Wednesday, 22 November 2023 20:14

ከስደት ተመላሾችና መኪና አስመጪዎች፣ መንግሥት ከማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እንዲታደጋቸው ተማጸኑ

Written by  (ልዩ ሪፖርታዥ)
Rate this item
(1 Vote)

•  ጉምሩክ 237 ተሽከርካሪዎችን በሃራጅ ለመሸጥ የጀመረውን እንቅስቀሴ መንግሥት  እንዲያስቆምላቸው ጠይቀዋል

•  ገንዘብ ሚኒስቴር በጉዳዩ ላይ ለሚኒስትሮች ም/ቤት ያቀረበው  የውሳኔ ሃሳብ ተጥሷል ብለዋል

•  ቅሬታ አቅራቢዎቹ  አቤቱታቸውን በተደጋጋሚ ለመንግሥት አካላት  ማቅረባቸውን ተናግረዋል
 
 ከስደት ተመላሾችና  ያገለገሉ ተሽከርካሪ አስመጪዎች፣ ጉምሩክ፣ የመንግሥት  ውሳኔን በመጣስ፣ ከውጭ  ያስገቧቸውን  237  ተሽከርካሪዎች በሃራጅ ለመሸጥ በእንቅስቃሴ  ላይ  መሆኑን በመጥቀስ፣ መንግስት ንብረታቸውን በማጣት ከሚደርስባቸው ከፍተኛ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እንዲታደጋቸው ተማጽነዋል፡፡

ከአቤቱታ  አቅራቢዎቹ መካከል አሥሩ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች አስመጪ ሲሆኑ፤ የተቀሩት በአረብ አገራት ለረዥም ዓመታት በስደት ኖረው ወደ ሃገር ቤት የተመለሱ ናቸው ተብሏል፡፡

የተሽከርካሪ ባለቤቶቹ  መኪኖቹን የገዙት  አዲሱ የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ ከመጽደቁ በፊት ቢሆንም፣ በዓለማቀፍ ደረጃ በተከሰተው የኮቪድ ወረርሽኝ ሳቢያ ተሽከርካሪዎቹን ወደ አገር ውስጥ ማስገባት አለመቻላቸውን ይናገራሉ፡፡
 
ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች በነባሩ ምጣኔ  ታክስ  እንዲገቡ የሚፈቅደው የኤክሳይዝ አዋጅ  የጊዜ ገደብ ከተጠናቀቀ በኋላ ቁጥራቸው ወደ 297 የሚሆኑ ያገለገሉ  ተሽከርካሪዎች ወደ አገር ቤት እንዲገቡ መንግሥት ፍቃድ መስጠቱ የሚታወስ ነው።
   
ይህን የመንግሥት  ውሳኔ  በመጣስ  ከውጭ ያስገባናቸውን ተሽከርካሪዎች ጉምሩክ በሃራጅ ለመሸጥ እንቅስቃሴ ጀምሯል ያሉት  ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ ለዘመናት ለፍተን ባጠራቀምነው ጥሪት የገዛናቸውን ተሽከርካሪዎች አጥተን ለከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ  መዳረጋችን እኛን ብቻ ሳይሆን አገርንም የሚጎዳ በመሆኑ መንግሥት ጣልቃ ገብቶ መፍትሄ ይስጠን ብለዋል፡፡

አቤቱታቸውን በተደጋጋሚ ለመንግሥት አካላት ማቅረባቸውን የሚናገሩት ከስደት ተመላሾቹና ተሽከርካሪ አስመጪዎቹ፤ የኢፌዲሪ ጉምሩክ ኮሚሽን ተሽከርካሪዎቹን በሽያጭ የማስወገድ ሂደቱ እንዲዘገይ በታህሳስ 2015  ለአዳማ  ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት  ትዕዛዝ መስጠቱን አስታውሰው፤ ሆኖም  ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ትዕዛዙን በመጣስ፣ ከውጭ ያስገባናቸውን 237 ተሽከርካሪዎች በሃራጅ ለመሸጥ እንቅስቃሴ ጀምሯል ሲሉ ቅሬታቸውን አቅርበዋል፡፡

ከውጭ ተገዝተው ከገቡት 297 ተሽከርካሪዎች ውስጥ በጉምሩክ ውሳኔ  37 ተሽከርካሪዎች ለመንግስት መ/ቤቶች አገልግሎት እንዲውሉ መደረጋቸውን የሚናገሩት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ 23 ተሽከርካሪዎች በሽያጭ እንዲወገዱ መደረጋቸውንና  ቀሪዎቹ 237 ተሽከርካሪዎች ደግሞ በሃራጅ ሊሸጡ በሂደት ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

የእነዚህ ተሽከርካሪዎች ባለቤቶች ከጊዜ ገደቡ በፊት ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ያልቻሉት በአለማቀፍ ደረጃ በተከሰተው የኮቪድ  ወረርሽኝ ሳቢያ የወደብ እንቅስቃሴ በመስተጓጎሉ መሆኑን በመግለጽ፣ ተሽከርካሪዎቹን የገዙት ለዘመናት ያጠራቀሙትን ጥሪት በመጠቀም በመሆኑ፣ ንብረታቸውን ማጣታቸው ለከፍተኛ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ስለሚዳርጋቸው፣ መንግሥት ይህንን ችግራቸውን በመረዳት መፍትሄ እንዲሰጣቸው በተደጋጋሚ መጠየቃቸውን  ይናገራሉ፡፡

 የተሽከርካሪ ባለቤቶቹ ለመንግስት ተደጋጋሚ አቤቱታ ማቅረባቸውን የሚጠቁመው  በገንዘብ ሚኒስቴር የተጻፈውና ለሚኒስትሮች ም/ቤት የቀረበው የውሳኔ ሃሳብ፤ አስመጪዎቹ ከጊዜ ገደቡ በኋላ ወደ አገር ቤት በገቡት ተሽከርካሪዎች ላይ በአዲሱ የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ የተጣለውን ቀረጥና ታክስ ባለመክፈላቸው፣ ተሽከርካሪዎች እንደተተው ተቆጥረው መሸጣቸው በአስመጪዎቹ ላይ የሚያስከትለውን  ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ከግምት ውስጥ በማስገባት ባለ 3 ነጥብ የውሳኔ ሃሳብ አቅርቧል፡፡

በዚህም መሠረት፣ በጉምሩክ ኮሚሽን እጅ በሚገኙት 237 ተሽከርካሪዎች ላይ አስመጪዎቹ በቀድሞው  የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅና በሌሎችም ህጎች  መሠረት፣ ሊከፈል የሚገባውን ቀረጥና ታክስ ከፍለው ተሽከርካሪዎቹን እንዲረከቡ የውሳኔ ሃሳቡ መጠቆሙን ቅሬታ አቅራቢዎቹ ይናገራሉ፡፡

 የውሳኔ ሃሳቡ በተጨማሪም፣ በሐራጅ ከተሸጡት 23 ተሽከርካሪዎች ከተገኘው ብር 23,603,866,94 ውስጥ በቀድሞው ኤክሳይዝ ታክስ አዋጅና ሌሎች ህጎች መሠረት ሊከፈል የሚገባው ቀረጥና ታክስ ተቀንሶ ቀሪው ሂሳብ ለአስመጪዎቹ እንዲመለስላቸው ይጠቁማል፡፡

ለመንግስት መስሪያ ቤቶች የተከፋፈሉትን  37 ተሽከርካሪዎች በሚመለከትም  የቀረጥና ታክስ ማስከፈያ ዋጋቸው ተቀንሶ ብር 21,902,845,88  ለአስመጪዎቹ እንዲከፈላቸው የገንዘብ ሚኒስቴር በውሳኔ ሃሳቡ አመልክቷል፡፡  

ይህም ሁሉ ሆኖ ግን ጉምሩክ ከውጭ ገዝተን ያስመጣናቸውን  237 ተሽከርካሪዎች የገንዘብ ሚኒስቴርን የውሳኔ ሃሳብ በመጣስ በሃራጅ ለመሸጥ በሂደት ላይ ይገኛል ያሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ መንግሥት ጣልቃ በመግባት ከከፍተኛ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እንዲታደጋቸው ተማጽነዋል፡፡

Read 1432 times