለመጣል የሰሜን ኢትዮጵያ ተቃዋሚ ኃይሎች ካደረጉት ትግል በተለይ የኢሕአዴግ (ወያኔ) እንቅስቃሴ ምን ይመስል እንደነበር በመጽሐፉ ከቀረቡ መረጃዎች መሐል ታላላቅ የኃይማኖት አባቶች ሰይቀሩ በስለላ ስራ ላይ ተሰማርተው እንደነበር ማሳያ ሆኖ የቀረበ መረጃ አለ፡፡ በቀጣይነት ብሔር፣ ዘርና ቋንቋ ተኮር እንዲሆን የተፈለገው የፖለቲካ ስርዓት፤ ከሀገር ውስጥ አልፎ በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በብሔራቸው ቤተ ክርስቲያን ማቋቋም የጀመሩት በዚያ ምክንያት እንደነበር አስደማሚ መረጃ ቀርቧል - በመጽሐፉ፡፡  
የደርግ መንግስት ከወደቀ በኋላ የደህንነት ቢሮ ኃላፊነትን ኮሎኔል ተስፋዬ ወልደስላሴን ተክተው መምራት የጀመሩት አቶ ክንፈ ገብረመድህን ‹‹ዋኝተን ከማንወጣበት ባሕር ነው የተጣልነው›› ስለማለታቸው፤ ኢሕአዴግ አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ በኋላ ‹‹ደርግን ጥለናል ወደትግራይ እንመለስ›› በሚሉና ‹‹የደርግ መውደቅ ብቻ ዋስታና አይሆንም›› የሚሉ ሁለት ወገኖች ስለመፈጠራቸው፤ በዚህም ምክንያት የ‹‹ታላቋ ትግራይ›› እቅድ ስለመነደፉ፤ በዚህም እቅድ ትግራይ ከምዕራብ እስከ ደቡብ ኢትዮጵያ የሚዘረጋ ድንበር እንዲኖራት ስለመታሰቡ፤ አሜሪካኖች ያጠኑት (US ARMY ENGINEERS MAPING MISSION) የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ይህንን ታሳቢ አድርጎ እንዲገነባ፣ በ1984 ዓ.ም ተመክሮበት ውሳኔ ስለመሰጠቱ፤ በዚህ ምክክርና ውይይት ውሰጥ  የአቶ ንዋይ ገብረአብ ሚና ታላቅ እንደነበር በደራሲው አንደኛ ደረጃ ምስክር ሰጪነት መረጃዎቹ ተዘርግፈዋል፡፡ እነዚህ መረጃዎች ሀገራችንንን በተመለከተ  ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም እንዳሉት እውነት ላይ የምንደርስበት ጊዜ እንዳልተቃረበ የሚያመለክቱ ይመስላል፡፡



Read 3213 times