Tuesday, 12 December 2023 20:25

ምንጊዜም አዲስ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

      ማድረስ ሲባል አንድ ትእዛዝን በፌስታል አሽጎ ለደንበኛ ወርውሮ መምጣት ማለት አይደለም። በየጊዜው በየትእዛዙ ደንበኛዎን ማስገረም፣ ማስደነቅ እና ማስደሰት ማለት እንጂ።ትናንት ትእዛዝን በተቀበሉ ጊዜ የደረሱበትን መንገድ እና የሙያ ፍቅር ዛሬ ደግሞ ያሻሽሉት። ማሻሻልዎ የይዘትም የቅርጽም ይሁን። ደንበኛዎ ከሚገምትዎ ላቅ ብለው ይገኙ። ያን ጊዜ በደንበኛዎ ላይ አግራሞትን ይችራሉ። ደግሞ ነገ ከጠበቀው በላይ ሆነው ይገኙለት። ይህን ባደረጉ ቁጥር ደንበኛዎ በእርስዎ ላይ መተማመኑ ከፍ ያለ ይሆናል። ከዚህም ሲያልፍ እርስዎም በሙያዎ እና ብቃትዎ መታመንዎ እና የማይሸረሸር ስም መገንባትዎ እየጨመረ ይሄዳል። ታዲያ የዚህ ሁሉ ድምር ውጤት እርስዎ በበጎ የሚነሳ መለያ ጠባይን ከዕለት ዕለት እያዳበሩ መሄድዎ ነው። ይህ ወደ ስኬት የሚያደርስዎ ተግባራዊ የስኬት መንገድ ነው።ኃይሌ ገብረ ስላሴ በኦሎምፒክ ሊሳተፍ በቦሌ አየር ማረፊያ በኩል ስንሸኘው ይዞት የወጣው ልብስ ብቻ ይዞ የሚመለስ እንዳልሆነ እምነትን እንድናሳድር አድርጎናል። ኃይሌ ሲመለስ ወርቅ፣ ከወርቅ የላቀ የሪኮርድ ክብር፣ ብሎም ዛሬ ብዙኃኑን ማስተዳደር የቻለ ሀብት ይዞ ይመጣል። ማረስ ማለት ይህ ነው። ሁሉን በሰዓቱ፣ ግን በፍጥነት እና በጥራት።


አራትቅንጅትበመስተንግዶ ኢንዱስትሪ ውስጥ ነጠላ አገልግሎት ወይም የአገልግሎት ምንጭ የለም። አንድ ሆቴልን እንውሰድ ለምሳሌ። ደንበኛው አንድ አገልግሎትን ብቻ ፈልጎ መጣ እንበል። ያገኘው አንድ አገልግሎት ይሁን እንጂ ያአገልግሎት በተቀናጀ መንገድ የተገኘ እንጂ አንድ ግለሰብ ወይም አንድ ክፍል ብቻውን የሰጠው ሊሆን አይችልም።
ምግብ ተመግቦ የሄደ ደንበኛ፤ የጽዳት፣የጥበቃ፣ የኪችን፣ የመስተንግዶ፣ የሒሳብ አገልግሎት እና ሌሎችንም ክፍሎች ቅንጅት የሚጠይቅ አገልግሎት ነው ያገኘው። ምግብ ስለተመገበ ብቻ የአብሳይ አገልግሎት ብቻ አግኝቶ ሄደ ልንል አንችልም።
ስለዚህ እርስዎ ሊለዩ ወይም ሊታወቁ ከሚገቡባቸው ጠባያት አንዱ የተቀናጀ ሥርዓት መከተል ነው። ቅንጅቱ ከግለሰብ ግለሰብ፣ ከግለሰብ ክፍል፣ ከክፍል ክፍል፣ ከክፍል ግለሰብ መሆን አለበት።በቀዳሚዎቹ ክፍሎች እንዳየነው ኃላፊነትን መወጣት የሁሉም ድርሻ ነው። ኃላፊነትን መወጣት ታማኝነትን ለማግኘት የሚረዳ ጠባይ ነው። ስለዚህም አንድ ግለሰብ ወይም ክፍል ኃላፊነትን ወሰደ ማለት ሽልማቱንም ወቀሳውንም ይወስዳል ማለት ነው። ይህ እንዲሆን ደግሞ ግለሰቦች እና ክፍሎች ተናበው ተቀናጅተው መሥራት
ይገባቸዋል። በምግብ ደስተኛ የሆነ ደንበኛ በመኝታም ደስተኛ እንዲሆን የክፍሎች የተቀናጀ አግልግሎት ያስፈልጋል። ይህንን ጠባይ ገንዘብዎ እንዲደርጉ የሚያስችሉ ስልቶች የሚከተሉት ናቸው።


ኃላፊነትን መውሰድ የተቀናጀ አገልግሎትን ለማቅረብ ኃላፊነትን መውሰድ የመጀመሪያው ስልት ነው። እርስዎ የራስዎን ክፍል ኃላፊነት ከወሰዱ ሌላውም ሰው የራሱን ክፍል ኃላፊነት ለመውሰድ አይሰስትም።ስለዚህ ኃላፊነትን ይወሰዱ፤ እንደ ግለሰብ ወይም እንደ ክፍል ኃላፊነትን ሲወስዱ ሌሎችም በየደረጃቸው ኃላፊነታቸውን ይወስዳሉ።ሀቀኝነት አንድ የተቀናጀ ስራ እንዲቀጥል ወይም እንዳይቀጥል ወሳኙ ቁም ነገር የሚመነጨው ጉዳዩ ከሚመራበት የሀቀኝነት ልክ ላይ ነው። ሀቀኝነት በሌለበት የተቀናጀ እና የተሰናሰለ
አሰራር ሊኖር አይችልም። “የማይተማመን ባልንጀራ በየወንዙ ይማማላል” የሚለው አባባል ለዚህ አስረጅ መሆን ይችላል።በሀቀኝነት ላይ የተመሠረተ የተቀናጀ አሠራር በየዕለቱ እያደገ የሚመጣ ነው። በየዕለቱም ወደ ስኬት እየተለወጠ የሚሄድ ነው። ሀቀኝነት ከሌለበት ግን በየዕለቱ እየፈረሰ የሚመጣ ነው።ሀቀኝነት ከላይኛው ኃላፊነትን ከመውሰድ ጋር የሚመጣ ነው።


የምንከውነው ክዋኔ፣ የምናደርገው ድርጊት፣ የምናስበው እሳቤ ሀቅ ላይ ያልተመሰረተ ከሆነ እርስ በእርስ የተሰናሰለ ውጤትን ልናገኝ አንችልም። ይልቁንም የዛሬው ተግባር ከነገው ጋር የሚቃረን ይሆናል። የነገው ዕቅድ ከትናንቱ ጋር የሚፋረስ ይሆናል።ከሥራው አለመቀናጀት አልፎ ደንበኞቻችን እምነት እንዲያጡብን ሊያደርግ የሚችል ይሆናል። አንድ ደንበኛ ኮሪደር ላይ ካገኘው ሠራተኛ የሚያገኘው መረጃ ፍሮንት ዴስክ ላይ ከሚያገኘው መረጃ የሚምታታበት ከሆነ እስካሁን ስናነሳቸው የነበሩ በጎ ጠባያት ሁሉ ከንቱ ይሆናሉ። ታማኝነት እናጣለን። የነበረን የሥኬት መንገድ ጥርጣሬ ውስጥ የሚወድቅ ይሆናል። ሀቀኝነት እውነት ሆኖ ጊዜያዊ ከሆነም እርስ በእርሱ ሊቃረን የሚችል ውጤትን የሚያስከትል ይሆናል።
በሁኔታዎች ላይ የሚንጠለጠል እውነታ ከሆነ ያ እውነታ መሠረቱ ጥቅመኝነት ነው። ነገር ግን ለዘላቂ እውነት፣ ለዘላቂ ደንበኝነት ማገልገል ነው ሀቀኝነት። ደንበኛችን ኪስ ውስጥ ያለውን ገንዘብ አራግፈን እኛ ድርጅት ውስጥ ለማስቀረት ብዙ አመክንዮ ብንደርድርም የዛሬ አመክዮ
ለነገም የማይሠራ ከሆነ ጊዜያዊ ጥቅም እንጂ ሀቀኝነት ሊሆን አይችልም። ሀቅ የመታመን የጀርባ አጥንት ነው።


ግልጽነትከሀቀኝነት ብዙ የራቀም ባይሆን ያለንበትን ነገር ወደ ተግባር ከመለወጣችን በፊት በግልጽ ስለማስቀመጥ የሚያልም ጠባይ ነው። በግልጽ ያልተወራ፣ በግልጽ ያልተደረገ፣ በግልጽ ለውይይት ያልቀረበ ይዋል ይደር እንጂ ቂምን፣ አለመግባባትን ብሎም ውድቀትን ይዞ ሊመጣ የሚችል ነገር ነው። አንድ ተቋም በተቀናጀ አካሄድ ይመራ፣ ይሥራና ለውጥ ያምጣ ከተባለ፣ ነገሮች ከመጀመሪያው ጀምሮ በግልጽ
መመራት አለባቸው። “ይህ ባይነገርም ችግር የለውም”፤ የሚባል ነገር የተቀናጀ ሥርዓትን በመፍጠር ላይ ዋጋ የሌለው ነገር ነው። ነገሮች በግልጽነት ከተጀመሩ ወደ ሀቀኝነት ብሎም ወደ ተቀናጀ ሥርዓትነት ይለወጣሉ።
ምግባራዊነትየትኛውም ሙያ የራሱ ምግባር አለው። በሙያችን የተነሳ የምናውቃቸው በርካታ ምሥጢሮች አሉ። ምስጢሮችን መጠበቅ የሙያ ስነ ምግባር ነው።አንዳንዴ ገጥሟችሁ ያውቃል?
ባለሥልጣናት ወይም ባለሃብቶች ወይም ዝነኞችን አየን፤ እንዲህ አደረጉ… እንዲሁም አደረጉ ተብሎ ሲወራ? ይህ ምሥጢር በየት ወጣ? በአብዛኛው በአገልግሎት ሰጪዎች በኩል አይደለምን? የእነዚህን ዝነኞች ምሥጢር መያዝ ያላስቻለ፤ ሙያ ሊሆን አይችልም። “የሺህ ፍልጥ ማሰሪው ልጥ” እንደሚባለው የሁሉም ነገር መጠቅለያው የሙያ ሥነ-ምግባርን ማክበር ነው። የወል ምግባርም ሳይረሳ።
አምስትጽናትጽናት ኃይል ከሚለይቸው ጠባያት ዋነኛው ነው። ያለ ጽናት ወደ የትኛውም ውጤት መድረስ አይቻም። ጽናት የሥነ
ልቡና የአካል፣ የአዕምሮ፣ የሥሜት ዝግጁነትን የሚጠይቅ ነው።ትናንት በሞከርነው ላይ ዛሬ ተጨማሪ ሙከራ ማካሄድን ይጠይቃል። ምናልባት ትናንት ከደረስንበት አንጻር ስኬትን ለማረጋገጥ አንድ ስንዝር ብቻ መራመድ የዛሬ ኃላፊነታችን ይሆናል። ኪሎሜትሮችን
ሮጠን አንድ የማጠቃለያ ስንዝር ጽናት አጥተን ለሽንፈት ልንዳረግ እንችላለን።በሜካኒካል ኢንጅነሪንግ ውስጥ የአንድ
ብሎን አንድ ዙር መጥበቅ እና መላላት የራሱ ትርጉም አለው። በዓለም ላይ ታላላቅ የፈጠራ ሰዎች ከጽናት ማነስ የተነሳ የአንድን ብሎን
አንድ ክርክር አዙሮ ባለማጥበቅ፣ ለዘመናት የለፉባቸው የምርምር ሥራዎች ውጤት ባለቤት ሳይሆኑ ቀርተዋል። ተመራማሪዎቹ
ዕድሜ ዘመናቸውን የለፉባቸውን ልፋቶች ምናልባት ለሽርፍራፊ የጊዜ መለኪያ ያህል ጸንቶ መሞከር ስለአቃታው ከእነሱ ቀጥለው ጥቂት የሞከሩት የፈጠራው ወይም የአሸናፊነቱ ባለቤት እንዲሆኑ ያስችላቸዋል። ጽናትን ልንለማመድባቸው የምንችላቸው ቁምነገሮች የሚከተሉት ናቸው፡-- ቀጣይነት፡- የምንሞክረውን ነገር ቀጣይነት ማረጋገጥ። ለጊዜው ብልጭ ብሎ የሚጠፋ እንዳይሆን መጠንቀቅ።


ብልጭ ብሎ እንዲጠፋ ባደረግን ቁጥር ሐሳቦቻችንን ሜዳ ላይ እየበተንን እንገኛለን። ስለዚህ ሙከራችን፣ ጥረታችን እና ትግላችን ቀጣይነት ያለው፣ የማይቋረጥ መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። ለምሳሌ ለልባችን ደኅንነት በየጠዋቱ ገመድ መዝለል ታዝዞልን ከሆነ የልብ ምታችን እስኪስተካከል ብቻ አይደለም በገመድ ዝላዩ ላይ መትጋት ያለብን። ይልቁንም የእድሜ ዘመን ተግባራችን አድርገን አጽንተን መያዝ አለብን እንጂ።- ምግባር፡- ታጋሽነት፣ አድማጭነት፣ አንባቢነት፣ ፈታሽነት ወዘተ ሀብቶቻችን ሊሆኑ ይገባል። ምግባር የሌለው ሰው የሚጓዘው ርቀት በጣም አጭር ነው። ምግባር ባጣ ቁጥር በመንገዱ ላይ የሚያጋጥመው እንቅፋት እየበዛ፣ የሚፈትነው እና የሚጣላው እየበረከተ ይሄዳልና ወደ ስኬት ሳይሆን ወደ ውድመት ይመራል። ስለዚህም ጽናት ይኖረን ዘንድ ምግባር ያስፈልጋል። በምግባሩ የተመሰገነ ሰው በጉዞው ሁሉ የሚያበረታው፣ የሚያግዘውና የሚረዳው ሰው ስለሚያገኝ እስከ መጨረሻ ድረስ ጸንቶ ለመታገል የሚያስችለውን ስንቅ እያገኘ ይሄዳል።- ልህቀት፡- ጥረት ብቻውን ድንጋይ የመግፋት ያህል ነው። ጥረት የምናደርግበትን መንገድ መመርመርም ይገባል። በምንሠራበት ሥራ በተሠማራንበት ሙያ ምንጊዜም የላቅን ሆነን መገኘት ይገባል። እዚህ ድረስ የመጣንበት መንገድ ወደ ቀጣዩ ጎዳና ላያሻግረን ይችላል። ስለዚህም የጉዳዩ ልሂቅ ሆነን ለመቀጠል መታተር ያስፈልጋል። ኃይሌ ሆቴሎችና ሪዞርቶችና ሰርቶ የመቆም ሕልም አይደለም ጉዞው፤ የዘርፉ የልህቀት ማዕከል ሆኖ የመገኘት እንጂ። ይኸንንም እያስመሰከረ ይገኛል።

በበርካታ ከተሞች ቅርንጫፎችን ከመክፈትም ባለፈ ሁሉም ቅርንጫፎች የሙያው የሥልጣኔ ልክ መታያ ወይም የልህቀት መገለጫ እየሆኑ መጥተዋል። ስለዚህ በምንሰጠው አገልግሎት ውስጥ ልቆ መገኘት ወይም እየላቁ መገኘት የጽናት ጉልበትን ያስታጥቃል።- ቁርጠኝነት፡- ጽናት አለመሸነፍ ነው። ላለመሸነፍ ደግሞ ብርቱ ትግል ያስፈልጋል፤ እየወደቁ መነሳት፣ እየተነሱ መታገል ያስፈልጋል። ስለዚህ የትኛውም ፈተና ቢመጣ ፈተናውን ለመፋለም ቁርጠኛ ሆኖ መገኘት ይጠይቃል።- ጽናት ታሪክን ይቀይራል። ታሪካቸውን የማናውቃቸው፤ ከየትነታቸው የማይታወቅ፣ አዳዲስ ዝነኞች በየጊዜው በዓለማችን ላይ ብቅ ይላሉ። ስኬታማ የተባሉትን ሰዎች ታሪክ መለስ ብለን ስንመለከት የሁሉም ለማለት በሚያስችል ደረጃ ብዙ ፈተናዎችን መውጣት የጠየቀ ስኬት ነው ያላቸው።- ነገሮች ሁሉ አልጋ በአልጋ ሆነውለት ወይም እድሜውን በሙሉ በሎተሪ ስኬት ላይ የደረሰ የለም። መነሻውን ሎተሪ ያደረገ እንኳ ቢሆን ያንን የሎተሪ ዕጣ ለማስተዳደር ብዙ ፈተናዎችን ማለፍ እና በጽናት መሥራት ጠይቆት እናገኛለን። ያለ ጽናት ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ስኬት የለም።ይህ ለየዘርፉ የሚሰራ ነው። በዓለም ላይ አንደኛ የተባሉ ሳይንቲስቶችን ተመልከቷቸው። “ትምህርት የማይገባቸው” ተብለው ከትምህርት ቤት የተባረሩ ሁሉ አሉበት። በዓለም ላይ ምርጥ የተባሉትን ደራሲዎች ተመልከቷቸው። “ ስራዎቻቸው ለአቅመ ህትመት አልደረሱም” ተብለው በተደጋጋሚ በአሳታፊዎች የተገፉ ናቸው።
በዓለም ላይ ስኬታማ የሆኑ ስፖርተኞችን ተመልከቷቸው። አጋዥ አጥተው በባዶ እግራቸው በብርድና ቁር ሲለማመዱ የነበሩ ናቸው። ይህ ሁሉ የሚያመላክተው ጽናት የስኬት መጠቅለያ መሆኑን ነው።(ምንጭ፡- “ሆኖ መገኘት” ከሚለው
አዲስ መፅሐፍ የተቀነጨበ)

 

Read 385 times