Saturday, 16 December 2023 20:14

የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ድሮን ለኢትዮጵያ ማቅረቧን ባስቸኳይ እንድታቆም ተጠየቀ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(2 votes)

ድሮኖቹ በሠላማዊ ሰዎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት እየወሰዱ ነው ተብሏል

የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ለኢትዮጵያ መንግስት እያደረገች ያለው የሰው አልባ አውሮፕላን ‘የድሮን’ አቅርቦት በአስቸኳይ እንድታቆም በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ የኢትዮጵያ ሲቪክ ድርጅች ጠየቁ። ድርጅቶቹ ድሮኖቹ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት እየወሰዱ ናቸው ብለዋል።
በኢትዮጵያ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ያነጣጠረው የድሮን ጥቃት በእጅጉ አሳስቦናል ያሉት በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ የኢትጵያ ሲቪክ ማህበራት፤ የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ለኢትዮጵያ እያደረገች ያለውን የድሮን አቅርቦት በአስቸኳይ እንድታቆም ጠይቀዋል።

ኢትዮ አሜሪካውያን የልማት ምክር ቤት፣ የኒውዮርክ ኒውጀረስ፣ ተስፋ ለኢትዮጵያውያን ድርጅት፣ የኢትዮጵያውያን የህዝብ ዲፕሎማሲ ኔትወርክ የተባሉት ድርጅቶች ለተባበሩት አረብ ኢምሬትስ መንግስት በጋራ በላኩት ደብዳቤ እንደጠቀሱት፤ የኢትዮጵያ መንግስት በሰው አልባ አውሮፕላኖች በሰላማዊ ዜጎች ላይ እየወሰደ ያለው ጥቃት በእጅጉ አሳስቦናል ብለዋል።
“የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ መንግስት ሰላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት በማድረስ ላይ የሚገኙትን ድሮኖች ለኢትዮጵያ መንግስት ከማቅረብ እንዲቆጠብ” ሲሉ አሳስበዋል ድርጅቶቹ።
“የዓለም አቀፉ ህግና የጀኔቫው ስምምነት አንቀፅ 10 እና 16 ሰላማዊ ዜጎችን በቦምብ በመመታት፣ ሰብል በማጥፋት፣ የውሃ ግድቦችን በመደብደብ ጉዳት ማድረስን የሚከለክል በመሆኑ አገሪቱ ከዚህ ድርጊቷ የማትቆጠብ ከሆነና ድሮን ማቅረቧን የምትቀጥል ከሆነ አለም አቀፍ ህጉን በመጥቀስ ክስ ለማቅረብ እንገደዳለን” ብለዋል በደብዳቤያቸው፡፡
ከአገሪቱ አሳሳቢ መረጃዎች እየወጡ ናቸው ያሉት ድርጅቶቹ፤ በሰላማዊ ሰዎች ላይ፣ ረሃብን እንደ ጦር መሳሪያ መጠቀምና የመሳሰሉ ግፎች እየተፈፀሙ ስለመሆናቸው ሪፖርቶች ማመልከታቸውን ጠቁመዋል።
በዚህ ሁኔታም እስከ አሁን ከ100 በላይ የድሮን ጥቃቶች ተፈፅመዋል ሲሉ መግለፃቸውን ዶቼ ቬሌ ዘግቧል። የአሜሪካ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቅርቡ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ በጠራው ጉባዔ፣ ይኸው የድሮን ጥቃት ጉዳይ ተነስቶ ውይይት የተደረገበት ሲሆን የአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ

ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር ወደ ቱርክና የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ በመጓዝ፣ ሰው አልባ አውሮፕላኖች ለኢትዮጵያ መስጠቱ አሜሪካንን እንደሚያሳስባትና ድሮኖችም በአገሪቱ ያለውን ሁኔታ ይበልጥ እያወሳሰቡ መሆናቸውን በመግለፅ ለምክር ቤቱ መናገራቸው ይታወሳል፡፡

Read 1815 times