Saturday, 09 December 2023 00:00

ፀደይ ባንክ በአማራ ክልል የተከሰተውን የረሃብ አደጋ ለመመከት የ50 ሚ. ብር ድጋፍ አደረገ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በክልሉ ከ450 ሺ በላይ ሕዝብ አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ይፈልጋል ፀደይ ባንክ በአማራ ክልል የተከሰተውን የረሃብ አደጋ ለመመከት፣ የ50 ሚ. ብር ድጋፍ ያደረገ ሲሆን፤ የገንዘብ ድጋፉን
የፀደይ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ መኮንን የለውምወሰን፤ ለአማራ መልሶ ማቋቋምና ልማት ድርጅት (አመልድ) ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አለማየሁ ዋሴ፣ ባለፈው ቅዳሜ በባንኩ ዋና መ/ቤት በተከናወነ ሥነሥርዓት ላይ አስረክበዋል።
አቶ መኮንን ድጋፉን አስመልክተው እንደገለጹት፤ ባንኩ በአማራ ክልል የሰዎችብ ሞት ጭምር ያስከተለውን የድርቅና የረሃብ ችግር ለመቅረፍ የሚደረገውን ጥረት አቅም በፈቀደ መጠን ለማገዝ በማሰብ የገንዘብ ድጋፉ እንዲሰጥ ወስኗል።
የአመልድ ዳይሬክተር ዶ/ር አለማየሁ ዋሴ በበኩላቸው፤ ፀደይ ባንክ በራሱ ተነሳሽነት ለተጎዱ ወገኖች ያደረገውን ድጋፍ በድርጅታቸውና በተረጅው ወገን ስም አመስግነዋል። በተገኘው ድጋፍ
አስቸኳይ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች፣ ዕርዳታውን እንደሚያደርሱም ቃል ገብተዋል።
 አክለውም ዳይሬክተሩ፣ እንደ ፀደይ ባንክ ሁሉ፣ ሌሎች የዘርፉ ተዋንያንና ተቋማት
ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ ያደርጉ ዘንድ ጥሪ አቅርበዋል።
ዶ/ር አለማየሁ አያይዘውም፣ በአማራ ክልል በተለይ ከግንቦት ወር ወዲህ ከዝናብ መጥፋት ጋር ተያይዞ በተለይ በዋግኸምራና ሰሜን ጎንደር ዞኖች የሰዎችና የእንስሳት ሞት ያጋጠመበት አስከፊ ሁኔታ መከሰቱን ጠቅሰዋል።
ረሃቡ በሰዎች ላይ የጤና ችግር ከማስከተሉም በተጨማሪ 16 ሰዎች ለሞት መዳረጋቸውን፣ ከፍተኛ የእንስሳት እልቂት ማጋጠሙን ተናግረዋል። በክልሉ በአሁኑ ወቅት ከ450 ሺ በላይ ሕዝብ አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ እንደሚፈልግም ጠቁመዋል፡፡

Read 376 times