Saturday, 02 December 2023 19:45

በጠብ ጊዜ አሥር እንጀራ ለሁለት አይበቃም

Written by 
Rate this item
(9 votes)

 ካህሊል ጂብራን “መልዐኩ” በተሰኘው ምሳሌያዊ ጽሑፉ ስለ መልዐክና ስለ አንድ ሽፍታ እንዲህ ይተርካል፡፡
አንድ ጊዜ በልጅነቴ ከተራሮቹ ማዶ ባለው ጫካ ከአንድ ዛፍ ስር የሚኖረውን መልዐክ ልጠይቀው ሄጄ ነበር፡፡ ስለ ሰናይ ምግባር ጠቃሚነት እየተወያየን ሳለን በዚያ አካባቢ የታወቅ ሽፍታ እንደሚያነክስ ሁሉ ሸንክል ሸንክል እያለ ቀጭኗን የእግር መንገድ ይዞ ሽቅብ እኛ ወዳለንበት መጣ፡፡
ዛፉ አጠገብ ሲደርስ ከመልዐኩ ፊት ተንበረከከና፡፡
“መልዐክ ሆይ! ኃጢአቴ እጅግ ከብዶኛልና እባክህ ልናዘዝ፡፡ ሰላምና ምቾትን ላገኘ የምችለው ለአንተ ኃጢአቴን ከተናዘዝኩልህ ብቻ ነው!” አለው፡፡
መልዐኩም፤ “ወዳጄ ሆይ የእኔ ኃጢትምኮ እንዳንተው ኃጢአት እጅግ ከብዶኛል” አለው፡፡
ሽፍታ፡- “እኔኮ ሌባና ቀማኛ ነኝ”፡፡
መልዐክ፡- “እኔም ሌባ ቀማኛ ነኝ”
ሽፍታ፡- “መልዐክ ሆይ፤ እኔ ነብሰ-ገዳይ ነኝ፡፡ የብዙ ንጹሀን ሰዎች ደም በጆሮዬ ይጮሃል” አለው፡፡
መልዐክ፡- “እኔ ራሴም ነብሰ - ገዳይ ነኝ፡፡ የብዙ ንፁሀን ሰዎች ደም በጆሮዬ ይጮሃል፡፡”
ሽፍታ፡- “ግን እኮ መልዐከ ሆይ፤ እኔ ቁጥር ስፍር የሌላቸው ወንጀሎችን ፈጽሜአለሁ”
መልዐኩም መለሰ፡- “እኔም ስፍር ቁጥር የሌላቸው ወንጀሎችን ፈጽሜአለሁ፡፡
ከዚህ በኋላ ያ ሽፍታ ብድግ አለና መልዐኩን ትኩር ብሎ ያየው ጀመር፡፡ በዐይኖቹ ውስጥ እንግዳ ሁኔታ ይታያል፡፡ ተሰናብቶን ሄደ፡፡ አካሄዱ ፈጣን፣ ደስተኛና ዓለም የቀለለው ሰው ዓይነት ነበር፡፡
ወደ መልዐኩ ዘወር ብሎ፣
“መልዐክ ሆይ ያልፈፀምከውን ወንጀል ፈጽሜአለከሁ ብለህ ስለምን ራስህን ትወነጅላለህ? ይሄ ሰው ከእንግዲህ በጭራሽ ባንተ እንደማያምን አይታይህም?”
መልዐኩም ሲመልስ እንዲህ አለ፡-
“እውነት ነው ወዳጄ፡፡ ያ ሽፍታ ከእንግዲህ በእኔ አያምንም፡፡ ግን እንደዚያ ቅስሙ ተሰብሮ አቀርቅሮ እያነከሰ መጥቶ የነበረ ሰውዬ፣ ቀና ብሎ ሰላምና ምቾት እየተሰማው መሄዱን አላየህም? አየህ ዋናው ነገር ከእንግዲህ በእኔ አለማመኑ ሳይሆን ዛሬ ደስ ብሎ ተመችቶት መሄዱ ነው!”
በዚህ ጊዜ ሽፍታው ከሩቅ ካለው የሸለቆ መኖሪያው ውስጥ ሆኖ ሲዘፍንና ሲያፏጭ ተሰማ፡፡ የድምፁም ገደል-ማሚቶ ሸለቆውን በደስታ ሞላው፡፡
***
አገሩ በደስታ እንዲሞላ የድምፁ ገደል - ማሚቶ ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ የሚሞላ ሰው ለመፍጠር ይቻል ዘንድ፣ “በእኔ አመነም አላመነም ቀና ብሎ ይሂድ፣ እሱም ይመቸው” የሚል አስተዋይ መሪ፣ ፓርቲ፣ ድርጅት ፣ ወይም ማኅበር ማግኘት እንዴት ያለ መታደል ነበር? ከቶውንም ያጠፉትን አጥፍቻለሁ፣ የማያውቁትን አላውቅም ብሎ በግልጽ እቅጩን ተናግሮ መናዘዝ፣ ሲልም ንሥሀ መግባት ቢጨመርማ፣ የመፍትሄውን ግማሽ መንገድ መዝለቅ ነበር ፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ በአብዛኛው ያጣነው ይሄንን በግልጽ ችግርን የማስረዳት ባህል ነው፡፡ ለምሳሌ ደሞዝ ጨምሩልኝ ለማለት አዳም የዛፍ ፍሬ ስለመብላቱ፣ አብሃርም በድንኳን ስለመኖሩ፣ የኢዮብ ትዕግስት አስፈላጊ ስለመሆኑ፣ በላብህ ወዝ ጥረህ ግረህ ብላ ስለሚለው ትዕዛዝ ሁሉ ዘብዘቦ ሲያበቃ፣ የደሞዝን ታሪካዊ አመጣ በመተረክ በረዥሙ አውርቶ ያታክትና በመጨረሻ፣ “በአጭሩ ለማለት የፈለግሁት የሰው ልጅ ደሞዝ ቢጨመርለት ጥሩ ነው” ዓይነት የደሞዝ ጥያቄ ማቅረብ፡፡ ዱሮ በአንድ ቴያትር ላይ “ሶሻሊዝም ስብሰባ ያበዛል፡፡ ካፒታዝም ጭቆናና ብዝበዛ ያበዛል፡፡ ለማንኛውም ኢትዮጵያ ትቅደም፡፡ ወርቁ ቢጠፋ ሚዛኑ አይጥፋ፡፡” ሲባል ነበር፡፡ ዛሬም ዘመኑ የስብሰባ ሆኗል እንደ ኅብረ ትርዒት የሚጠብቀው ሰውም አለ፡፡ በመሰረቱ ሀሳብን በግልጽ ማስቀመጥ አስቀድሞ ሀሳብን በራስ ውስጥ ማደራጀትን ይጠይቃል፡፡ ያ ደግሞ ንባብን የአካባቢ ግንዛቤን፣ አእምሮን ክፍት ማድረግን፣ ለመማር ዝግጁ መሆንን፣ ለማየት፣ ለመስማት፣ለመቅመስ ደግ መሆንን ይጠይቃል፡፡ ሁለት ተሟጋቾች ልቡናቸው ዘግተው፣ ለመነጋገርና ለመለወጥ ዝግጁ ሳይሆኑ “የኔን አቋም ካልተቀበለ ገደል ይግባ!” የሚል ቅድመ ውሳኔ ደንግገው ሲያበቁ እንወያይ ቢሉ የሁለቱም በር ተዘግቷልና ከንቱ ልፊያ ነው የሚሆነው፡፡ እርግጥ ነው እንዳለ መታደል ሆኖ የሚነገረውን የማይሰማ፣ በውሃ ወቀጣ አይነት ድግግሞሽ የሚነተርክ ልፋ ያለው ተናጋሪም ያጋጥማል፡፡ ዶክተርም ፕሮፌሰርም ቢሆን፣ “እወቅ ያለው ባርባ ቀኑ፣ አትወቅ ያለው ባርባ ዘመኑ” እንዲሉ፣ እንዴ የከረቸመበትን አእምሮ በግድ እንክፈተው ቢባል አጉል ድካም ነው፡፡ አንዳንዱ ተወያይ የጀመረበት ርእስ እስኪጠፋው ድረስ ሲዘበዝብ ውሎ፣መማር! ይሰኛል፡፡ “ሳያስቡ የጀመሩት ቀረርቶ ለመመለስ ያስቸግራል” እንደሚባለው ተረት መሆኑ ነው፡፡በሀገራችን በየዘመኑ የታዩ የፖለቲካ ድርጅቶች፤ ማህበራትና ታዋቂ ግለሰቦች በመጨረሻ ወድቀው ተንኮታኩተው የፀፀትና የንስሀ ዘመን እስኪደርሱ ድረስ በአንድ ዓይነት የትግል ሀዲድ ላይ ሲጓዙ መታየታቸው እጅግ አስደናቂና አሳዛኝ ነው- ትራጆ ኮሜዲ!፡፡ የአብዛኞቹ ጉዞ “ከማይረባ ጓደኛ የረባ ባለጋራ ይሻላል” የሚለውን ተረት ያላገናዘበ ነው፡፡ አንዳንዶቹ በሌላው መቃብር ላይ አብበናል ለምልመናል ሲሉ ቆይተው የባሰ ጥፋት የባሰ መከፋፈል፣ የባሰ መጠፋፋት ላይ የሚገኙ ይሆናሉ፡፡ መሪ ተዋናዩም ባላንጣውም፣ አስተኔ - ባህርያቱም በጅምላ የሚሞቱበት እጅግ የአሳዛኝ ትራጀዲ ቴያትር ይመስላል፡፡
ቃል የገቡት ሳይፈፀም የተመኙት እግቡ ቀርቶ እውገቡ ሳይደርስ ተሸመድምደው ጭራሽ እነሱንም ሀገርንም ህዝብንም የከፋ መቀመቅ ውስጥ ለሚከት ውድቀት ይዳርጋል፡፡ “ሞት የሌለበት አገር እሄዳሁ ብሎ ሬሳ ቆጥ ላይ የሚያስቀምጡበት አገር ደረሰ” የሚባልበት ሁኔታ ነው፡፡ እርስ በርስ በእውቅሁሽ ናቅሁሽ መተቻቸት፣ መሸራደድ መናናቅና መጠላለፍ ሥረ-ቢስ አካሄድ ነው፡፡ ማንንም በሁለት እግር ለመቆም አያበቃምና አንድም “ድፍርስ ብጥብጥን ትሰድባለች” እንዲሉ፣ አንዱ ካንዱ ላይሻል ነገር ሲያንጓጥጥና ሲያሽሟጥጥ ቢውልም እያደር መኮስመንን ቢያሳይ እንጂ አንዳችም የጥንካሬ ምልክት አይሆንም፡፡
ጠላትን የማይመጥንና የማይረታ ሙግትና ጩኸት ከንቱ ጉልበት መጨረስ ነው፡፡ ወደ ኋላ ሰብሰብ ብሎ አቅም ገዝቶ ጎልብቶ ወደፊት ለመራመድ መጣር ይሻላል እንጂ በትንሽ በትልቁ ጉዳይ፣ ባልተደራጀ ብቃት፣ እግር በጣለና ቃል እንዳመጣ መናገር እንኳን ወንዝ አስፋልት አያሻግርም፡፡ “ሞኝ ውሻ ነጎድጓድ ላይ ይጮሃል” እንዲል መጽሀፍ፣ ሲበዛ ለውድቀት የሚዳርግ ሲያንስ ደግሞ መሳቂያ የሚያደርግ ተግባር ነው፡፡
ልዩነቶች ምንጊዜም ይኖራሉ፡፡ በመሪና፤ በተመሪ በመንግስትና በተቃዋሚዎች ወዘተ መካከል መጠኑ ይለያይ እንጂ ምን ጊዜም ልዩነት ይኖራል፡፡ በተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች መካከልም ልዩነት ይኖራል፡፡ ሆኖም መቻቻል መኖር አለበት፡፡ በአንድ የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ ባሉ አባላትም መካከል መቻቻልና መግባባት መኖር አለበት፡፡ በምሁራን መካከል መቻቻል መኖር አለበት፡፡ ማሰብና መተሳሰብ መኖር አለበት፡፡ በጠላትነት ተፈራርጆ፣ ጆሮን ከፍቶ ልብን ዘግቶ፣ ባንድ መታደግ ምንም ፍሬ አያፈራም፡፡ “ከተስማሙ አንድ እንጀራ ለዘጠኝ ባልንጀሮች እንደሚበቃ” ሁሉ “በጠብ ጊዜ አስር እንጀራ ለሁለት አይበቃም” የሚለውን ልብ ማለት ያለብን ሰዓት አሁን ነው፡፡ ባልታዛር ግራሺያን የተባለው ፀሐፊ “ሞኝ ከጓደኞቹ ከሚማረው ይልቅ ብልህ ከጠላቶቹ የሚማረው ይበልጣል” ያለውንም አለመርሳት ነው፡፡



Read 1457 times